ለዘላቂ ልማት የፌደራሊዝሙ ጉድለቶች ይታረሙ!

ሰሞኑን በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች የተከሰተውን ብጥብጥና በዚህ ምክንያት በሰዎችና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ የኢዴፓ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሚከተሉትን አቋሞች ወስዷል፡፡

  1. የኢዴፓ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ ባደረገው ውይይት እና ማጣራት ለግጭቱ መነሻ የሆነው ዋና ምክንያት ለአዲስ አበባና ለአጎራባች የኦሮሚያ ክልል ከተሞች የተዘጋጀው የጋራ የልማት መሪ ፕላን መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ ኢዴፓ የተዘጋጀው መሪ ፕላን ለአካባቢው የልማት እድገት ጠቃሚ መሆኑንና የአገራችንን ህግጋት የጣሰ አካሄድ አለመሆኑን አምኖበታል፡፡
  2. ማንኛውንም ቅሬታ አለኝ የሚል ወገን ቅሬታው ወይም ተቃውሞው ሊከበርለት ይገባል፡፡ መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ቅሬታ አለን የሚሉ ወገኖችን (ለሚያነሱት ቅሬታ ሌላ ፖለቲካዊ ትርጉም ሳይሰጥ) በአግባቡ ማዳመጥና ተገቢውን መልስ መስጠት ይገባዋል፡፡
  3. በመሪ ፕላኑ ላይ ቅሬታ ያላቸው ወገኖች ቅሬታቸውን ለመግለፅ ህጋዊና ሰላማዊ መንገድን ብቻ መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡ በሰዎች ህይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ተቃውሞን ለመግለፅ የሚደረገውን ሙከራ ኢዴፓ ያወግዛል፡፡
  4. መንግስት ህግና ስርአት እንዲከበር የማድረግ ሃላፊነት እና ግዴታ ያለበት መሆኑን እንደተጠበቀ ሆኖ በአመፅ መልክ ለሚገለፁ ተቃውሞዎች የሚወሰደው እርምጃ ጥንቃቄ የተሞላበትና በተቻለ መጠን በሰዎች አካልና ህይወት ላይ ጉዳት የማያስከትል መሆን ይገባዋል፡፡
  5. ሰሞኑን በተለያዩ ከተሞች በተፈጠረ ብጥብጥ የሰው ህይወትና የአገር ሃብት ተጠያቂው ማን እንደሆነ በአግባቡ የሚያጣራ ገለልተኛ ኮሚቴ መንግስት እንዲያቋቁምና በተጠያቂው አካል ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ኢዴፓ ይጠይቃል፡፡
  6. በአጠቃላይ እንዲህ አይነቱ ብሔራዊ ማንነትን መሰረት ያደረገና ለአገራዊ የልማት እድገት ፀር የሆነውን ጠባብ አመለካከት በአገራችን እየተጠናከረ የመጣውና ምናልባትም ወደፊት የበለጠ ተባብሶ ሊቀጥል የሚችለው በዋናነት በብሔራዊ ማንነት መሰረት ካደረገው የአገሪቱ የፌደራል አደረጃጀት ጉድለቶች በመነጨ ነው፡፡ ይህ አይነቱ ችግር በዘላቂነት ሊፈታ የሚችለው የፌዴራሉ አደረጃጀት እና ፖሊሲዎች ለአገር አንድነትና ለጋራ ልማት በሚበጅ መልኩ  ሲሻሻሉ ብቻ ነው ብሎ ኢዴፓ ያምናል፡፡

የኢዴፓ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
                      ሚያዝያ 28/2006 ዓ.ም
                ሰላምና ህብረ-ብሄራዊነት አላማችን ነው!!

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter