ኢዴፓ 5ኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን ዛሬ ያደርጋል፤

ከሶሰት ወራት በላይ ዝግጅት ሲደረግበት የነበረው የኢዴፓ 5ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ በታቀደለት ፕሮግራም መሰረት ግዮን ሆቴል አካባቢ በሚገኘው የቀድሞው አደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ  ዛሬ እንደሚደረግ ታውቋል::

የፓርቲው አባላት ለዐያሌ ሳምንታት በተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በመወያየት ያቀረቡትን የውሳኔ መነሻ ሃሳብ እንዳስፈላጊነቱ በማሻሻል እና በማዳበር ያጸድቃል ተብሎ የሚበቀው ይኸው ጉባዔ፤ ላለፉት ሁለት አመታት ፓርቲውን ሲመራ የቆየውን እና የኃላፊነት ጊዜውን ያጠናቀቀውን አመራር በማሰናበት በምትኩ አዲስ አመራር ይሰይማል ተብሎም ይጠበቃል::

ነገ ሰኞ ከቀኑ አሥር ሰአት ተኩል ጀምሮ በራስ ሆቴል በሚደረግ ዝግጅት የድርጅታዊ ጉባኤው ውጤት ለህዝብ ይፋ እንደሚሆን እና አዲሱም አመራር ከህዝብ ጋር እንደሚተዋወቅ ለማወቅ ተችሏል::የውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲን ለማስፈን በሚያደርገው ጥረት የሊቀመንበሩን የሀላፊነት ጊዜ በመወሰን በሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪክ ብቸኛ የሆነው ኢዴፓ፤ በዚህ ዝግጅት ላይ ለሁለት ተከታታይ  የሀላፊነት ጊዜያት(terms) ያገለገሉትን አቶ ልደቱ አያሌውን በደማቅ ሁኔታ ያሰናብታል ተብሎም ይጠበቃል::በዝግጅቱ ላይ የኢዴፓ አባላት፣ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና ጋዜጠኞች ይገኛሉ::

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter