ግልጽ ደብዳቤ ለጀርመን ድምፅ ራድዮ የአማርኛው ፕሮግራም

ጉዳዩ፡- ማስተባበያ መስጠትን ይመለከታል

ጥር 5 ቀን 2003 ዓ.ም በሬድዮ ጣቢያችሁ በተላለፈው ፕሮግራም በቅርቡ በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የአካባቢ ምርጫ አስመልክቶ አቶ ታደሰ እንግዳ የተባሉት አዲስ አበባ የሚገኙ ዘጋቢያችሁ ዘገባ እንዳስተላለፉ ይታወሳል፡፡ አቶ ታደሰ እንግዳ በዚያ ፕሮግራም ባስተላለፉት ዘገባ በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ፓርቲዎች አመራሮችን በአካልና በስልክ አግኝተው በማነጋገር ጉዳዩን በሚመለከት ያላቸውን አቋም ከገለጹ በኋላ ወደ ኢዴፓ ቢሮ ሁለት ጊዜ ተመላልሰው ቢሮው ዝግ በመሆኑ የኢዴፓን አቋም ማወቅ እንዳልቻሉ ገልፀዋል፡፡ ፓርቲው ይህ የአቶ ታደሰ እንገዳ ዘገባ እውነት ስለመሆኑ ለማረጋገጥ ባደረገው ማጣራት በዚህ ሳምንት ውስጥ ኢዴፓ በአዲስ አበባ ያሉት ሁለት ቢሮዎች በስራ ሰዓት ሙሉ በሙሉ ክፍት እንደነበሩ በማወቁ ዘገባው ሃሰት መሆኑን አረጋግጧል፡፡ አቶ ታደሰ እንግዳ ያስተላለፉት ይህ የሀሰት ዘገባ ከአንድ ጋዜጠኛ ነኝ ብሎ ከሚያምንና የጀርመን ድምፅ ሬዲዮ ወኪል ከሆነ ሰው የማይጠበቅ ተግባር መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡ አቶ ታደሰ በጉዳዩ ላይ የኢዴፓን አቋም ማወቅና መዘገብ ቢፈልጉ ኖሮ ወደ ፓርቲው ቢሮ መሄድ እንኳን ሳያስፈልጋቸው አመራር አባላቱን በቀላሉ በስልክ ማነጋገር በቻሉ ነበር፡፡ ግለሰቡ ሌላ ምክንያት ባይኖራቸው ኖሮ ጀርመን አገር የሚገኙ የጣቢያችሁ ጋዜጠኞችም ሆኑ አዲስ አበባ የሚገኙት ሌላው ወኪላችሁ ጋዜጠኛ ጌታቸው ተድላ በየጊዜው እያገኙ የሚያነጋግሯቸውን የኢዴፓ አመራሮች እርሳቸው ማግኘት ባልተሳናቸው ነበር፡፡

ግለሰቡ ላለፉት 5 ዓመታት ከተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በርካታ ቃለ መጠይቆችን ሲያደርጉና የተለያዩ ፕሮግራሞችን ሲሰሩ አንድም ቀን ስለ ኢዴፓ ፕሮግራም ሰርተው እንደማያውቁ፤ ኢዴፓ በተለያየ ጊዜ በሰጣቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ አቶ ታደሰ እንዲገኙ በስልክ ቁጥራቸው 0911 65 44 43 እየተደወለ የተነገራቸው ቢሆንም አንድም ቀን ተገኝተው እንደማያውቁ፣ ምርጫ 97ን ተከትሎ በአገራችን በተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስም ኢዴፓን የሚያጣጥሉ ፕሮግራሞችን ከግል የፖለቲካ ስሜታቸው በመነሳት በተደጋጋሚ በሬዲዮ ጣቢያችሁ ሲያስተላልፉ እንደነበር በአግባቡ ተገንዝባችሁ ከአሁን በኋላ ኢዴፓን በሚመለከት ግለሰቡ የሚሰሯቸውን ዘገባዎች በጥንቃቄ እንድትመረምሩ ኢዴፓ ያሳስባል፡፡ ይህ ማስተባባያችንም  የሃሰት ዘገባ እንዲያዳምጥ ለተደረገው ህዝብ በራዲዮ ጣቢያችሁ እንዲተላለፍ እንጠይቃለን፡፡

ከሰላምታ ጋር
ሙሼ ሰሙ
ዋና ጻሃፊ

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter