የዋጋ ተመኑ የህዝቡን የኑሮ ውድነት በዘላቂነት ለመፍታት በቂ መፍትሄ አይደለም!

ከኢዴፓ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

ኢዴፓ ላለፉት አምስት ዓመታት በአገራችን መከሰት የጀመረው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት አፋጣኝና ተገቢ መፍትሄ እንዲሰጠው ለመንግስት ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርብ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ መንግስት በአንድ በኩል የችግሩን ክብደት በተመለከተ የተሳሳተ ግንዛቤ የነበረው በመሆኑ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የችግሩን ምንጭ ሊያደርቅ የሚችል ተገቢ የመፍትሔ እርምጃ በተገቢው ወቅት መውሰድ ባለመቻሉ ችግሩ ተባብሶ ከፍተኛ አገራዊ አደጋ ለመሆን በቅቶል፡፡ ችግሩ አሁን በደረሰበት ደረጃ አሣሣቢ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር ከመሆን አልፎ ፖለቲካዊ ችግር ወደመሆን እየተሸጋገረ ይገኛል፡፡ ይህም ስርአቱ የሚያራምደው አጠቃላይ የኢኮኖሚ አቅጣጫና እስትራቴጂ በብዙ ስህተቶች ድክመቶች የተሞላ መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡

መንግስትነ ሰሞኑን በተመረጡ ምርቶች ላይ ያደረገው የዋጋ ተመንና ውሳኔውን ለማስፈጸም የጀመረው የዘመቻ ስራ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል በቂ መፍትሔ ባይሆንም ቢያንስ በጣም ዘግይቶም ቢሆን መንግስት የችግሩን ክብደትና አደገኛነት በተወሰነ ደረጃ እተረዳው መምጣቱን አሳይቶል፡፡ይህንን መንግስት ለችግሩ መስጠት የጀመረውን ትኩረት ኢዴፓ እንደ አንድ በጎ ጅምር በአድናቆት ይመለከተዋል፡፡ ነገር ግን የኢዴፓ አመራር ሰሞኑን መንግስት የወሰደውን የዋጋ ተመን እርምጃ በጥልቀትና በዝርዝር ለመገምገም ባደረገው ሙከራ እርምጃው የህዝቡን የኑሮ ውድነት በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል በቂ መፍትሔ ሆኖ አላገኘውም፡፡

ኢዴፓ ከ15 ቀናት በፊት መንግስት በአገሪቱ እየተባባሰ የመጣውን ያዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት የሚያቃልል የመፍትሄ እርምጃ እንዲወስድ መግለጫ አውጥቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዚህ መግለጫው ላይ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላሉ ብሎ የሚያምንባቸውን የመፍትሄ ሀሣቦች በዝርዝር ጠቁሞ ነበር፡፡ የጠቆማቸው የመፍትሄ ሃሳቦችም፡-
– ከዋጋ ንረቱ ጋር የሚመጣጠን የደመወዝና የጡረታ አበል ጭማሪን፣

– ተደራራቢ የተጨማሪ እሴት ታክስ ክፍያን ማስወገድ፣

– የኑሮ ውድነቱ በተከሰተባቸው የህብረተሰቡ ፍጆታዎች ላይ የሚደረግ የተጨማሪ እሴት ታክስ ቅነሳና ስረዛ፣

– የመንግስት የካፒታል በጀት ጊዜያዊ ቅነሳ፣

– በነዳጅ ዋጋ ላይ የሚደረግ ጊዜያዊ የመንግስት ድጎማ፣

– የዋጋ ንረቱ በሚታይባቸው ምርቶች ላይ የሚደረግ የአቅርቦት መጠን ጭማሪንና

– ህገ-ወጥ ተግባር በመፈፀም የዋጋ ንረቱን በሚያባብሱ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰድ የቁጥጥር እርምጃዎች የሚካተቱ የመፍትሔ ሃሳቦች ናቸው፡፡

በአገራችን በተከሰተው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት በዘላቂነት ሊፈታ የሚችለው ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትን ከችግሩ ምንጮች ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተያያዙ ጉዳዮች ያካተቱ የመፍትሄ እርምጃዎችን በመውሰድ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት መንግስት ችግሩን ለመፍታት እየሞከረ የሚገኘው ግን ከጠቆምናቸው ሰባት የመፍትሄ ሃሳቦች ውስጥ በአንዱ ብቻ – በነጋዴው ህብረተሰብ ላይ ቁጥጥር በማድረግ ዙሪያ ብቻ ያተኮረ ነው፡፡ ቀደም ሲል ኢህአዴግ በአገሪቱ የተከሰተውን የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት ለነጋዴዎች ብድር በመከልከልና ከውጭ የሚመጣ ስንዴን በገቢያ ውስጥ በመርጨት ብቻ ለመቆጣጠር ያደረገው ጥረት ችግሩን በብቃትና በዘላቂነት ማቃለል ሳያስችለው እንደቀረው ሁሉ አሁንም ይህ በነጋዴው ህብረተሰብ ላይ የሚደረግ ቁጥጥርና የዋጋ ተመን እርምጃ ብቻውን ችግሩን በዘላቂነትና በበቂ ሁኔታ ሊፈታው አይችልም፡፡ ምክንያቱም በንግዱ ህብረተሰብ ዙሪያ የሚታየው ችግር የዋጋ ንረቱን እያባባሱ ከሚገኙት በርካታ ችግሮች ውስጥ አንዱ እንጂ ብቸኛው አይደለም፡፡ ስለዚህም የሰሞኑ የመንግስት እርምጃ የኑሮ ውድነቱን በዘላቂነት ሊፈታ አይችልም ብቻም ሳይሆን በአሁኑ ወቅት ያለበቂ ዝግጅትና ጥናት መንግስት እየወሰደ ያለው የዋጋ ተመን እርምጃ የህዝቡን የኑሮ ውድነት የበለጠ የሚያባብስና የግብይት ሰላምን የሚያናጋ ውጤት ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት ፓርቲያችን አድሮበታል፡፡

ኢዴፓ ህገ-ወጥ ድርጊት በመፈፀም የኑሮ ውድነቱን እያባባሱ በሚገኙ ነጋዴዎች ላይ መንግስት ጥብቅ የቁጥጥርና የቅጣት እርምጃ መውሰድ አለበት ብሎ ሲያምንና ሲጠይቅም ይህ የኢዴፓ አቋም አሁንም መንግስት ዋጋን በመተመን እየወሰደ ከሚገኘው እርምጃ የተለየ መሆኑን መግለፅ ይወዳል፡፡ በኢዴፓ እምነት ሆን ብለው የተለያዩ ሸቀጦችንና ምርቶችን እየሰበሰቡ በመከዘንና ሰው ሰራሽ እጥረት በገቢያ ውስጥ እየፈጠሩ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት የሚሞክሩ፤ የነፃ-ገበያ ስርዓት በሚፃረር ሁኔታ እርስ በእርስ እየተመካከሩ የራሳቸውን የመሸጫ ዋጋ በአድማ በመተመን በሸማቹ ህብረተሰብ ላይ በደል በሚፈፅሙ ነጋዴዎች ላይ መንግስት ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግና አጥፍተው ሲገኙ ጥብቅ የቅጣት እርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ እንዲህ አይነቱን የመንግስት እርምጃ ከአድሎና ከማንኛውም ወገንተኛነት በፀዳ ግልፅነት ያለው አሰራር መፈፀም የሚገባው ሲሆን ለአፈፃፀሙ ተግባራዊነትም ህዝቡ ከመንግስት ጎን በመቆም የጎላ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ኢዴፓ በንግዱ ህብረተሰብ ላይ ቁጥጥር መደረግ አለበት ሲል እንዲህ አይነቱን የነፃ ገበያ ስርዓት ጥያቄ ውስጥ የማያስገባ አሰራር ተግባራዊ እንዲሆን በመፈለግ ነው እንጂ አሁን መንግስት እየተገበረው የሚገኘው አኳኋን የዋጋ ተመን በዘመቻ መልክ ተግባራዊ ማድረግ ችግሩን በብቃትና በዘላቂነት ይፈታዋል ብሎ በማመን አይደለም፡፡ መንግስት አሁን እየወሰደ በሚገኘው እርምጃም ሆነ እኛ እያቀረብነው በምንገኘው አማራጭ መንገድ በንግዱ ህብረተሰብ ላይ የሚደረገው ቁጥጥር የቱንም ያህል በብቃት ተግባራዊ ቢያደርግ እንኳ በአገራችን የተከሰተውን የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት ለማቃለል አንድ ተጨማሪና አጋዥ ግብዓት ይሆናል እንጂ ችግሩን በብቃትና በዘላቂነት ለመፍታት አያስችልም፡፡ ችግሩ በወሳኝ መልኩ ሊፈታ የሚችለው በአንድ ጉዳይ ላይ በመረባረብ ብቻም ሳይሆን ከላይ በዝርዝር ያቀረብናቸውንና ከችግሩ ምንጭ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሰባት የመፍትሄ ሃሳቦች ግምት ውስጥ ያስገባ እርምጃ በመውሰድ ነው፡፡ መንግስት እስከ አሁን እያደረገው እንደሚገኘው በራሱ ዙሪያ የሚገኙ መፍትሄዎችን ምንም ሳይነካካ በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ዙሪያ የሚታዩ ድክመቶችን በማስተካከል ብቻ ችግሮችን ለመፍታት የሚያደርገው ሙከራ ችግሩን በበለጠ በማባባስ በስተቀር ዘላቂ መፍትሄ ሊያመጣ አይችልም፡፡

በመንግስት በአሁኑ ወቅት የዋጋ ተመንን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ እየወሰደ የሚገኘው እርምጃ ችግሩን በብቃትና በዘላቂነት የማይፈታው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ስለአፈፃፀሙ ተገቢ ጥናትና ዝግጅት ያልተደረገበት መሆኑ በግልፅ እየታየ ነው፡፡ ይህን ለማለት የሚያስደፍሩን ምክንያቶች፡-

 

  1. አብዛኛዎቹ ተመን የወጣባቸው ምርቶች ደሃውን ህብረተሰብ የማይመለከቱ ከመሆናቸው በላይ ደሃውን ህብረተሰብ በሚመለከቱት ምርቶች ላይ የተደረገው የዋጋ ቅናሽም ትርጉም ያለው ሆኖ አልታየም፡፡ አንዳንዶቹ የዋጋ ተመን የተጣለባቸው ምርቶች ደሃውን ህብረተሰብ ተጠቅሞባቸው የማያቅ ሲሆን ደሃው ህብረተሰብ በየዕለት ኑሮው የሚጠቀምባቸው በርካታ ምርቶች ደግሞ በዋጋ ተመኑ ላይ ተካተው አልታዩም፡፡

 

  1. ዋጋ ተመኑ ቸርቻሪዎችን ብቻ እንጂ አምራቾችንና አከፋፋዮችን የሚመለከት አይደለም፡፡ ይህም በራሱ በግብይት ሰንሰለቱ ላይ የተዛባ አሰራር የሚፈጥርና በንግዱ ህብረተሰብ መካከልም ሆነ ነጋዴው ከሸማቹ ጋር ባለው ግንኙነት ከፍተኛ አለመግባባት የሚያስከትል ይሆናል፡፡

 

  1. አብዛኛዎቹ ምርቶች የዋጋ ተመን የተደረገባቸው ይዘታቸውን ሳይሆን መጠናቸውን መሰረት በማድረግ ስለሆነ እንዲህ አይነቱ አሰራር በአገሪቱ ከፍተኛ የምርት ጥራት ችግር ያስከትላል፡፡

 

  1. የዋጋ ተመኑ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን ብቻ ሳይሆን በአስመጪዎች ፍላጎትና ምርጫ ከውጭ የሚገቡትን ጭምር የሚያካትት በመሆኑ በአሁኑ ወቅት አገር ውስጥ የገቡ ምርቶች አንድ ጊዜ በተመኑ መሰረት ተሸጠው ካለቁ በኋላ ከፍተኛ የአቅርቦት እጥረት በአገሪቷ ሊያስከትል ይችላል፡፡

 

  1. የዋጋ ተመኑ በተለያዩ የጥራት ደረጃ ላይ የሚገኙ የአገልግሎት ሰጪዎችን ግምት ውስጥ ያላስገባ በመሆኑ ከፍተኛ የአገልግሎት (በተለይ የቤት ኪራይና የሰራተኛ ደመወዝ) ያለባቸው ድርጅቶች ለኪሳራ ሊዳርግ ይችላል፡፡

 

  1. የዋጋ ተመኑ የአቅርቦት እጥረት የተፈጠረባቸውን ብቻም ሳይሆን እጥረት ያልተፈጠረባቸውን ምርቶችም ጭምር የሚያመለክት በመሆኑ ወደፊት ባለሃብቶች በአገሪቱ የነፃ-ገበያ ስርዓት ሰተማምነው የሩቅ ጊዜ የአምራችነት ኢንቨስትመንት ውስጥ እንዳይገቡ ያደርጋል፡፡ በአጠቃላይ እንዲህ አይነቱን በቂ ጥንቃቄና ጥናት ያልተደረገበት የዘመቻ አሰራር የምርት አቅርቦት እጥረት በአገሪቱ ሊያስከት የሚችል ከመሆኑም በላይ የጥቁር ገቢያ እንዲስፋፋ በማድረግ የአገሪቱን የነፃ-ገበያ ስርዓት ትርጉም የለሽ ያደርገዋል፡፡ ችግሩ እንዲቃለልለት የምንፈልገው ህዝብም ወደፊት በተመጣጣኝ ዋጋ ብቻም ሳይሆን በውድ ዋጋም አንዳንድ ምርቶች ፈልጎ እንዳያገኝ የሚያደርግ አደጋ ሊያስከትል ይችላል፡፡ ስለሆነም በኑሮ ውድነቱ ክፉኛ የተጎዳው ህዝብ ከደረሰበት ህልውናን የሚፈታተን የኑሮ ጫና አኳያ ሰሞኑን በመንግስት እየተወሰደ ያለው እርምጃ አስደሳች መስሎ ቢታዬውም ከላይ በዝርዝር ባስቀመጥናቸው ድክመቶች ምክንያት የወቅቱ የመንግስት እርምጃ የኑሮ ውድነቱን ችግር በብቃትና በዘላቂነት ሊፈታው እንደማይችል ተገንዝቦ መንግስት ችግሩን በዘላቂነት የሚፈታ የመፍትሄ እርምጃ እንዲወስድ አስፈላጊውን ሰላማዊና ህጋዊ ግፊት ማድረግ ይገባዋል፡፡

 

ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ችግሩን ዘላቂ መፍትሄ ሊያገኝ የሚችለው በፓርቲያችን የተጠቆመው ሰባት የመፍትሄ ሃሳቦች በዝርዝር ጥናትና ዝግጅት ተደግፈው ተግባራዊ ሲደረጉ ነው፡፡ ይህ መሰረታዊ መፍትሄ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ መንግስት በንግዱ ህብረተሰብ ዙሪያ የሚታዩትን ችግሮች ለመፍታት የሚያደርገው ጥረትም አሁን በተግባር ላይ ከዋለው አማራጭ ይልቅ ክቡር ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የዋጋ ተመኑን አዋጅ ይፋ ባደረጉበት ወቅት በሁለተኛ አማራጭነት የጠቆሙትን አማራጭ ታሳቢ ያደረገ ቢሆን የተሻለ ይሆናል ብሎ ፓርቲያችን ያምናል፡፡ ይኸውም በተለያዩ ምርቶችና ሸቀጦች ላይ በገቢያው ውስጥ የተፈጠረው የአቅርቦት አጥረት እስኪወገድ ድረስ መንግስት በራሱ የልማት ድርጅት አማካኝነት እጥረት የታየባቸውን ሸቀጦችና ምርቶች ከውጭ ወደ አገር ውስጥ እያስገባ ህዝቡ በአቋቋማቸው (ወደፊትም ሊቋቋሙ በሚችሉ) የሸማቾችና የአገልግሎት የህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት በጊዜያዊነት ለሽያጭ ቢያቀርብ የተሻለ አማራጭ ይሆናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መንግስት በተለያዩ የልማት ድርጅቶች አማካኝነት በአገር ውስጥ እራሱ እያመረተ የሚያከፋፍላቸው ምርቶች ላይ (ስኳርንና ሲሚንቶ የመሳሰሉ) የዋጋ ቅናሽ ማድረግ ያለበት ሲሆን በእነዚህም መንግስት እራሱ በሚያመርታቸው ምርቶች ላይ የችርቻሮ የዋጋ ተመን ተግባራዊ ማድረጉ ተገቢ አሰራር ይሆናል፡፡

የንግዱ ህብረተሰብ ‹‹መንግስት ተፅእኖ እያደረገብኝ ነው›› እያለ ከማማረር ይልቅ ህጋዊ በሆነ መንገድ በገቢያ ስርዓት እየተወዳደረ ነግዶ ለመኖር ያለውን ቁርጠኛነት በተግባር ማሳየት አለበት፡፡ ነጋዴው ህብረተሰብ በሰሞኑ የዋጋ ተመን ምክንያት በኑሮዬ ኪሳራ ሊደርስብኝ ነው ብሎ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደገባው ሁሉ ሸማቹ የኢትዮጵያ ህዝብ ለብዙ አመታት ምን ያህል በኑሮ ውድነት ሲሰቃይ እንደኖረ መገንዘብ አለበት፡፡ ያለ ሸማቹ ህዝብ ደህንነት እየነገዱ መኖርም ሆነ መክበር እንደማይቻል በመረዳት ከህዝቡ ጋር ተሳስቦ ለመኖር መወሰን አለበት፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter