በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው የነበሩትን የኢዴፓ አመራርና አባላት በሚመለከት

ሐምሌ 10 ቀን 2006 ዓ.ም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት የኢዴፓ አመራርና አባላት ትናንት ወደ ማምሻው ላይ በነጻ ተለቀዋል፡፡ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩበት ምክንያት ፖሊስ ሲያስረዳ ‹‹ ፍቃድ ሳይኖራቸው ግለሰቦች በቅስቀሳ ስራ ላይ በመሠማራታቸው እንደሆነ ሳጅን አንተነህ ገልጸዋል፡፡ ግለሰቦቹ የያዙት ፍቃድ የአዳራሽ ስብሰባ ፍቃድ እንደሆነና የቅስቀሳ ፍቃድ  እንደሌላቸው ፖሊስ አክሎ ገልጿል፡፡

ይህ በመሆኑም የመኪናው ባለቤት በህገወጥነት ተፈርጆ የገንዘብ ቅጣት የተጣለበት ሲሆን ኢዴፓም ‹‹ ከዚህ ጀምሮ ምንም አይነት ቅስቀሳ ማካሄድ አይችልም›› ሲል ፖሊስ አዟል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የፓርቲው ሃላፊዎች ወደ አዲስ አበባ መስተዳድር ህዝባዊ ስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ቢሮ ሔደው የቅስቀሣ ፈቃድ ጠይቀው ‹‹የቅስቀሳ ፍቃድ የሚባል ነገር የሌለና ሌላ ይህንን አይነት የቅስቀሣ ፈቃድ የሚሰጥ የመስተዳድሩ አካል እንደሌለ የክፍሉ ኃላፊ አቶ ማርቆስ ብዙነህ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነቱን ፍቃድ ሰጥተው እንደማያውቁም ተናግረዋል፡፡

የኢዴፓ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ኤርሚያስ ባልከው የአቶ ማርቆስን መልስ አጠናክረው ከዚህ ቀደም ኢዴፓ የህዝባዊ ስብሰባ ቅስቀሳ ሲያካሒድ እንዲህ አይነቱ ፍቃድ ወስደውም ሆነ  ተጠይቀው እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡ አቶ ኤርሚያስ አክለውም የህዝባዊ ስብሰባና  ቅስቀሳ ማሳወቂያ ዝርዝር ሒደቶች ውስጥ ለቅስቀሳ የሚሆን የተለየ ፍቃድ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ በከተማ መስተዳደሩ የከንቲባው ጽ/ቤት የተሰጠው ፍቃድ ላይም ግልባጭ ለብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንና ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተላከ ሲሆን ፖሊስ ይህንን እያወቀ እንዲህ አይነቱን እስር መፈጸሙ ግራ እንዳጋባቸው ገልጸዋል፡፡   በተጨማሪም አቶ ኤርሚያስ ኢዴፓ ለህዝባዊ ስብሰባው አንድ ቀን እንደቀረው ገልጸው የቅስቀሣው ስራ እንዲቆም ፖሊስ ያዘዘበት ምክንያት አሣማኝ እንዳልሆነና እና ምንም የህግ መሠረት የሌለው እንዲሁም ፀረ- ዴሞክራሲያዊ አካሔድ በመሆኑ ኢዴፓ የቅስቀሣውን ስራ ዛሬም የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አሁን ከጥቂት ሰዓታት በፊት በደረሰን ዜና መሠረት በትናንትናው እለት በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት የፓርቲው ቀስቃሽ አባላት በሙሉ ዛሬም በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም የፓርቲው የህዝብ ግንኑነት ሃላፊ  አቶ ወንደሰን ተሾመ፣ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ባልከው፣ የጥናትና ምርምር ሃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ እና የፓርቲው የአዲስ አበባ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዴንጎ ደሜ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ይህ ዜና እንደደረሰን የፓርቲውን ፕሬዘዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደን በጉዳዩ ላይ አነጋግረናቸው በዚህ አይነት ሁኔታ ህዝባዊ ስብሰባውን ማካሄድ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሰው ለብሄራዊ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስቸኳይ ደብዳቤ ጽፈው ግልባጭ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት እንደላኩ ገልጸዋል፡፡ መንግስት አስቸኳይ መፍትሄ ካልተሰጣቸው ህዝባዊ ስብሰባውን ለመሰረዝ ፓርቲው እንደሚገደድም ገልጸዋል፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter