የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች

በኢዴፓ 5ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ቀርበው በሚፀድቁ የውይይት ርዕስ ጉዳዮች ዙሪያ የተደረገ ቅድመ-ውይይት

የኢዴፓ 5ኛ ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ተወያይቶ አቋም በሚወስድባቸው ጉዳዮች ላይ የመወያያ ረቂቅ ለማዘጋጀት የፓርቲው አባላት የሚያካሂዱት ስብሰባ ለአራተኛ ጊዜ ተካሂዷል፡፡በዚህ የኢዴፓ አባላት ውይይት ላይ የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡
ማህበራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ በዋናነት ውይይት የተደረገባቸው ትምህርትና ጤና ሲሆኑ የሴቶች፣ የወጣቶች፣የህፃናትና የአካል ጉዳተኞች ጉዳዮችም ትኩረት የሚያሻቸው ማህበራዊ ጉዳዮች መሆናቸው ታምኖባቸው ውይይት ተደርጐባቸዋል፡፡
ትምህርትን በተመለከተ በተደረገው ውይይት በአሁኑ ወቅት መንግስት በትምህርት ተደራሽነት ረገድ የሚያስመሰግን ስራ እየሰራ እንደሆነ የታመነበት ሲሆን የትምህርት ጥራትን በተመለከተ የሚታየው ችግር ግን እጅግ ሰፊና አሳሳቢ መሆኑ ታምኖበታል፡፡ አንድን ትውልድ ለአገርና ለወገን በሚጠቅም መልኩ በመቅረፅ እረገድ የትምህርት ሚና የማይተካና ከሁሉም በላይ በመሆኑ በዋናነት ከካሪኩለም ቀረፃ፣ ከትምህርት መርጃ መሳሪያ አቅርቦትና ከመምህራን ብቃትና ብዛት ጋር የተያያዙ ችግሮችን በመፍታት የትምህርት ጥራትን በከፍተኛ መጠንና ፍጥነት ማሻሻል እንደሚገባ ታምኖበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ገዢው ፓርቲ መምህራንንና ተማሪዎችን የራሱ የፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ በማሰብ በትምህርት ተቋማት ላይ የሚፈፅመው መጠነ ሰፊ ድርጅታዊ ጣልቃ ገብነት ለትምህርት ጥራት መጓደል አንድ አሳሳቢ ችግር በመሆኑ ሊወገድ እንደሚገባው ታምኖበታል፡፡

ጤናን በተመለከተ በተደረገው ውይይት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የጤና ተቋማትን በማዳረስ፣ ኤች አይ ቪ ኤድስንና ወባን በመከላከል ረገድ መንግስት አበረታች ተግባር እያከናወነ መሆኑ የታመነበት ሲሆን ከጥራት አኳያ ግን ከጤና መርጃ መሳሪያዎች፣ ከመድሃኒትና ከጤና ባለሙያዎች እጥረት ጋር በተያያዘ በጤናውም ዙሪያ ከፍተኛ ድክመት እንደሚታይ ታምኖበታል፡፡ በከተሞች አካባቢ የጤና ጉዳይ በቂ ትኩረት ያላገኘ ከመሆኑም በላይ በከተሞች አካባቢ እየተስፋፉ የሚገኙት የግል የጤና ተቋማት ብቻ በመሆናቸው ከህዝቡ አቅም ጋር በማይመጣጠን ደረጃ የህክምና ዋጋ ውድ መሆኑ ታምታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በጤናው ሴክተር ዙሪያ የሚታየው የጤና ባለሙያዎች የስነምግባር ጉድለት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ በመሆኑን እና አስቸኳይ መፍትሄም እንደሚያስፈልገው ታምኖበታል፡፡

ከትምህርትና ከጤና ጉዳይ በተጨማሪ በሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በተደረገው ውይይት የህብረተሰቡ ግማሽ አካል ለሆኑት ሴቶች የሚሰጠው ትኩረት ከፕሮፓጋንዳና ከድርጅታዊ የፖለቲካ ጥቅም በፀዳ አኳኋን ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት፤ የእናቶችና የህፃናት ሞትን ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው፤ በብዙ ሚሊዎን የሚቆጠሩ የአገራችን አካል ጉዳተኞች በዙሪያቸው የሚታዩ ፈርጀ ብዙ ችግሮች እንዲፈቱ የሚያስችል ጥረት መደረግ እንዳለበት፤ የአገሪቱ ተረካቢ የሆኑትን ወጣቶች በተመለከተ ቁሳዊና መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን በማሟላት ረገድ ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ የሆነ ጥረትና እርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ታምኖበታል፡፡

ኢከኖሚያዊ  ጉዳየችን በተመለከተ በተደረገው ውይይት በዋናነት ትኩረት የተደረገባቸው በአገሪቱ የነፃ-ገበያ ኢኮኖሚ ውስጥ የመንግስት ሚና ምን ሊሆን ይገባል?፤ አገሪቱ ልትከተለው የሚገባው የኢኮኖሚ ስትራቴጂስ ምን ዓይነት ሊሆን ይገባል? የሚሉት ጥያቄዎች ሲሆኑ የመንግስት የልማት ድርጅቶች፣ ከፖለቲካ ፓርቲ ጋር ግንኙነት ያላቸው የንግድ ድርጅቶችና የወቅቱ የኑሮ ውድነት ጉዳይም ውይይት ተደርጐባቸዋል፡፡ በውይይት ወቅት በአንድ በኩል ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የመንግስት ሚና የበለጠ እንዲጠናከር እየሰራ ከመሆኑና የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ ገና በጥርጣሬና በስጋት የሚያይ ከመሆኑ አንፃር፣ በሌላ በኩል ደግሞ በአሁኑ ወቅት ገበያ በማረጋጋት ሰበብ በበርካታ የፍጆታ ምርቶችና ሸቀጦች ላይ እየጣለ ከሚገኘው የዋጋ ተመን አንፃር በአሁኑ ወቅት በአገራችን የዕዝ ወይም የቅይጥ ኢኮኖሚ እንጅ የነፃ-ገበያ ኢኮኖሚ አለ ሊባል እንደማይችል ታምኖበታል፡፡

በነፃ-ገበያ ስርዓት የመንግስት ዋና ተግባር ህግ የማውጣትና የገበያ ስርአቱ በአግባቡ እየተካሄደ ስለመሆኑ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ሲሆን መንግስት በህግ በተገደበ አግባብና በጊዜያዊነት በገበያ ውስጥ ተሳትፎ ሊኖረው የሚችለውም የህብረተሰቡን ጥቅም የሚጐዳ ወቅታዊ ችግር ሲፈጠርና በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ሊሸፈኑ ያልቻሉ ክፍተቶች ሲፈጠሩ ብቻ እንደሆነ ታምኖበታል፡፡ ከዚህ አንፃር መንግስት በአሁኑ ወቅት በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ሊሸፈኑ የሚችሉ አንዳንድ የንግድ ተቋማትን በልማት ድርጅት ስም ይዞ መቀጠሉ ተገቢ አለመሆኑ የታመነበት ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ማንኞውም የፖለቲካ ፓርቲ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በንግድ ስራ ውስጥ ሊሰማራ እንደማይችል ከሚከለክለው የአገሪቱ ህግ በተፃፃሪ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ኢህአዴግ የበርካታ የንግድ ድርጅቶች ባለቤት ሆኖ መቀጠሉ ከነፃ-ገበያ ስርአት ጋር የሚጋጭ ስህተት ብቻም ሳይሆን በአገሪቱ ህግ መሰረት ወንጀል መሆኑ ታምኖበታል፡፡

ከኢኮኖሚ ስትራቴጂ አንፃር ኢህአዴግ የሚከተለው ግብርና መር ወይም ገጠርንና አርሶ አደርን መአከል ያደረገው ስትራቴጂ በአገራችን እንዳልሰራ የኢህአዴግ የመጀመሪያዎቹ 13 የአገዛዝ ዓመታት በበቂ ሁኔታ እንዳረጋገጡ ታምኖበታል፡፡ ለአለፉት 6 ዓመታት የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት በአገራችን መታየት የቻለው ኢህአዴግ በአዋጅና በግልፅም ባይሆን ለአለፉት ስድስት ዓመታት ለኢንዱስትሪና ለአገልግሎት ዘርፉ፣ በተለይም ለኮንስትራክሽን ዘርፍ በተወሰነ ደረጃ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀሱ መሆኑ ታምኖበታል፡፡ ኢህአዴግ የተቃዋሚዎችን አማራጭ ሃሳብ ተቀብዬ ተለውጫለው ማለት አሳፍሮት የቀድሞ አቋሙን ከሙሉ ልብ ለመለወጥ ባለመቻሉ እንጂ በአገሪቱ የግብርና፣ የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፍ መሪና ተመሪ ሆነው ሳይሆን ሁሉም ዘርፎች ተገቢ ትኩረት አግኝተው እርስ በእርስ ተደጋግፈውና ተመጋግበው እንዲያድጉ የሚያስችል የኢኮኖሚ ስትራቴጂ በሙሉ ልብ ተግባራዊ ቢደረግ በአገራችን የበለጠ ፈጣንና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ሊመጣ እንደሚችል ታምኖበታል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገራችን የተከሰተውን የኑሮ ውድነትና የገንዘብ ግሽበት በዘላቂነት ለመፍታትም በነጋዴዎች ላይ የሚደረግ የአሰራር ቁጥጥርን፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ቅነሳን፣ ጊዜያዊ የነዳጅ ዋጋ ድጐማን፣ ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የደሞዝ ጭማሪን፣ የካፒታል በጀት ጊዜያዊ ቅነሳንና ከሁሉም በላይ የአቅርቦት መጠንን ማሳደግን ያካተቱ እርምጃዎች በበቂ ጥናትና ዝግጅት ተደግፈው ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል፡፡ በውይይቱ ሂደት በአሁኑ ወቅት በአገራችን ከኑሮ ውድነትና ከዋጋ ግሽበት ጋር በተያያዘ እየታየ ያለው የኢኮኖሚ ቀውስ የነፃ-ገበያ የኢኮኖሚ ስርዓት የፈጠረው ችግር ሳይሆን ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የነፃ-ገበያ ስርዓትን በአግባቡ ለማካሄድ ካለመቻሉ ጋር በተያያዘ የተፈጠረ ቀውስ መሆኑን አስምሮበት አልፏል፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter