የኢዴፓ መልዕክት

ሰሞኑን  በአዲስ አበባ   መስተዋል የጀመረው የፍጆታ ሸቀጦች  የዋጋ ንረት በአዲስ አበባም ሆነ በክልሎች  የሚገኘውን  ሸማቹን የህብረተሰብ ክፍል አስደንግጧል፡፡  በመላው አገሪቱ ላለፋት 15 ወራት ተስተውሎ የነበረው የነጠላ አሃዝ የዋጋ ግሽበት በዚሁ  ይቀጥላል የሚለው እምነትም በህብረተሰቡ ዘንድ እጅጉን እየሳሳ መጥቷል፡፡ ሰሞኑን ለታየው የዋጋ ንረት ዋነኛው መንስኤ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው የዋጋ ግምት (inflation expectation) ሲሆን ለዚህ የዋጋ ግሽበት ጥርጣሬ መንስኤ ደግሞ በቅርቡ የተገለፀው የመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ እና የ2007 ዓ.ም የባጀት ጉድለት የሚሞላበት መንገድ  በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡

ኢዴፓ ይህ የደሞዝ ጭማሪ የዋጋ ግሽበቱን ከማናር ባለፈ ለደሞዝተኛው እና ለጡረተኛው የህብረተሰብ ክፍል ዘላቂ እና የተጨበጠ ጥቅም አያመጣም ብሎ ያምናል፡፡ መንግስት ከደሞዝ ጭማሪው በፊት ሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የሚገኘው ስር የሰደደ ብልሹ አሰራር፣ የምንቸገረኝነት ስሜት እንዲሁም  በየመስሪያ ቤቱ የሚታየው የመንግስት እና የፓርቲ ስራ መደበላለቅ ችግሮቹ በቅድሚያ መቀረፍ አለባቸው ብሎ ኢዴፓ ያምናል፡፡ እነዚህ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ በመጡበት በአሁኑ ወቅት እንዲሁም የሲቪል ሰራተኛው አገልግሎት አሰጣጥና ምርታማነት ባልተሻሻለበት ሁኔታ የመንግስት ሰራተኛ የደሞዝ ስኬል መጨመሩ የዋጋ ግምቱን (inflation expectation) እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ የዋጋ ግሽበቱ ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ  ያሳድራል፡፡

ኢዴፓ ሸማቹን የህብረተሰብ ክፍል ማገዝ የሚቻለው የደሞዝ ወለሉን (minimum wage) በማሻሻል እንዲሁም በጊዜያዊነት የስቪል ሰራተኛው ከገንዘብ ጋር ያልተገናኙ ጥቅሞችን (non-monetary incentives) በመጠቀም ሲቪል ሰራተኛውን ከኑሮ ውድነት ችግር በማውጣት ነው ብሎ ያምናል፡፡ ሌላው የዋጋ ግምትን (Inflation Expectation) ጥርጣሬ የሚፈጥሩ የ2007 ዓ.ም ባጀት ጉድለት የሚሞላበት መንገድ ነው፡፡ መንግስት ይህንን ጉድለት የሚሞላው በግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ አና በአገር ውስጥ ብድር መሆኑ ለግሽበቱ ከፍተኛ ጥርጣሬን እያሳደረ ይገኛል፡፡ በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ አላማ የገንዘብ ፖሊሲ መሳሪያ ሆኖ ማገልገል ሳይሆን የመንግስትን ባጀት ጉድለት መሙያ ሆኖ ማገልገሉ የማእከላዊ ባንኩን ነፃነትና ገለልተኝነት በጥያቄ ውስጥ የሚጥል በመሆኑ ለዋጋ ግምት መናር የራሱ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ሂደት ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ነፃ እና ገለልተኛ ያልሆነው ብሄራዊ ባንክ ባለበት ሁኔታ መንግስት በፈለገና በፈቀደ ጊዜ  ከባንኩ መበደር መቻሉ ለዋጋ ግሽበቱ ቀጥተኛ አስተዋፆ ያደርጋል! በመሆኑም ኢዴፓ እንዲህ አይነቱን የዋጋ ግሽበቱን መቆጣጠር የሚቻለው ባጀቱን ለተገቢው  አላማ እንደሚውል በማረጋገጥ እናም ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚወጡትን የመንግስት ብክነቶችን በማስወገድ ነው ብሎ ያምናል፡፡ አንዲሁም መንግስት  ብሄራዊ ባንክን ነፃነት እና ገለልተኝነት የሚያጠናክር እርምጃዎችን በመውሰድ ባንኩ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት በመጨመር ነው ብሎ ያምናል፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter