ኢዴፓ አዲስ ፕሬዚዳንት መረጠ

Chane Kebede, President of Ethiopian Democratic Party

Chane Kebede, President of Ethiopian Democratic Party. Photo – Reporter

የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ማዕከላዊ ምክር ቤት ባለፈው እሑድ ፓርቲውን ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የሚመሩትን ፕሬዚዳንት መረጠ፡፡

ፓርቲውን በፕሬዚዳንትነት የሚመሩት አቶ ጫኔ ከበደ ናቸው፡፡ከአቶ ጫኔ በተጨማሪ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ዋና ጸሐፊና ዘጠኝ ሥራ አስፈጻሚዎችን መርጧል፡፡ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ዶ/ር ባንተይገኝ ታምራት ሲሆኑ፣ ዋና ጸሐፊ ሆነው የተመረጡት አቶ ሳህሉ ባዬ ናቸው፡፡

ቀደም ሲል ፓርቲውን በፕሬዚዳንትነት የመሩት አቶ ሙሼ ሰሙ፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሶፊያ ይልማና የፓርቲው ዋና ጸሐፊ አቶ መስፍን መንግሥቱ ሥልጣናቸውን ለአዲሶቹ ተመራጮች አስተላልፈዋል፡፡ አቶ መስፍን ቀደም ሲል በግል ጉዳያቸው ምክንያት ኃላፊነታቸውን በማስረከባቸው ቦታው ባዶ ነበር፡፡

የኢዴፓ የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ ልደቱ አያሌው ፕሬዚዳንት ለመሆን ዕጩ ሆነው ይቀርባሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር፡፡ ምክንያቱም ከአንድ ሳምንት በፊት በተካሄደው የኢዴፓ ጠቅላላ ጉባዔ 25 አባላት ያሉት ማዕከላዊ ምክር ቤት አባላትን መምረጡ ይታወሳል፡፡ አቶ ልደቱ የማዕከላዊ ምክር ቤት አባል ሆነው ተመርጠዋል፡፡

ቀጣዮቹን የፓርቲው ዘጠኝ ሥራ አስፈጻሚዎች፣ ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንትና ጸሐፊ የሚመርጠው ይህ 25 አባላት ያሉት ማዕከላዊ ምክር ቤት ነው፡፡ አቶ ልደቱ የማዕከላዊ ምክር ቤት አባል ሆነው በመመረጣቸው ፕሬዚዳንት ሆኖ በድጋሚ የመመረጥ አዝማሚያ ታይቷል በሚል የአቶ ልደቱ መመለስ ተጠብቆ ነበር፡፡

ነገር ግን አቶ ሙሼም በድጋሚ ለመመረጥ ፍላጐት ባለማሳየታቸው ኢዴፓ ከዶ/ር አድማሱ ገበየሁ፣ ከአቶ ልደቱ አያሌውና ከአቶ ሙሼ ሰሙ ቀጥሎ አራተኛውን ፕሬዚዳንት ሰይሟል፡፡

አራተኛው ፕሬዚዳንት አቶ ጫኔ ተወልደው ያደጉት በአማራ ክልል ባህር ዳር አካባቢ ነው፡፡ የመጀመርያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዚያው ተከታትለዋል፡፡

በመቀጠል አስመራ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በሒሳብ ትምህርት የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ሲያገኙ፣ ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በዴቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት አሜሪካ በሚገኘው አትላንቲክ ኢንተርናሽናል ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በርቀት ትምህርት ለማግኘት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡

አቶ ጫኔ በሥራው ዓለም በመምህርነት ለረዥም ጊዜ ያገለገሉ መሆናቸውና በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው ዲማ ኮሌጅ የተባለ ትምህርት ተቋም ባለቤት ናቸው፡፡ አቶ ጫኔ በፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡

አቶ ጫኔ ኢዴፓ የምሥራቅ ጐጃም ክንፍ እንዲያቋቁም ከማድረግ ጀምሮ እስከ መምራት ድረስ ከመጓዛቸውም በላይ፣ በ1997 ዓ.ም. ቅንጅትን በመወከል ተወዳድረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት የፓርቲውን በትረ ሥልጣን ተረክበው የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸውን አንድ ብለው ጀምረዋል፡፡

የዜና ምንጭ – ሪፖርተር

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter