በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሊበራል ዴሞክራሲ አዋጭነት

በኢዴፓ 5ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ቀርበው በሚፀድቁ የውይይት ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የተደረገ ቅድመ-ውይይት

መጋቢት 11 ቀን 2003 ዓ.ም የሚካሄደው የኢዴፓ 5ኛ ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ተወያይቶ አቋም በሚወስድባቸው 10 አጀንዳዎች ዙሪያ የፓርቲው አባላት ለጉባኤው ረቂቅ ሃሳብ ለማመንጨት የሚያስችል ቀዳሚ ውይይት ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ታህሣስ 24 ቀን 2003 ዓ.ም በተካሄደው የመጀመሪያ ስብሰባ “በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሊበራል ዴሞክራሲ አዋጭነት” በሚል የመጀመሪያ የመወያያ ነጥብ ላይ ውይይት ተካሂዶ የሚከተለው መግባባት ላይ ለመድረስ ተችሏል፡፡
የፓርቲው አባላት በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ባደረጉት ጥልቅ ውይይት – የሊበራል ዴሞክራሲ ታሪካዊ አመጣጥንና በአሁኑ ወቅት የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ፤ ሊበራል ዴሞክራሲ ከሌሎች ርዕዮተ አለማዊ አቅጣጫዎች ጋር ሲነጻጸር ዘላቂ ሰላምን ከማምጣት፣ ዴሞክራሲያዊ ስርአትን ከማጠናከር፣ ማህበራዊ ችግሮችን ከማቃለል፣ የመቻቻል ፖለቲካን ከማስፈን፣በእውነተኛ የነፃ-ገበያ ስርአት አማካኝነት ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትን ከማምጣትና የግልን የቡድን መብቶችን በተሞላ ሁኔታ ከማክበር አንፃር ያለውን ጠቀሜታ ተወያይቶበታል፡፡ በአጠቃላይም ሊበራል ዴሞክራሲ በአሁኑ ወቅት ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ከሚያራምደው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር በተነፃፃሪ የአገራችን ወቅታዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ተመራጭ የሚያደርጉትን ባህሪዎች ለመገምገም ሞክሮል፡፡

 

በዚህ ውይይት ሊበራል ዴሞክራሲ ከብዙ መቶ አመታት ጀምሮ በምዕራቡ ዓለም ባሳለፍነው ሂደት ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር እራሱን እያጣጣመ፣ ከራሱ ድክመቶችና ስህተቶች በድፍረት እየተማረና በሌሎች ርዕዮተ-ዓለማዊ መስመሮች ውስጥ ያሉ በጎና ጠቃሚ አስተሳሰቦችን ጭምር በሂደት እየተቀበለ እራሱን በስክነት በማደስና በማጠናከር በአሁኑ ወቅት በአለም ላይ ከሁሉም የተሻለ ገዢ አስተሳሰብ ለመሆን የበቃ መስመር መሆኑ ታምኖበታል፡፡ ሊበራል ዴሞክራሲ በአንድ በኩል ሁሉም ነገር እንደነበረ ይቀጥል የሚል አክራሪነትን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሁሉም ነገር ስር ነቀል በሆነ የህዝብ እንቅስቃሴ በዘመቻ መልክ ይለወጥ የሚል የአብዮታዊነት ባህሪን የሚቃወምና በጥናትና በህብረተሰብ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ የሰከነ ለውጥን የሚደግፍ መስመር በመሆኑ በሃገራችን ዘላቂ ሰላምና የመቻቻል ፖለቲካ እንዲመጣ የሚያስችል መስመር መሆኑ ታምኖበታል፡፡

በዚህ ነጥብ ላይ የፓርቲው አባላት ባደረጉት ውይይት አገራችን አሁን ለምትገኝበት ውስብስብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ለመጋለጥ የበቃችው ሲፈራረቁባት በኖሩት የፊውዳልና የግራ ፖለቲካ አራማጅ ስርዓቶች አማካኝነት ከሊበራል ዴሞክራሲ አስተሣሠብ ጋር ሳትተዋወቅ በመኖሯ መሆኑን አስምሮበታል፡፡ የ1967 ዓ.ምቱ የአገራችን አብዮታዊ ለውጥ በንጉሱ ዘመን የነበሩትን ለካፒታሊስት ስርዓት ግንባታ መሰረት የሚሆኑ በጐ ነገሮችንም ጭምር ሙሉ በሙሉ ጥርግርግ አድርጐ በማጥፋት ለአገሩ ባህልና ነባራዊ ሁኔታ ባዕድ በሆነ የማርክሲዝም ሌኒኒዝም ርዕዮተ-ዓለም እንዲተካ ከማድረግ ይልቅ በነበሩት በጎ ነገሮች ላይ አዲስ በጎ ነገሮችን በመጨመር አገሪቱ ወደ ሊበራል ዴሞክራሲ እንድትሸጋገር ተደርጎ ቢሆን ኖሮ የወቅቱ የኢትዮጵያ ሁኔታ እጅግ የተለየና የተሻለ ይሆን እንደነበር ታምኖበታል፡፡
የ1960ዎቹ የለውጥ አጋጣሚ በተሳሳተ አቅጣጫ መሄዱ ለወቅቱ የአገራችን ሁኔታ ዋና ተጠያቂ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በአሁኑ ወቅት በመንግስት ስልጣን ላይ የሚገኙትም ሆኑ የተቃዋሚውን ጐራ በመምራት ላይ የሚገኙት አብዛኛዎቹ የፖለቲካ መሪዎች ከግራ ፖለቲካ አስተሣሠብና ባሕል ሙሉ በሙሉ ያልተላቀቁ መሆናቸው የሊበራል ዴሞክራሲ አስተሣሠቦች በህዝቡ ውስጥ ተገቢውን ቦታ እንዳያገኙ በማድረግ እረገድ የፈጠረው ጫና ከፍተኛ መሆኑ ታምኖበታል፡፡ከዚህ ግምገማ በመነሳት በአገራችን ለዘላቂ ሰላምና ለመቻቻል ፖለቲካ መሰረት የሚሆን የሊበራል ዴሞክራሲ አስተሣሠብ ስር እንዲሰድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚጠበቀው በዋናነት ከግራ ፖለቲካ አስተሣሠብ ጋር ተቆራኝቶና ተጣብቶ ካላደገው ከአዲሱ የአገሪቱ ትውልድ መሆኑ ታምኖበታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ሊበራል ዴሞክራሲ በአንድ አገር ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሊመጣ የሚችለው በመንግስት ሳይሆን በዋናነት በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ የማይተካ ሚና ነው ብሎ የሚያምን መስመር በመሆኑ በአገራችን እውነተኛ የነፃ-ገበያ ስርዓት እንዲጠናከርም ሆነ ስራ ፈጣሪ የሆነ የኢንቨስትመንት መስክ በበቂ መጠን እንዲስፋፋ የተሻለ አማራጭ መሆኑ ታምኖበታል፡፡ ሊበራል ዴሞክራሲ አሁን በደረሰበት የዕድገት ደረጃ በህዝብ ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ ማህበራዊ ቀውሶችን ለመታደግ ሲባል በኢኮኖሚ ውስጥ የሚደረግ በህግ የተገደበ የመንግስት ጣልቃ ገብነትንና ጊዜያዊ የድጎማ አሰራሮችን የሚደግፍ በመሆኑ “ሊበራሊዝም ለሃብታሞች ብቻ የቆመ ስርአት ነው” በሚል ከአንዳድ የግራ ኃይሎች የሚቀርብበትን ትችት ጊዜው ያለፈበትና ሊብራሊዝም በአሁኑ ወቅት የደረሰበትን ደረጃ ያልተገነዘበ መሆኑ ታምኖበታል::

ሊበራሊዝም የሁሉንም ዜጎች መብት በእኩልነትና በተሟላ ሁኔታ ለማክበር ለሚያስችለው የግለሰቦች መብት መከበር ቀዳሚና ልዩ ትኩረት የሚሰጥ አስተሣሠብ በመሆኑ ዜጎች ከየግል አስተሣሠባቸውና ፍላጎታቸው በመነጨ እንዲከበርላቸው የሚፈልጉት የቡድን መብት በተሟላ ሁኔታ ሊከበር የሚችለው በሊበራል ዴሞክራሲ አስተሣሠብ መሆኑ ታምኖበታል፡፡ በአሁኑ ወቅት የግለሰብ ብቻ ሳይሆን የቡድን መብቶች በአግባቡ ሲከበርባቸው የሚታዩት አገሮች የሊበራል ዴሞክራሲ አራማጅ የሆኑ የምዕራብ አገሮች በመሆናቸው ኢህአዴግ “የቡድን መብትን አብዮታዊ ዴሞክራሲ በሚያስከብረው መጠን ሊበራል ዴሞክራሲ ሊያስከብረው አይችልም” በማለት የሚያቀርበው ትችት የተሳሳተና ከአለም ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የማይጣጣም መሆኑ አምኖበታል::

አገራችን በአሁኑ ወቅት ከምትገኝበት ዝቅተኛ የማህበረ-ኢኮኖሚ የዕድገት ደረጃ ጋር በተያያዘ መካከለኛ ገቢ ያለው ህብረተሰብ (middle class) አለመኖሩ ሊበራል ዴሞክራሲን በሚፈለገው ፍጥነት በአገሪቱ ለመገንባት የማያስችል እንቅፋት መፍጠሩ በውይይቱ የታመነበት ሲሆን፣ ነገር ግን ለሊበራል ዴሞክራሲ መጠናከር መሰረት የሚሆን መካከለኛ ገቢ ያለው ህብረተሰብ በአገሪቱ እንዲፈጠር ለማድረግም የሚቻለው በእያንዳዷ ዕለት የሊበራል ዴሞክራሲ አስተሣሠብ በህዝቡ ውስጥ በፍጥነት እንዲሰርፅ በመታገል መሆኑ ታምኖበታል:: በአሁኑ ወቅት በሊበራል ዴሞክራሲ አስተሣሠብ ለከፍተኛ እድገት የበቁ አገሮች የሊብራል ዲሞክራሲ አራማጅ በሆኑበት በመጀመሪያ ወቅት ላይ የነበሩበት ማህበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ደረጃ ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ያልተሻለ እንደነበር በማስታወስም “ሊበራል ዴሞክራሲን በአገራችን ለመገንባት የወቅቱ የማህበረ-ኢኮኖሚ ደረጃችን አይፈቅድልንም” የሚለው የኢህአዴግ ትችት ውሃ የማይቋጥር መሆኑ ታምኖበታል:: ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በአገራችን የሚታየው አንፃራዊ የኢኮኖሚ ዕድገትና የትምህርት መስፋፋት በአገራችን መካከለኛ ገቢ ያለው ህብረተሰብ በስፋት እንዲፈጠር አስፈላጊ ቅድመ-ሁኔታዎች በመሆናቸው እነዚህ በጎ ጅምሮች በዙሪያቸው የሚታየው ጉድለትና ድክመት ታርሞ ለአፍታ ሳይስተጎጐሉ የበለጠ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ኢዴፓ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት ታምኖበታል፡፡

የኢዴፓ አባላት ከሊበራል ዴሞክራሲ በተፃራሪ ባሁኑ ወቅት ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ እያራመደ የሚገኘውን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር ለመገምገም ሞክሮል፡፡ በተደረገው ግምገማም የኢህአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር በካፒታሊስትዊ ስርዓት ማእቀፍ ውስጥ ከሚገኙ አማራጮች ጋር ምንም ዓይነት ተዛምዶ የሌለውና ይልቁንም በግራ ፖለቲካ አስተሳሰብ ማዕቀፍ ውስጥ የሚገኝ አስተሳሰብ በመሆኑ፤ የህግ የበላይነትንና የተቋማት ግንባታን መሰረት አድርጎ በሂደት ከሚመጣ ጤናማ የለውጥ ሂደት ይልቅ በዘመቻ የሚፈፀም አብዮታዊ ስር-ነቀል ለውጥን የሚያራምድ በመሆኑ፤ በአገራችን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲመጣ ወሳኝና የማይተካ ሚና ያለው ኃይል የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ሳይሆን መንግስት ነው ከሚለው የተዛባ እምነቱ በመነጨ የግል ባለሀብቶችን በጥርጣሬና በስጋት የሚያይ በመሆኑ፤ በቡድን መብቶች መከበር ስም የሁሉም መብቶች መከበር መሰረት የሆኑት የግለሰብ መብቶች በቂት ትኩረት እንዳያገኙ ያደረገና ሰፊ ትርጉምና ይዘት ያለውን የቡድን መብትም በቁንፅል የብሄር ብሄረሰቦች መብት ብቻ አድርጎ የሚያይ ጠባብ አስተሣሠብ በመሆኑ፤ ባጠቃላይም ተገቢ ሚዛን በአልጠበቀ ሁኔታ ህዝቡን በአንድነት ለሚያስተሳስሩ ጉዳዮች ሳይሆን በህዝቡ ውስጥ ለሚገኙ ልዩነቶች ልዩ ትኩረት የሚሰጥና “ወዳጅና ጠላት” በሚል ተገቢ ያልሆነ ፍረጃ ህብረተሰቡን በተለያዬ የልዩነት ነጥቦች እያቧደነ ቅራኔ የመፍጠር ስልት የሚያራምድ አስተሣሠብ በመሆኑ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አገራችንን ለዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ ስርአትም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ብልፅግና የሚያበቃ መስመር አለመሆኑን አምኖበታል::

የኢህአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሣሠብ በአገሪቱ የግል ኢንቨስትመንትን በማስፋፋትና የታክስ መሰረትን በማስፋት የመንግስት ገቢ በዘላቂነት እንዲጨምር ከማድረግ ይልቅ መሬትን የመሰሉ ቁልፍ የሃብት ምንጮችን በብቸኝነት ተቆጣጥሮ በመያዝ በገበያ ውስጥ እጥረት በመፍጠር የኪራይ ሰብሳቢነት ሚና እራሱ እየተጫወተ እንደሆነና በአገሪቱም በአሁኑ ወቅት ኢህአዴግ እየፈጠራቸው የሚገኘው በርካታ ባለሃብቶች በገበያ-ስርዓት ከሌላው ዜጋ ጋር በእኩልነት ተወዳድረው የሚበለፅጉ ሳይሆን መንግስት የሚፈጥረውን ዕጥረት በመጠቀም በአቋራጭ የሚከብሩ ኪራይ ሰብሳቢ ባለሀብቶች መሆናቸው ታምኖበታል፡፡

ከዚህ አጠቃላይ ግምገማ በመነሳት በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ውይይት ያደረጉት የፓርቲው አባላት ኢዴፓ ቀደም ሲል ባካሄደው ድርጅታዊ ጉባኤዎቹ ሊበራል ዴሞክራሲን ለማራመድ የወሰናቸው ውሳኔዎች በሃሳብ ብቻም ሳይሆን በሂደት በተግባር የተረጋገጡ ትክክለኛ ውሳኔዎች መሆናቸውን በማመን በቅርቡ የሚካሄደው የፓርቲው 5ኛ ጠቅላላ ጉባኤም ይሄንኑ ውሳኔ በድጋሚ አረጋግጦ እንዲያልፍ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ ኢዴፓ በአገሪቱ ጠንካራ የግል ክፍለ ኢኮኖሚና በኢኮኖሚ ውስጥ በቂ የገበያ ውድድር ገና አለመፈጠሩን ግምት ውስጥ በማስገባት በአሁኑ ወቅት በኢኮኖሚው ውስጥ የሚኖርን በህግ የተወሰነና የነፃ-ገበያ ስርአትን የማይፃረር ጊዜያዊ የመንግስት ጣልቃ ገብነት መደገፉ ትክክለኛ አቋም መሆኑ ታምኖበታል፡፡ ከዚህ አቋሙ ጋር በተያያዘም ኢዴፓ ከርዕዮተ-ዓለም አሰላለፍ አንፃር የሚኖረው ቦታ አሁንም መካከለኛ ቀኝ (center right) ሆኖ እንዲቀጥል አባላቱ አሣስበዋል፡፡ የሚቀጥለው ውይይትም “ህገ-መንግስትና ህገ-መንግስታዊ ጉዳዮች በኢትየጵያ” በሚል ዕርስ ላይ እንዲሆን ወስነዋል::

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter