ከአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ኢ. ቦዝ እና በአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ዴፕዩቲ አሲስታንት ከሆኑት ካርል ኢ. ዋይኮፍ ጋር በኢዴፓ ጽ/ቤት የተደረገ ውይይትና የስራ ጉብኝት ሪፖርት

የተከበሩ የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ኢ.ቦዝ እና የተከበሩ በአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ዴፕዩቲ አሲስታንት  የሆኑት ካርል ኢ. ዋይኮፍ ከኢዴፓ ፕሬዚዳንት ከአቶ ሙሼ ሰሙ ጋር በኢዴፓ ጽህፈት ቤት በውቅታዊ ጉዳች ላይ  ውይይት አደረጉ፡፡ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ጽ/ቤት በላከልን ዜና መሰረት ቅደሜ ከሰዓት በኃላ በኢዴፓ ጽ/ቤት በተካሄደውና  አንድ ሰዓት ያህል በፈጀው በዚህ ውይይት ላይ ከአምባሳደሩና ከአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ኃላፊ በተነሱ ወቅታዊ የሀገራችን ጉዳዮችና  በተለይ ደግሞ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች  ስለሚገኙበት ተጨባጭ ሁኔታ እንዲሁም እየደረሰባቸው ስላለው ተጽእኖና  በጥቅሉ ከጊዚ ወደ ጊዜ ይበልጥ እየጠበበ በመጣው የፓለቲካ ምህዳር ዙርያ ሰፊና ጠቃሚ ውይይት አድርገዋል፡፡
የተከበሩ የአሜሪካ አምባሳደርና የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ በቅርቡ በኢዴፓ ተዘጋጅቶ በጋራ የፖለቲካ ፓርቲዎች  መድረክ ላይ ለውይይት የቀረበውን  የመገናኛ ብዙሃን  አሰራርና አጠቃቀም የማሻሻያ ሰነድን  አስመልክቶ ጥያቄዎች ያነሱ ሲሆን በተነሱት ጥቄዎች ላይ  ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በውይይቱ  ሂደት ሰነዱ የቀረበበት መንገድና በሰነዱ ጠቃሚነት ዙርያ መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን በውይይቱ ወቅትም የተነሱ አንኳር ነጥቦች  በሚባለውና አሜሪካንና እንግሊዝን ጨምሮ ከ15 ያላነሱ ሀገራት አምባሳደሮች በተወከሉበት የኢትዮጵያውያን ፓርትንርስ ግሩፕ (ኢፒጂ) የጋራ ኮሚቴ ላይ እንደሚነጋገሩበት ገልጻዋል፡፡

መልዕክተኞቹ በውይይቱ መርካታቸውንና ላነሷቸው ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ያገኙ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን ግንኙነቱ በቀጣይም እንዲካሄድ ሁኔታዎችን የሚያመቻቹ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተያያዘ ዜናም የፓርቲውን የድርጅት ጉዳይና የሕዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችን ያካተተውና  በኢዴፓ ፕሬዚዳንት የተመራው ቡድን  በአዋሳ፣ በአለታ ወንዶ፣ በወላይታ ሶዶ እና በሻሸመኔ የሚገኙ ጽ/ቤቶችን የጎበኝ ሲሆን በአዋሳ ከተማ ላይ የአራቱም ጽ/ቤቶች የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በተገኙበት በተደረገው ስብሰባ ጽ/ቤቶቹ  የጋራ ኮሚቴ ስለሚያቋቁሙበትና ስራቸውን አጠናክረው ስለሚሰሩበት ሁኔታ ውይይት  አደረገ፡፡

በጉብኝቱና በውይይቱ  ወቅት በምርጫ 2002  ያጋጠሙ ችግሮችና የምርጫውን ውጤትን ተከትሎ ስለደረሱ መጠነ ሰፊ እመቃዎች፣ እስር እና እንግልት እንዲሁም በተከሰቱት ከስራና ከአካባቢ የማፈናቀል ድርጊቶች ላይ ወይይት ተደርጎል፡፡
በውይይቱ ሂደት በተናጠል የቀረቡ ችግሮች በድርጅት ጉዳይ አማካኝነት በተዘጋጀው  ሪፖርት ማድረጊያ ፎርማት አማካኝነት በመረጃ ተደግፈው እንዲቀርቡና እንደ ችግሮቹ ባህርይ አስቸኳይነት እየመዘኑ ከሚመለከታው አካላት ጋር ከመወያየት ጀምሮ  ሕጋዊ ጥረቶችን ባካተተ መንገድ  በጽ/ቤት፣ በድርጅት ጉዳይና  በማህበራዊ ጉዳዮች ኮሚቴ ሰባሳቢዎች  አማካኝነት መፍትሄ እንዲፈለግላቸው ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

በመቀጠልም በየአካባቢቸው ስላለው እንቅስቃሴ ውይይት የተደረገ ሲሆን በተለይ ከምርጫ 2002 በኃላ የታየው የመቀዛቀዝና የመዳከም ስሜት መንስዔው በተለይ በገዥው ፓርቲ የተካሄደው ምርጫ ማጭበርበርና በመቀጠልም የተከሰተው ከፍተኛ የሆነ ማዋከብና ተጻእኖ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ በጥቅሉ ችግሩ ሁሉንም የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የካተተ ቢሆንም፤ የመዳከሙ ዝንባሌ በአንጻራዊነት ሲታይ ከኢዴፓ ይልቅ በሌሎች  ተቃዋሚ ፓርቲዎች  የሚብስ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ለዚህም በምሳሌነት ያቀረቡት ኢዴፓ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የህዝባችንን የልብ ትርታ የሚያዳምጡ ተከታታይ መግለጫዎችን ከመስጠት ጀምሮ ጠቅላላ ጉባኤውን በወቅቱ ማድረጉና አዲስ አመራረር መተካቱ ፓርቲው ትግሉን በጽናት ለመቀጠል ያለውን ዝግጁነት ያረጋገጠበት በመሆኑ በህዝብ ዘንድ መተማመንን መፈጠሩን ጠቅሰዋል፡፡

ይህም ሆኖ በኢዴፓ በኩል አሁንም በርካታ ስራዎች  መሰራት እንዳለባቸው መተማመን ላይ የተደረሰ ሲሆን በቀጣይነት ጽ/ቤቶቹ ስራቸውን  አጠናክረው ለመቀጠልና ተባብሮ ለመስራት እንዲችሉ በማቀድ አራቱንም ጽ/ቤቶች የሚያካትት አንድ የጋራ ኮሚቴ  በማዋቅር ጉብኝቱና ውይይቱ በመግባባት  ተጠናቋል፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter