ቅድሚ ትኩረት የዜጎችን ህይወት ለማዳን ይሁን

ዛሬም እንደገና የአገራችን ስም በድርቅና በረሃብ ምክንያት የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን መነጋገርያ ርዕስ ሆኖል፡፡ በዝናብ እጥረት ምክንያት በሁሉም የምስራቅ አፍሪካ አገሮች የተከሰተው ድርቅና ረሃቡ  ዓለምን እያነጋገረ ቢሆንም  የድርቅ ውጤት የሆነውን ረሃብ አስቀድሞ ከመተንበይ ጀምሮ ዜጎችን ከሞትና ከስደት ከመከላከል አኳያ የኢህአዴግ መንግስት ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዳልተወጣ ከዓለም አቀፍ ሪፖርቶች መረዳት ይቻላል፡፡

ድርቅ የዝናብ እጥረት ውጤት በመሆኑ ለዝናብ እጥረት ኢህአዴግን ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም፡፡ ነገር ግን ደርቅ እንዳይከሰት አካባቢን ማልማትና የዝናብ እጥረት ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ  ረሀብ በመፍጠር በሰዉ ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ከማድረሱ በፊት የመከላከል  ስራ መስራት የመንግስት ሀላፊነትና ግደታ ነዉ፡፡ በአርብቶ አደሩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የተከሰተው ድርቅ የሚያሳየን መንግስት አካባቢዎቹን በዘላቂነት ለመለወጥ የሚያስችል ሰፊ የልማት ስራ እንደተሰራ አድርጎ ሲያቀርብ የነበረው ሁሉ ትክክል አለመሆኑን ነው፡፡

ባለፉት ዓመታት  አርብቶ አደር ህዝብ በሚበዛባቸው ክልሎች  የሚታየው የፖለቲካና የስልጣን ሹኩቻ መቋጫ አጥቶ በመቆየቱ ምክንያት የተረጋጋ አስተዳደራዊ ስራን በመስራት መንግስታዊ ተቋማቱ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የሚወጡበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንዳልተቻለ ያታወቃል፡፡ ሹማምንቶቹ በስልጣን ሽሚያና ፖለቲካዊ ሽኩቻ ተጠምደው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ባለመቻላቸው ምክንያት ለህዝብ ተጠሪና ተጠያቂ የሆነ የአስተዳደር መዋቅር ለመዘርጋት አልተቻለም፡፡ በተከሰተው ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ አለመረጋጋትና ክፍተት ምክንያት የህዝቡን መሰረታዊ ችግሮች የሚቀርፍና ዘለቄታ ያለው ለውጥ ሊያመጣ የሚችል የልማት ስራ ካለመሰራቱም በላይ አርብቶ አደሩ የተረጋጋና የሰከነ  ህይወት ሊመራ ባለመቻሉ ምክንያት በተለያየ ጊዜ ለተደጋጋሚ ድርቅ ተጋላጭ ሆኖል፡፡

እንደ ኢዴፓ እምነት ከላይ ከቀረበው አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ችግር በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት አርብቶ አደሩ በሚኖርባቸው አካባቢዎች በከፋ ሁኔታ የተከሰተው የድርቅና የረሀብ አደጋ የሚያረጋግጠው ኢህአዴግ በአካባቢዎቹ ላይ ዘላቂ ለውጥ ሊያመጣ የሚያስችል ፖሊሲ ሲከተል እንዳልነበረ ነው፡፡ በእነኚህ አካባቢዎች የዝናብ እጥረት ተደጋግሞ የሚስተዋል በመሆኑ ምክንያት ከፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊና የልማት ችግሮች በተጨማሪ ተፈጥሮ ድርቅና ረሀብ እንዲከስት ሁኔታዎችን እንዳመቻቸ ያታወቃል፡፡ መንግስት መሰረታዊ ችግሩን ከመቅረፍ አኳያ ውጤታማ ስራ ያልሰራ ከመሆኑም በላይ ድርቅ ከተከሰተም በኋላ ቢሆን በዜጎች ህይወትና ንብረት ላይ የከፋ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ህይወትን ለመታደግ የሚያስችሉ በቂ ዝግጅት እንዳልነበር  የሚታየው ውጣ ውረድ ምስክር ነው፡፡

የኢህአዴግ መንግስት ችግሩን በወቅቱ ተረድቶ ስለችግሩ አግባብነት ያላቸውን መረጃዎች ለኢትዮጵያ ህዝብ ማቅረብ ባለመቻሉ ምክንያት የኢትዮጵያ ህዝብ አርብቶ አደሩ በብዛት በሚኖርባቸው አካባቢዎች  በሚገኙ  ወገኖቹ ላይ የደረሰውን ድርቅና ያስከተለውን የከፋ አደጋ አስቀድሞ የሰማው  ከመንግስት ሳይሆን ከውጪ እርዳታ ለጋሽ አካላት ነው፡፡ ይህ ድርጊት ለህዝብ ተጠያቂ እና ተጠሪ ነኝ ከሚል መንግስት የሚጠበቅ ባለመሆኑ፤ ኢዴፓን በእጅጉ አሳዝኖታል፡፡

በአሁኑ ወቅት ዝናብ አጠር በሆኑ የአርብቶ አደርና ከዚህ ቀደም በድርቅ ተጠቅተው በማያውቁ አንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በከፋ የረሀብ አደጋ ውስጥ መውደቃቸው ግልጽ ሆኖል፡፡ እውነታውን ከመንግሰት በኩል ከሚቀርቡ ዘገባዎች ማረጋገጥ ባይቻልም የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን በረሃብና በስደት ምክንያት የሰው ህይወት በከፋ ሁኔታ እየተቀጠፋ መሆኑን እየዘገቡ ናቸው፡፡ መንግስት ችግሩን ስለተቆጣጠርኩኝ የዜጎች ሕይወት እየተቀጠፈ አይደለም ቢልም የተከሰተው የከብቶች እልቂት፣ የምግብና ውሃ እጥረት የሰዎችን ህይወት እየቀጠፈ ለመሆኑ  በቂ ማረጋገጫ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት የመንግስት ዓይነተኛ ትኩረት መሆን የሚገባው በረሀቡ ምክንያት ህይወቱ የሚያልፈው ዜጋ ቁጥር ላይ እሰጣ አገባ መፍጠር ሳይሆን አንድም ዜጋ ቢሆን እንዳይሞት የሚደረገውን ጥረት ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በማስረዳት በቂ እርዳታ ተገኝቶ  አደጋው ሳይባባስ የዜጎችን ሕይወት መታደግ ነው፡፡  እንሰሳት እያለቁ ሰው ተርቦ እየሞተ ባለበት ሁኔታ የተረጂን ቁጥር ለመቀናነስ የሚደረገው የፕሮፓጋንዳ ጥረት የሰው ህይወት ከተረፈ በኋላ ሊደረስበት ስለሚችል ቅድሚያ ትኩረት የዜጎች ህይወት በማዳን ላይ እንዲሆን ኢዴፓ ያሳስባል፡፡

የኢህአዴግ መንግስት ይህን ከማድረግ ባሻገር በአርብቶ አደር አካባቢዎች ሲከተለው የነበረው የልማት ፖሊሲ ተጨባጭ ውጤት አለማምጣቱን ተቀብሎ በድርቀተ ጠጠቂዎች አካባቢ ዘላቂ ልማትና እድገት የሚያረጋግጥ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የአርብቶ አደሩ ህይወት የሚታደግ ልማትና ልማቱን የሚያረጋግጥበት የአስተዳደር ስርዓት እንዲዘረጋ ኢዴፓ ያሳስባል፡፡ በዚህ አጋጣሚም ድርቁ ወደተባባሰ ረሃብ ተለውጦ የዜጎች ሕይወት በከፍተኛ ቁጥር እንዳይቀጠፍ ጥረት እያደረገ ያለውን ዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ እያመሰገንን ችግሩን ዘለቄታ ባለው መንገድ ለመፍታት ሁለ ገብ እንቅስቃሴና  ዜጎቻችንን የማገዝ ጥረት  ተጠናክሮ እንዲቀጥል ኢዴፓ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter