የኢዴፓ አመራሮች ስብሰባ እና ስልጠና ላይ ተካፍለው ተመለሱ

የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ አባላት ምርጫ ቦርድ ከundp ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ስብሰባ እና ስልጠና ላይ ተካፍለው ተመለሱ፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩንና በምርጫ 2007 ፓርቲዎች በሚኖራቸው ተሳትፎ ዙርያ ለማወያየት ለሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ባደረገው ጥሪ መሰረት ኢዴፓን ጨምሮ 8 ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ተካፋይ ሆነዋል፡፡

በቦታው ላይ የተገኙትም የፓርቲ ተወካዮች በጋራና በተናጥል ስለ ፖለቲካ ምህዳሩና ስለ ምርጫ 2007 ተሳትፎአቸው ለundp ተወካዮች አስረድተዋል፡፡ ስብሰባውን በንግግር የከፈቱት የምርጫ ቦርድ ዋና ጸሃፊ ሲሆኑ በቦታው የተገኙት የፓርቲው የጥናትና ምርምር ሃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ የፓርቲውን አቋም ለundp ተወካዮች አስረድተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ኤርምያስ ባልከው ለ5 ቀናት ደብረ ዘይት በሚገኘው የስራ አመራር ኢንስቲትዩት በግጭት አፈታት (conflict management) ዙርያ በተዘጋጀ ስልጠና ላይ ተካፍለው ተመልሰዋል፡፡ በስልጠናው ላይ ኢህአዴግን ጨምሮ 23 ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ተካፋይ ሆነዋል፡፡  ፓርቲዎቹ በግጭት አፈታት ዙርያ ያላቸውን ተሞከሮ በውይይትና በቡድን ስራ ላይ እርስ በርስ የተለዋወጡ ሲሆን  ችግር እንዳይፈጠርና ችግር ተፈጥሮም ቢገኝ  ፓርቲዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸውና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህላችን መዳበር እንዳለበት መጠቆማቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡

በስልጠናው ማጠቃለያም የምርጫ ቦርድ ዋና ጸሃፊ ለስልጠናው ተካፋዮች የምስክር ወረቀት ሰጥተዋል፡፡ ይሄ ስልጠና ለ2ኛ ግዜ የተካሄደ ሲሆን በመጀመርያ ዙር በተካሄደው ስልጠና ላይ የፓርቲው የፋይናንስ ሃላፊ አቶ አዳነ ታደሰ ተካፍለው መመለሳቸው የሚታወስ ነው፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter