ምርጫ 2002 እና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች የኃይል አሰላለፍ

በኢዴፓ 5ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ቀርበው በሚፀድቁ የውይይት ርዕስ ጉዳዮች ዙሪያ የተደረገ ቅድመ-ውይይት

የኢዴፓ 5ኛ ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ተወያይቶ አቋም በሚወስድባቸው ጉዳዮች ላይ የመወያያ ረቂቅ ለማዘጋጀት የፓርቲው አባላት የሚያካሂዱት ስብሰባ ለአምስተኛ ጊዜ ተካሂዷል፡፡በዚህም መሰረት የኢዴፓ አባላት ምርጫ 2002 እና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች የኃይል አሰላለፍ በሚለው ዕርስ ጉዳይ ላይ ውይይት ተካሂዶዋል፡፡
በዕርሰ ጉዳዩ ላይ በተደረገው ውይይት በ2002 ምርጫ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለምን ሙሉ ለሙሉ በሚባል መጠን ተሸናፊ ሆኑ? የ2002 ምርጫ የአገሪቱን የመድብለ ፓርቲ ስርአት ከማጠናከር ይልቅ ለምን ወደኋላ የቀለበሰ ሆኖ ተጠናቀቀ? በአጠቃላይስ የ2002 ምርጫ በአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ምን ዓይነት የኃይል አሰላለፍ ለውጥ አመጣ? ለሚሉት ጥያቄዎች ውይይቱ መልስ ሰጥቶ ለማለከፍ ሞክሮል፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሽንፈት በተመለከተ የተለያዩ ነጥቦች በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡ ከተጠቀሱት ምክንያቶች ውስጥ በዋናነት ጎልቶ የወጣው ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫ 97 ማግስት የፈፀሙት ከፍተኛ ስህተት ነው፡፡ምርጫ 97ን ተከትሎ በአገራችን በተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ ተቃዋሚዎች በምርጫ ያገኙትን ውጤት በአግባቡ ይዘውና ተጠቅመው ትግሉን አጠናክረው ከመቀጠል ይልቅ ፓርላማ ላለመግባትና አዲስ አበባ መስተዳደርን ላለመረከብ የወሰዱት የተሳሳተ አቋም እራሳቸውን በማዳከምና በህዝብ ዘንድ እምነት እንዲያጡ በማድረግ ለ2002 ምርጫ ሽንፈት እንደዳረጋቸው ታምኖበታል፡፡

ለተቃዋሚዎች ሽንፈት ዋናው ምክንያት ይህ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ለአለፉት አምስት ዓመታት ገዢው ፓርቲ የፈፀማቸው ሁለት ተግባራት ተጨማሪ ምክንያት መሆናቸው ተገልፆል፡፡ገዢው ፓርቲ በ97 ዓ.ምቱ ምርጫ የደረሰበት ዓይነት ያልተገመተ ሽንፈት ዳግም እንዳይከሰት በመስጋት እራሱን እንደ አዲስ አጠናክሮ በመውጣት በአንድ በኩል ከአለፉት አመታት የተሻለ የልማት ስራ በመስራት የተሻለ የህዝብ ድጋፍ ለማግኘት መቻሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በህዝቡ ላይ የተለያዩ ተፅኖዎችንና ጫናዎችን ለመፍጠር የሚያስችል ድርጅታዊ አቅም በመፍጠር የ2002 ምርጫን ለማሸነፍ መቻሉ ታምኖበታል፡፡ ገዢው ፓርቲ ከመጠን ባለፈ ስጋት ውስጥ ሆኖ በምርጫው ወቅት በህዝቡ ላይ በፈፀመው ከገደብ ያለፈ ጫና  ምክንያት ምርጫውን አሣማኝ በሆነ የድምፅ ልዩነት ከማሸነፍ አልፎ የአገሪቶን የዲሞክራሲ ሂደትም ሆነ የብዙሃን ፓርቲ ስርዓት ትርጉም በሚያሳጣ መጠን ምርጫውን 99.6% ሊያሸንፍ እንደቻለ ታምኖበታል፡፡

ምርጫ 2002 ከዚያ በፊት ከነበረው ሁኔታ በተሻለ ገዢው ፓርቲ እንደ አንድ በምርጫ እንዳሸነፈ መንግስት የተሻለ የህዝብ እውቅና (legitimacy) ያገኘበት ወቅት ቢሆንም ኢህአዴግ በፈፀመው ከገደብ ያለፈ ጫናና ተፅእኖ ምክንያት አጠቃላዩ የምርጫ ውጤት በአገራችን የዴሞክራሲ ሂደቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና እየተጠናከረ ከመሄድ ይልቅ ወደ ኋላ እየተቀለበሰ መምጣቱን፤ አገሪቱም በአንድ አምባገነናዊ ፓርቲ ብቸኛ ቁጥጥር ስር በመውደቅ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን በአግባቡ ለማስተናገድ እንዳልቻለች ያረጋገጠ ሂደት መሆኑ ታምኖበታል፡፡

ከፖለቲካ ድርጅቶች የኃይል አሰላለፍ አንፃር ምርጫ 2002 ኢህአዴግን በአገሪቱ ብቸኛ አምባገነናዊ ኃይል ሆኖ አንዲወጣ ያደረገ ሲሆን በአንፃሩ ተቃዋሚዎችን የበለጠ የተዳከመና ለህዝቡ ለውጥ ተስፋ የማይሰጡ ኃይሎች እንዳደረጋቸው ታምኖበታል፡፡ ህዝቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንደ አንድ አማራጭ ኃይል ያለማየት ተስፋ መቁረጥ ውስጥ በመግባትና ኢህአዴግን እንደ አንድ በውድም ሆነ በግድ አገሪቱን እየገዛ ወደፊት ከመቀጠል የማይመለስ ድርጅት አድርጐ በማዬት በትግሉ ሂደት የመሳተፍ ፍላጐቱ እየቀዘቀዘ መምጣቱ ታምኖበታል፡፡ ይህ ሁኔታ ተለውጦ የትግሉ ሂደት እንደገና እንዲጠናከርም በአንድ በኩል ተቃዋሚዎች በ2002 ምርጫ የደረሰባቸውን ሽንፈት በሃቅና በድፍረት በመገምገም ከድክመቶቻቸውና ከስህተቶቻቸው ተምረው አዲስ ስልትና ስትራቴጂ ቀይሰው መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባቸው፤ ህዝቡም በጊዜያዊ ሁኔታ ተደናግጦ ተስፋ መቁረጥ ዘላቂ መፍትሄ እንደማይሆን በግልፅ ተገንዝቦ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንደገና ተጠናክረው ለመውጣት የሚያስችላቸውን ሁለንተናዊ እገዛ ማድረግ እንዳለበት ታምኖበታል፡፡

ምርጫ 2002 በአገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ሂደትና በአጠቃላይ በተቃዋሚው ጐራ አስከትሎት ያለፈው ጉዳት ከባድ ቢሆንም ከስህተቱ ለመማር ዝግጁ ለሆነ አካል ሂደቱ ከፍተኛ ትምህርት ሊቀሰምበት የሚችል ሂደት እንደነበር ታምኖበታል፡፡ ኢዴፓ ተቃዋሚ ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን በ2002 ምርጫ በተቃዋሚው ጐራ የደረሰውን ጉዳት በቀጥታ የሚጋራ ቢሆንም የምርጫው ሂደት ለኢዴፓ የተለየ ትርጉምና ፋይዳ እንደነበረው ታምኖበታል፡፡ ኢዴፓ ከምርጫ 97 ማግስት ጀምሮ የተካሄደበትን ያሉባልታ ዘመቻ በማክሸፍ በምርጫ ዘመቻው ወቅት ከሌሎች ፓርቲዎች የተሻለ ዝርዝር ማንፌስቶ ያቀረበ፣በምርጫው ወቅት በተካሄዱ የክርክር መድረኮችም የሃሳብ አሸናፊነቱን ያሳዬ፣ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ባካሄዳቸው ህዝባዊ ስብሰባዎችም የማይናቅ የህዝብ ድጋፍ ያለው ፓርቲ መሆኑን ያሣዬና በመጨረሻ በምርጫው በተገኘው የህዝብ ድምፅም በአገሪቱ ከሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ በተናጠል ሲሰላ የተሻለ የህዝብ ድምፅ ያገኘ ፓርቲ መሆኑን ያረጋገጠበት ሂደት መሆኑ ታምኖበታል፡፡ ይህ ሁኔታም ለኢዴፓ የወደፊት ጥንካሬ እንደ አንድ በጐ አጋጣሚና ዕድል የሚቆጠር መሆኑ ታምኖበታል፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter