የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ስብሰባ ከ2002ቱ ሃገር አቀፍ ምርጫ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ተካሄደ

መጋቢት 21 ቀን 2003 ዓ.ም የተሰበሰበው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት  አራት አጀንዳዎችን ቀርጾ ለውይይት አቅርቧል፡፡ በዕለቱ የተቀረጹት አጀንዳዎች
1.    ከዚህ ቀደም በተቋቋመው ኮሚቴ አማካኝነት የተረቀቀውንና የጋራ ም/ቤቱ የሚመራበትን ውስጠ ደንብ ተወያይቶ ማፅደቅ፡፡
2.    በምርጫ ህጉ ማዕቀፍ ውሰጥ ሊካተቱ ያልቻሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፋይናንስ የሚያገኙበትን ሁኔታ በተመለከተ ከኢህአዴግ የቀረበው መነሻ ሃሳብ ላይ መወያየት፡፡
3.    ፖለቲካ ፓርቲዎች የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀምና በአጠቃቀም ሂደቱ በተከሰቱ ችግሮች ዙርያ  መወያየትና ወደፊት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቂ የመገናኛ ብዙሃን  ሽፋን የሚያገኙበትን ሁኔታ መፍትሔ ማፈላለግ፡፡
4.    ምርጫ ቦርድ በምርጫ 2002 የነበረውን አሰራርና ሂደት መፈተሽ የሚሉት ነበሩ፡፡
በዚሁ መሰረት ቀደም ብሎ ከጋራ ም/ቤቱ ተውጣጥቶ በተቋቋመው ኮሚቴ ተዘጋጅቶ እንዲያቀርብ በተወሰነው መሰረት በቀረበው የም/ቤቱን የውስጥ መተዳደሪያ ደንብ ላይ ምክር ቤቱ ሰፊ ውይይት አድርጎ በቀጣይነት ስራውን በቀለጠፈ ሁኔታ ለማካሄድ የሚያግዘውን ደንብ አፅድቋል፡፡ በዚሁ ደንብ ላይ ከተካተቱት መካከል በየሁለት ወሩ ቋሚ የስብሰባ ቀን እንዲኖርና የጋራ ም/ቤቱ አባል ፓርቲዎች በየትኛውም ጊዜ አስቸኳይ አጀንዳ ሲያጋጥማቸው አስቸኳይ ስብሰባ መጥራት እንዲችሉ የሚያዙት አንቀጾች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በሁለተኛነት  የቀረበው አጀንዳ  በኢህአዴግ በኩል የተነሳው ሲሆን አጀንዳውም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በ2002 ዓ.ም ባወጣው የፓርቲዎች የፋይናስ ክፍፍል ስርዓት ላይ ፓርቲዎች ለስራ ማስኬጃ የሚሆናቸውን ከመንግስት የሚመደብ በጀት በፓርላማና በክልል ምክር ቤት በሚኖራቸው መቀመጫ ልክ እንዲከፋፈሉ ስለሚደነግግና በ2002 ምርጫ ፓለቲካ ፓርቲዎች በምክር ቤት ወንበር የሌላቸው በመሆኑ ምክንያት ድጋፍ ሊደረግላቸው ስለማይችል ይህንኑ ክፍተት ለመሙላት እንዲያስችል ኢህአዴግ ከተመደበለት የተወሰነ የፋይናንስ በጀት ወደምርጫ ቦርድ ተመላሽ በማድረግ  የምክር ቤቱ አባላት የሆኑ ፓርቲዎች  እንዲከፋፈሉት በመወሰኑ  በቀረበው ረቂቅ የአከፋፈል ስርዓት ላይ  ፓርቲዎቹ ምክክር በማድረግ የቀረበውን ረቂቅ መስፈርት ተቀብለዋል፡፡ የም/ቤቱ  አባላትም በተስማሙበት መስፈርት መሰረት ምርጫ ቦርዱ  ክፍፍሉ እንዲካሄድ ስምምነት ላይ ተደርሶል፡፡ መስፈርቱም

1.    20 በመቶ እኩል ለሁሉም ፓርቲዎች
2.    60 በመቶ በምርጫ 2002 ባቀረቡት እጩ ልክ
3.    20 በመቶ ባቀረቡት ሴት እጩዎች ልክ

በመጨረሻም በሚድያ ጉዳይ ላይ የተያዘውን አጀንዳ ለማስቀጠል መነሻ የሚሆን ረቂቅ የሜድያ መመሪያ ሰነድ ኢዴፓ አዘጋጅቶ ለማቅረብ በጠየቀው መሰረት ም/ቤቱ የተቀበለው ሲሆን ም/ቤቱ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ  በድጋሚ ተገናኝቶ ኢዴፓ በሚቀርበው ሰነድ ላይ ውይይት ለማድረጝ በመስማማት ስብሰባው ተጠናቋል፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter