ሕገ-መንግስትና ሕገ-መንግስታዊ ጉዳዮች

በኢዴፓ 5ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ቀርበው በሚፀድቁ የውይይት ርዕስ ጉዳዮች ዙሪያ የተደረገ ቅድመ-ውይይት

የኢዴፓ 5ኛ ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ተወያይቶ አቋም በሚወስድባቸው ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የፓርቲው አባላት የሚያደርጉት ቀዳሚ ውይይት ለ2ኛ ጊዜ ተካሂዷል፡፡ በውይይቱ ላይ የቀረበው ርዕሰ ጉዳይ ሕገ-መንግስትና ሕገ-መንግስታዊ ጉዳዮች በኢትዮጵያ የሚል ሲሆን የአገሪቱን ሕገ-መንግስት አጠቃላይ ይዘት በተመለከተ ኢዴፓ ሊይዘው ስለሚገባ አጠቃላይ አቋም የሚከተለው መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ዋና ዋና የሚባሉትና የተመረጡ ሰባት ሕገ-መንግስታዊ ጉዳዮች ላይ ደግሞ በሚቀጥለው ሳምንት ቀጣይ ውይይት ለማድረግ ተወስኖል፡፡
የፓርቲው አባላት የወቅቱን የአገሪቱ ሕገ-መንግስት በተመለከተ ባደረጉት ውይይት ሕገ-መንግስቱ በተረቀቀበትና በፀደቀበት ወቅት ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ የራሱን ድርጅታዊ የፖለቲካ አቋም ያለአግባብ በሕገ-መንግስቱ እንዲካተት እንዳደረገ፤ ሕገ-መንግስቱ በማርቀቁና በማፅደቁ ሂደትም ሌሎች የተለየ አመለካከት ያላቸው የፖለቲካ ኃይሎች በቂ ተሳትፎ እንዲኖራቸው እንዳልተደረገ፤ እነዚህን ምክንያቶች ሰበብ በማድረግም አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ህገ-መንግስቱን ሙሉ ለሙሉ እውቅና ወደ መንፈግ አክራሪ አቋም እንደገቡና በእነዚህ መሰረታዊ ምክንያቶችም የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች በአገሪቱ የወቅቱ ሕገ-መንግስት ዙሪያ ብሄራዊ መግባባት መፍጠር እንዳልቻሉ አምኖበታል፡፡ በአንድ በኩል ገዢው ፓርቲ ከወቅቱ የአገሪቱ ሕገ-መንግስት መንፈስ በሚቃረን ሁኔታ ሕገ-መንግስቱን ምንም አይነት ጥያቄ ሊነሳበት የማይገባ ኃይማኖታዊ (መንፈሳዊ) ሰነድ አድርጐ በማየት ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ሕገ-መንግስቱን ያለምንም ቅሬታና ጥያቄ እንዲቀበሉትና እንዲያምኑበት የሚፈልግ መሆኑ፤ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለሕገ-መንግስቱ ተገቢውን እውቅና ባለመስጠት በሂደት በህዝብ ውሳኔ እንዲሻሻል ሳይሆን እንደ አንድ ተራ ሰነድ ተቀዶ እንዲጣል የሚጠይቅ አክራሪ አቋም የሚያራምዱ መሆናቸው በሕገ-መንግስቱ ዙሪያ ብሔራዊ መግባባት እንዳይፈጠር እንቅፋት መሆኑ ታምኖል፡፡

የኢዴፓ አባላት ርዕሰ-ጉዳዩን አስመልክቶ ባደረጉት ውይይት የወቅቱን ሕገ-መንግስት በተመለከተ ገዥው ፓርቲም ሆነ አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያራምዱት አቋም መሰረታዊ ችግር እንዳለበት አምነውበታል፡፡ የማንኛውም አገር ሕገ-መንግስት በአንድ ወቅታዊ ሁኔታ ፀድቆ በሂደት ከህብረተሰቡ የእድገት ደረጃና የፖለቲካ ሁኔታ አንፃር እየተሻሻለ የሚሄድ ሰነድ መሆኑ እየታወቀና ማንኛውም ሕገ-መንግስት እንዴት ሊሻሻል እንደሚችል እራሱን የቻለ የማሻሻያ አንቀፅ አካቶ የሚቀረፀውም በዚሁ ምክንያት መሆኑ እየታወቀ ኢህአዴግ ሁልጊዜ ሕገ-መንግስቱ ምንም አይነት ትችትና ተቃውሞ ሊነሳበት የማይችል ዘላለማዊ ሰነድ እንደሆነ አድርጐ በማሰብ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ የሚያቀርበው ትችት የተሳሳተ መሆኑ ታምኖበታል፡፡ በውይይቱ ወቅት በአለማችን በዴሞክራሲያዊ ይዘቱ እንደ አንድ በጐ ምሳሌ የሚጠቀሰው የአሜሪካን ሕገ-መንግስት በምን አይነት ሂደት ውስጥ አልፎ ከዛሬ እንደደረሰ ለማየት ተሞክሮል፡፡የአሜሪካ ሕገ-መንግስት በውስጡ ከአገሪቱ የእድገት ደረጃ ጋር አብረው የማይሄዱ ድንጋጌዎች ያሉት መሆኑ እየታወቀ ሲመጣ ለ27 ጊዜ እንዲሻሻል የተደረገ መሆኑን በማስታወስ ኢህአዴግ የሕገ-መንግስት ማሻሻያ የሚጠይቁ ፓርቲዎችን እንደ ፀረ-ዴሞክራሲና ሕገ-ወጥ አካል መቁጠሩ ስህተት መሆኑ ታምኖበታል፡፡ ከዚህ በመነሳትም ኢህአዴግ እንደ ገዥ ፓርቲነቱ የአገሪቱ ሕገ-መንግስት እንዲከበርና የበላይ ሕግ ሆኖ አገሪቶን እንዲያስተዳድር እንጅ ምንም አይነት ተቃውሞ እንዳይገጥመው መጠበቁ የተሳሳተና ከራሱ ከሕገ-መንግስቱ መንፈስ የሚቃረን አመለካከት መሆኑ ተሰምሮበታል፡፡ የኢትዮጵያ የወቅቱ ሕገ-መንግስት ዜጎች ወይም የፖለቲካ ድርጅቶች በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ማንኛውንም ጉዳይ የመቃወም መብት ያላቸው መሆኑን እውቅና የሰጠ ስለሆነ እራሱን ሕገ-መንግስቱን መቃወምም ከራሱ ከሕገ-መንግስቱ የሚመነጭ መብት መሆኑን ኢህአዴግ አምኖ መቀበል እንዳለበት ታምኖበታል፡፡

ውይይቱ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያራምዱትን አቋም ለመገምገም ባደረገው ሙከራም በአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሕግ እውቅና አግኝተው መንቀሳቀስ የቻሉትና ወደፊትም ሕጋዊ ዋስትና ሊኖራቸው የሚችለው በስራ ላይ የሚገኘው ሕገ-መንግስት እውቅና የሰጣቸው ፖለቲካዊና ሰብአዊ መብቶች ሲከበሩ ስለሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሕገ-መንግቱን የማክበርና በሕገ-መንግስቱ የመገዛት ግዴታ ያለባቸው መሆኑ ታምኖበታል፡፡ በአንድ አገር አንድ ሕግ መከበር ያለበት ሕጉ “ጥሩ” ወይም “ትክክለኛ” ነው ተብሎ ስለታመነ ብቻ ሳይሆን ሕጉ የአገሪቱ ሕግ ሆኖ በስራ ላይ እስካለ ድረስ በማንኛውም ዜጋም ሆነ የፖለቲካ ኃይል መከበርስላለበት መሆኑን አፅንኦት ሰጥቶ ተወያይቶበታል:: አንድ ሕግ የፀደቀበትን ትክክለኛ ያልሆነ ሂደትም ሆነ በውስጡ የሚገኙ መሻሻል ይገባቸዋል ተብለው የሚታመኑ አንቀፆችን ምክንያት በማድረግ ሕጉን አለማክበርና በሕጉ አለመገዛት ስለማይቻል አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዚህ እረገድ የሚያራምዱት አቋም መስተካከል እንዳለበትና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሕገ-መንግስቱን ማክበር ብቻም ሳይሆን የማስከበር ኃላፊነትም ያለባቸው መሆኑን አምነውመቀበል እንዳለባቸው ታምኖበታል፡፡

አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለወቅቱ የአገሪቱ ሕገ-መንግስት ተገቢ እውቅና ባለመስጠት የሚያራምዱት አክራሪ አቋምም ገዥው ፓርቲ እራሱን እንደ ሕግ አስከባሪ፣ ተቃዋሚዎችን ደግሞ እንደ ሕገ-ወጥ ኃይሎች አድርጐ በማቅረብ ያልተገባ የፕሮፓጋንዳ ጥቅም እንዲያገኝ እንደረዳው ታምኖበታል፡፡ ስለሆነም ኢዴፓ በአንድ በኩል በወቅቱ የአገሪቱ ሕገ-መንግስት ውስጥ የሚገኙ ለአገሪቱ አንድነትና የኢኮኖሚ እድገት እንቅፋት የሆኑ አንቀፆች እራሱ ሕገ-መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት በሕዝብ ውሳኔ እንዲሻሻሉ የሚያደርገው ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤ በተመሳሳይ ሁኔታም የወቅቱን ሕገ-መንግስት በአግባቡ አክብሮና በሕገ-መንግስቱ ተገዥ ሆኖ መታገል እንዳለበት ታምኖበታል፡፡ ኢዴፓ ሕገ-መንግስቱን ማክበርና በሕገ-መንግስቱ መገዛት ብቻም ሳይሆን ሌሎች የአገሪቱ ዜጎችም ሆኑ የፖለቲካ ኃይሎች ሕገ-መንግስቱን በተመሳሳይ ሁኔታ የማክበርና በሕገ-መንግስቱ የመገዛት ኃላፊነትና ግዴታ ያለባቸው መሆኑን ግልፅ አቋም ወስዶ ማስተማር እንዳለበት ታምኖበታል፡፡

የአገሪቱ ሕገ-መንግስት አፈፃፀምን በተመለከተ በተደረገው ግምገማም በአንድ በኩል በተለያዩ ጊዜያት ገዥው ፓርቲ የሚያወጣቸው አዋጆችና መመሪያዎች ከሕገ-መንግስቱ መንፈስ በሚቃረን ሁኔታ የሕግ-አውጪውንና የሕግ-ተርጎሚውን ኃላፊነትና ስልጣን ለአስፈፃሚው አካል የሚሰጡ በመሆናቸው፤ በሕገ-መንግስቱ እውቅና ያገኙ የዜጎች ሰብአዊና ፖለቲካዊ መብቶችም በአስፈፃሚው አካል በየእለቱ በሰፊው የሚጣስበት ሁኔታ በአገራችን እየታየ በመሆኑ አገሪቶ ሕገ-መንግስት ያላት አገር ብትሆንም ሕገ-መንግስታዊነት የሰፈነበት አገር ለመሆን ግን ገና እንዳልቻለች ታምኖበታል፡፡ ኢህአዴግም ሕገ-መንግስቱን ሌሎች እንዲያከብሩትና እንዲገዙበት ሁልጊዜ ሲወተውት የሚደመጥ ቢሆንም ከማንም በላይ እራሱ ሕገ-መንግስቱን አክብሮ መገኘት እንደተሳነው ታምኖበታል፡፡

ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር በተያያዘ በ2002 ምርጫ ሕዝቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሳይመርጥ የቀረው ተቃዋሚዎች ሕገ-መንግስቱን ስላልተቀበሉ ነው በማለት ኢህአዴግ የሚያቀርበው ትችት ስህተት መሆኑ ታምኖበታል፡፡ የ2002 ምርጫ የተካሄደው በአጠቃላይ ፓርቲዎች በአገራዊ ጉዳዮች ያላቸውን አማራጭ በማቅረብ እንጂ ሕገ-መንግስቱ በተለያ ሁኔታ ለሕዝቡ በሪፈረንደም መልክ ያልቀረበ መሆኑን በማስታዎስ፣ ከምርጫዉ በኋላም ህዝቡ ለምን ተቃዋሚዎችን እንዳልመረጠ የተደረገ ጥናት አለመኖሩን በመገንዘብ፣ ተቃዋሚዎች ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ ካገኙበት ከ1997 ዓ.ምቱ ምርጫ በኋላም ሕገ-መንግስቱን በሚመለከት የተለየ የወሰዱት አዲስ አቋም እንደሌለና ሕዝቡም ሕገ-መንግስቱን በሚመለከት የተለየ አቋም እንዲይዝ ያስገደደው የተለየ የፖለቲካ ሁኔታ በአገሪቱ ያልተፈጠረ መሆኑን በማመን ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን ሕዝቡ ያልመረጣቸው ሕገ-መንግስቱን ስላልተቀበሉ ነው በማለት የደረሰበት ግምገማ ስህተትና ከእውነታው ጋር የማይዛመድ መሆኑ ታምኖበታል፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter