የኑሮ ውድነቱ አሁንም ተጨማሪ መፍትሄ ይፈልጋል!

ከኢዴፓ የተሰጠ መግለጫ

ሰሞኑን መንግስት ለጡረተኞችና ለመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ማድረጉን ይፋ አድርጓል፡፡ መንግስት ያደረገው ይህ የደሞዝ ጭማሪ በአገሪቱ ከተከሰተው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ጋር የማይመጣጠንና ዘግይቶ የመጣ ቢሆንም በመንግስት ሰራተኞችና በጡረተኞች ላይ የተጫነውን የኑሮ ውድነት ለማቃለል እንደ አንድ በጐ እርምጃ ሊታይ የሚገባው ነው፡፡

ኢዴፓ ለአለፉት አራት ዓመታት ለመንግስት ሰራተኞችና ለጡረተኞች የደሞዝ ጭማሪ እንዲደረግ መንግስትን በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ቆይቷል፡፡ በ2002 የምርጫ ዘመቻ ወቅትም ኢዴፓ የደመወዝ ጭማሬን ጉዳይ በምርጫ ማንፌስቶው በማካተት ጥያቄው ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡መንግስት ለአለፉት አራት ዓመታት የደሞዝ ጭማሪ የገንዘብ ግሽበቱን ያባብሳል በማለት የኢዴፓን ጥያቄ ሲነቅፍና ሲያጣጥል የነበረ ቢሆንም አሁን ዘግይቶም ቢሆን እርምጃ መውሰድ ጀምሮአል፡፡

ኢዴፓ ይህንን ጅምር የሚያደንቅ ቢሆንም በአገራችን የተከሰተውን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ችግር ለማስወገድ መንግስት በአሁኑ ወቅት እየወሰዳቸው የሚገኙ እርምጃዎች ከተዛማጅነት፣ ከፍጥነትም ሆነ ከመጠን አኳያ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በቂ አይደሉም፡፡ ኢዴፓ ባለፈው ሳምንት በሰጠው መግለጫ በግልፅ እንዳስቀመጠው ከሸቀጦች ዋጋ ተመን ጋር በተያያዘ መንግስት በአሁኑ ወቅት እየወሰደ የሚገኘው እርምጃ በቂ ጥናትና ዝግጅት ያልተደረገበት ከመሆኑም በላይ የአገሪቱን የንግድ ሰላም በማናጋት ችግሩን የማቃለል ሳይሆን የበለጠ የማባባስ ስጋት ፈጥሮል፡፡ በተለይም በአንዳንድ ክልሎች ቀይና አልጫ ወጥን በመሳሰሉ የበሰሉ የምግብ ዓይነቶች ጭምር ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የዋጋ ተመን የአገሪቱን የነፃ-ገበያ ኢኮኖሚ አራማጅነት ትርጉም የለሽ አድርጐታል፡፡

የመንግስት ሰራተኞችንና የጡረተኞችን ደሞዝ የመጨመሩ እርምጃ የሚያስመሰግን ቢሆንም ከወቅቱ ኑሮ ውድነት ጋር ሲመዛዘን የመንግስት ሰራተኞችም ሆነ የጡረተኞች መነሻ ደሞዝ ከ500 ብር ያነሰ መሆኑ ተገቢ አይደለም ብሎ ኢዴፓ ያምናል፡፡ ኢዴፓ የራሱን ጥናት አካሂዶ በምርጫ ማንፌስቶው ላይ በግልፅ እንዳሰፈረው በአሁኑ ወቅት አንድ እራሱን ችሎ የሚኖር ሰው ከ1200 ብር ባነሰ ገቢ የወር ወጪውን ሊሸፍን አይችልም፡፡ ከአገሪቱ ድህነት አንፃር ለጊዜው ይህን ያህል የመነሻ ደሞዝ መክፈል አስቸጋሪ ቢሆንም የአንድ ሰራተኛ መነሻ የወር ደሞዝ ቢያንስ 500 ብር ሊሆን ይገባዋል ብሎ ኢዴፓ ያምናል፡፡ በአገራችን ተቀጣሪ ሰራተኞች የሚገኙት በመንግስት መስሪያቤቶች ብቻ ባለመሆኑ መንግስት በግሉ ዘርፍ ተቀጥረው የሚኖሩ ዜጐችም ተገቢ ደሞዝ ጭማሪ የሚያገኙበትን አሰራር ባስቸኳይ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

የኑሮ ውድነቱ ተቀጣሪ ሰራተኞችን ብቻም ሳይሆን በተለያየ የግል ስራ ላይ የተሰማሩና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የከተማ ነዋሪዎችን የሚመለከት በመሆኑም የእነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ችግር የሚያቃልል እርምጃ በአስቸኳይ መወሰድ አለበት፡፡በአጠቃላይ መንግስት በአሁኑ ወቅት ከደሞዝ ጭማሬ እና ከዋጋ ቁጥጥር ጋር በተያያዘ እየወሰዳቸው የሚገኙ እርምጃዎች የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል መወሰድ ከሚገባቸው በርካታ እርምጃዎች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው ዕንጂ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ በቂ እርምጃዎች አይደሉም፡፡ በአገራችን የተከሰተውን የኑሮ ወድነቱን በተሻለ ሁኔታ ለማቃለል መንግስት ከነዳጅ ዋጋ ድጐማ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ክፍያና ከአቅርቦት እድገት ጋር የተያያዙ ሌሎች እርምጃዎችን መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡

መንግስት የህዝቡን የኑሮ ውድነት ለማቃለል ከልቡ እስካሰበ ድረስም በራሱ የልማት ድርጅቶች አማካኝነት በሚያመርታቸው ስኳርን፣ ሲሚንቶንና ብረት በመሳሰሉ ምርቶች ላይ ትርጉም ያለው ቅናሽ ማድረግ አለበት፡፡ መንግስት ከፍተኛ ትርፍ እያጋበሰ በሚገኝባቸው መብራትን፣ ውሃንና ስልክን በመሳሰሉ የአገልግሎት ዘርፎችም የታሪፍ ቅናሽ የማድረግ ዕርምጃ የመፍትሄው አካል ተደርጐ መታዬት ይገባዋል፡፡ በሸቀጦች ላይ በቂ ጥናትና ዝግጅት ያልተደረገበት የዋጋ ተመን በማድረግ ችግሩን ከማባባስም ይልቅ ከፍተኛ የአቅርቦት ዕጥረትና የዋጋ ንረት የሚታይባቸውን የተመረጡ ሸቀጦች መንግስት በራሱ መንገድ በጊዜያዊነት ከውጭ እያስገባ ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የማዳረስ እርምጃ ቢወስድ የተሻለ መሆኑን ኢዴፓ በድጋሚ ማሳሰብ ይወዳል፡፡ በደሞዝ ጭማሪና በነዳጅ ድጐማ ምክንያት የአገሪቱ የገንዘብ ግሽበት የበለጠ እንዳይባባስም መንግስት በካፒታል በጀቱ ላይ ትርጉም ያለው ጊዜያዊ ቅናሽ በማድረግ በአገሪቱ ጤናማና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት እንዲኖር የሚያስችል እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡ ሰሞኑን በሰሜን አፍሪካ አገሮች የሚታየው ዓይነት የፖለቲካ ቀውስ በአገራችን እንዳይከሰት መንግስት ከህዝቡ የኑሮ ውድነት ጋር ተዛማጅ የሆኑ የመፍትሄ እርምጃዎችን በስፋትና በፍጥነት መውሰድ አለበት ብሎ ኢዴፓ ያምናል፡፡ ሕዝቡ በአገራችን የተከሰተው የኑሮ ውድነት ዘላቂ መፍትሄ ያገኝ ዘንድም በመንግስት ላይ ሰላማዊና ህጋዊ ግፊት እንዲያደርግ ኢዴፓ በዚህ አጋጣሚ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የኢዴፓ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ጥር 19 ቀን 2003 ዓ.ም
አዲስ አበባ

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter