የፓርቲውን ድርጅታዊ ብቃትና አቅም ለማጠናከርና የአባላትን ቁጥር ለማሳደግ በኢዴፓ ፕሬዚዳንት የሚመራ ቡድን የክፍለ ሀገር ቢሮዎች ጉብኝት ሊያካሄድ ነው፡፡

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በ5ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት እንዲያገለግል አዲስ የተመረጠው አመራር እንዲያከውናቸው ከተወሰኑት መሰረታዊ ተግባራት መካከል አንደኛው  የፓርቲውን ድርጅታዊ ብቃትና አቅም ማጠናከርና የአባላትን  ቁጥር ማሳደግ በወሳኝነት ይጠቀሳል፡፡

ይህንን ተከትሎ ላለፈው አንድ ወር ያህል ሲመክር የነበረው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የ6ቱን ቋሚ ኮሚቴዎችና የአመራሩን  የሁለት ዓመት የስራ እቅድና መርሐ ግብር ላይ ተወያይቶ ያጸደቀ ሲሆን በመርሓ ግብሩም መሰረት የፓርውን ቋሚ ቢሮዎች ማጠናከርና ተጨማሪ ቢሮዎችን የመክፈት እንቀስቃሴ ቅድሚያ እንዲሰጠው በመወሰን፤  በፓርቲው ፕሬዚዳንት የሚመራና የድርጅት ጉዳይና የሕዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችን በቋሚነት ያካተተ ቡድን አቋቋሟል::

የተቋቋመው ቡድን እስከ ሐምሌ መገባዳደጃ ድረስ በሁሉም ቢሮዎች ጉብኝት በማድረግና የተሟላ የስራ ግምገማ በማካሄድ ቢሮዎቹን ለማጠናከርና ሕብረተሰቡን በተጠናከረ አወቃቀር እስከ ወረዳ ደረስ ለማደራጀት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ መነሻ ሃሳብ በማዘጋጀትና የጉብኝቱን ውጤት በሪፖርት መልክ አቀናብሮ ነሐሴ ወር መጀመርያ ላይ ለሚካሄደው የመጀመርያ የማዕከላዊ ምክር ቤት ስብሰባ እንዲያቀርብ ወስኗል፡፡

በውሳኔው መሰራት የራሱን የጉብኝት መርሃ ግብር የቀየሰውና በፓርቲው ፕሬዚዳንት የሚመራው ከስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተውጣጣው ቡድን  ነገ እሁድ ግንቦት 6 ቀን 2003 ዓ.ም አዋሳን ማዕከል በማድረግ አዋሳን፣ ወላይታ ሶዶን፣ ሻሸመኔን፣ አለታ ወንዶንና በነዚህ ከተሞች ዙርያ የተደራጁ ቢሮዎችን የሚጎበኝ ሲሆን በቀጣይ  ግንቦት 20 ቀን 2003 ዓ.ም ባህርዳርን ማዕከል በማድረግ ባህርዳርን፣ ጎንደርን፣ ደብረማርቆስንና በዙርያው በሚገኙ አጎራባች ከተሞች የተደራጁ ቢሮዎችን ይጎበኛል፡፡

በዚህ ጉብኝት ወቅት ጠቅላላ ጉባኤው ያስተላለፋቸው ወሳኔዎች ላይ ውይይት የሚያድርግ ሲሆን በውሳኔዎቹ አፈጻጸም ዙሪያ የጋራ አቋም ላይ በመድረስ ወደ ተግባር የሚገባበት ሁኔታ ያመቻቻል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter