ከኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) 5ኛ ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

Ethiopian Democratic Press Conference, December 2010ኢዴፓ መጋቢት 11 ቀን 2003 ዓ.ም 5ኛ ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን በአዲስ አበባ ከተማ ያካሂዳል፡፡ በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ከ250 በላይ የሆኑ በየደረጃው የሚገኙ የፓርቲው ድርጅታዊ መዋቅር ተወካዮች የሚሳተፉ ሲሆን ጉባኤው በተለያዩ አበይት አጀንዳዎች ዙሪያ ውይይት አካሂዶ ውሳኔዎችን ያስተላልፋል፡፡
ጉባኤው የማዕከላዊ ኮሚቴውን የሁለት አመት የስራ ክንውንና የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴ የስራ ሪፖርቶችን አዳምጦ ያጸድቃል፡፡ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብና የፖለቲካ ፕሮግራም ላይ ውይይት በማድረግም ሊሻሻሉ የሚገባቸው ጉዳዮች ከተገኙ የማሻሻያ ውሳኔዎችን ይሰጣል፡፡ የስራ ጊዜውን የጨረሰውን አመራር በማሰናበትም ለሚቀጥሉት ሁለት አመታት ፓርቲውን የሚመራውን የአመራር አካል ይመርጣል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጉባኤው የፓርቲውንና የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በጥልቀት በመገምገም በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የአቋም መግለጫ ያወጣል፡፡ ጉባኤው ሊወያይባቸው ይገባል ተብለው የታሰቡ አስር ወቅታዊ ጉዳዮች አስቀድመው ተመርጠው በአሁኑ ወቅት በየሳምንቱ በፓርቲው አባላት ተከታታይ ውይይት እየተደረገባቸው ሲሆን ከእነዚህ ውይይቶች የሚመነጩት ሃሳቦች ተጨምቀው ለጉባኤው በረቂቅነት የሚቀርቡበት ሁኔታ እየተመቻቸ ይገኛል፡፡ ጉባኤው በጥልቀት ተወያይቶ አቋሙን ይገልጽቸዋል ተብለው የሚጠበቁት ዋና ጉዳዮች፡-
1.    በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሊብራል ዴሞክራሲ አዋጭነት፣
2.    ህገ-መንግስትና ህገ-መንግስታዊ ጉዳዮች በኢትዮጵያ፣
3.    ወቅታዊ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች፣
4.    ወቅታዊ ማሕበራዊ ጉዳዮች፣
5.    ወቅታዊ የውጭ ጉዳዮች፣
6.    ምርጫ 2002 እና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ወቅታዊ የኃይል አሰላለፍ፣
7.    የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተዋናኞችና ወቅታዊ ሚናቸው፣
8.    የተቋማት ሚና በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት፣
9.    የፖለቲካ ፓርቲዎች የትግል ስልት፣
10.    የኢዴፓ የወደፊት ዋናዋና የትግል አቅጣጫዎች የሚሉ ናቸው፡፡

ኢዴፓ 5ኛ ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባኤው በስኬት ተጠናቆ ቀጣይ የትግል እንቅስቃሴው ውጤታማ ይሆን ዘንድ ከህብረተሰቡ የተለያዩ ተሳትፎዎችንና እገዛዎችን ይጠብቃል፡፡ ለጉባኤው በመወያያ ሃሣብነት በሚቀርቡ ጉዳዮች ዙሪያ አባላት የሚያደርጓቸው ውይይቶች እስከ ጉባኤው እለት ድረስ በየሳምንቱ በጋዜጦች አማካኝነት ይፋ ስለሚደረጉ ህብረተሰቡ እነዚህን ውይይቶች እየተከታተለ የራሱን አስተያየት እንዲሰጥባቸው፣ጋዜጦችም እነዚህን የውይይት መነሻ ሃሳቦች ለህዝብ በማቅረብ ረገድ ትብብር እንዲያደርጉ ኢዴፓ ጥሪውን ያቀርባል፡፡ ህብረተሰቡ ኢዴፓ ሊያሻሽላቸው ይገባል ብሎ የሚያምንባቸው የፖለቲካ ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብን የሚመለከቱ ሃሳቦች ካሉም ጥቆማዎቹን ተቀብሎ ለጠቅላላ ጉባኤው ውይይት ለማቅረብ ያለውን ፍላጎት ይገልጻል፡፡

ከፊታችን የሚካሄደው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ፓርቲውን በሃሳብ ብቻ ሳይሆን በሰው ኃይልም የተጠናከረ እንዲሆን የማድረግ አላማ ስላለው በፓርቲው የፖለቲካ ፕሮግራም እምነት ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም በፓርቲው አባልነት እየተመዘገቡ በፓርቲው ውስጥ የጎላ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አዴፓ ጥሪውን ያቀርባል፡፡ ይህንን ድርጅታዊ ጉባኤ በሚፈለገው መጠን ውጤታማ ለማድረግም ሆነ ከጉባኤው ማግስት ፓርቲው የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድርን በምርጫ አሸንፎ ለመረከብ የሚያደርገው ትግል ለውጤት እንዲበቃም የፓርቲውን አላማ የሚደግፉ የህብረተሰብ ክፍሎች የገንዘብ እርዳታ በማድረግ ፓርቲውን እንዲያጠናክሩ ኢዴፓ በአክብሮት ይጠይቃል፡፡

ታህሣስ 21 ቀን 2003
የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ
አዲስ አበባ

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter