ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያውያን ቋሚ ሀብት እንጅ የአገዛዝ ሥርዓቶች የስሜት መግለጫና ርዕዮተ ዓለም ማንፀባረቂያ መሣሪያ መሆን የለበትም!

Gizachew Animawበግዛቸው አንማው

ሠንደቅ ዓላማ ብሔራዊ ምልክቶች ከሚባሉት ውስጥ አንዱና ዋናው ነው፡፡ በቁም ትርጉሙ “ሰንደቅ” ቋሚ ማለት ሲሆን “ዓላማ” ደግሞ ምልክት የሚለውን ቃል ይወክላል፡፡ የሁለቱ ቃላት ጥምረትም ቋሚ ምልክት ይሆናል ፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን የኦሪት እምንትን ከመቀበሏ በፊት በኑቢያ በኋላም በአክሱም የነበሩት መንግስታት ለራሳቸው በሚስማማቸው አይነት የተቀረፀ ሠንደቅ ዓላማና ሥርዓተ መንግስት አቋቁመው ህዝቡን ሲያተዳድሩ እንደቆዩ የተፃፉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በኢትዮጵያ መንግስት አስተዳደር የዛሬው አይነት አረንጋዴ፣ቢጫ፣ቀይ የሆነው ሠንደቅ አላማ የተመሰረተው ወይም የተቀረፀው ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ982-958 ዓመተ ዓለም ባለው ዘመን በሀገራችን ነግሶ በነበረው ቀዳማዊ ሚኒሊክ እንደሆነ በ1919 ዓ.ም በብላቴን ጌታ ህሩይ የተፃፈው ጎህ ፅባህ መፅሐፍ ያሣያል፡፡ በሰንደቅ ዓላማ ላይ ምልክት ማድረግ የተጀመረው በአብርሃ ወአፀብሃ ዘመነ መንግስት ( 303-330 ዓ.ም) አንስቶ እንደሆነ ከላይ የተጠቀሰው መፅሀፍና ሠላማዊ ሠልፍና ውስጣዊ አሠራር ( 1939) የሚሉ ሠነዶች ያረጋግጣሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ቀጥሎ በአፄ ሐይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት በ1934 ዓ.ም በተደረገው የሠንደቅ አላማዎች አመሰራረት ሥርዓት መሠረት ፡ 1. የቤተ ነጋሲ ሠንደቅ አላማዎች 2. የቤተ መንግስት ሠንደቅ አላማዎች 3. የጦር ክፍሎች ሠንደቅ ዓማላዎችና 4. የሰላማዊ ክፍሎች ሠንደቅ አላማዎች ፤ በሚል በነባሩ ሰንደቅ ዓላማ ላይ የተመደቡበትን ክፍል የሚያንፀባርቅ ምልክት ብቻ ታክሎበት ሥራ ላይ ሲውል እንደቆየ የአፍሪካ ቀንድ መፅሄት በነሃሴ 10፣1985 እትሙ አስነብባል ወደ ዋናው ርዕስ ጉዳይ ስመጣ፤ ሰንደቅ አላማ ለሀገር አንድነት መጠናከር ከሚጫወተው ከፍተኛ ሚና በተጨማሪ ዜጎች የሀገር ፍቅር ስሜት እንዲኖራቸውም የሚያበረክተው ጉልህ አስተዋፅኦ መተኪያ የሌለው ነው፡፡ ሠንደቅ ዓላማ ይህንን ሓላፊነት በስኬት እንዲወጣ ከተፈለገ ከፖለቲካ መጠቀሚያነትና ከአገዛዝ ርዕዩተ አለም ተፅፅኖ ነፃ መሆን አለበት! በማንኛውም የዓለማችን ክፍል ፤ ዲሞክራሲያዊም ይህን አማባገነናዊ ሥርዓት ባለባቸው ሀገሮች በማንኛውም መንገድ ወደ ሥልጣን የወጣ አካል የሚያስተዋውቃቸው አዳዲስ ለውጦችና ፖለቲካዊ አስተሣሠቦች በምንም ታምር የሁሉንም ህዝብ ይሁንታ የሚገኙበት ነባራዊ ሁኔታ የለም፡፡ ስለሆነም ወደ ሥልጣን የወጣው አካል /አገዝዝ/ የሚያመጣቸው ለውጦች ሙሉ በሙሉ የሕዝብ ተቀባይነት የማግኝት ዕድል የላቸውም ፡፡ በሠንደቅ አላማ ላይ የሚጨመር ምልክት የአገዛዝ ስርዓቱ የለውጥ አካል በሚሆንበት ወቅት ሠንደቅ አላምው ከህዝብ ቋሚ ሃብትነት ወርዶ የአገዝዝ ሥርዓቶች የርዕዮተ አለም ማራማጅ አሊያም የፖለቲካ ፕሮግራም ማንፀባረቂያ መሣሪያ ይሆናል፡፡

የምልክቶቹ በሰንደቅ አላማው ላይ መቀመጥ የሚፈጥረው አሉታዊ አንድምታ ከአብራሃ ወአፅብሃ ዘመን መንግስት ጀምሮ ለ1700 ዓመታት በአረንጋዴ -ቢጫ-ቀይ ሠንደቅ ዓላማ ላይ የተለያዩ ምልክቶችን ማስቀመጥ የኢዮጵያዊያንን የሃገር ፍቅር ስሜት የጎዳና እየጎዳ ያለ እኩይ ተግባር ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የቅርቦቹን ሦስት የአገዛዝ ሥርዓቶች አንድ በአንድ ብናይ ችግሮቹን የበለጠ ያጎላዋል የሚል እምነት አለኝ አፄ ሓይለ ስላሴ የመሠረቱትን ንጉሳዊ አስተዳደር በሠንደቅ አላማው መካከል ላይ አንበሣ በማስቀመጥ የገለፁ ሲሆን ለአፄው ሥርዓት ደጋፊ የሆነ የህብረተሰብ ክፍል እንደለ ሁሉ ለሥርዓቱ ከፍተኛ ጥላቻ የነበረው የህብረተሰብ ክፍል ነቀፌታውንና ጥላቻውን ይገልፅ የነበረው ሥርዓቱ ያመጣቸውን ለውጦች ባለመቀበል ሲሆን ታይቷል፡፡ አሁንም እየታየ ነው፡፡ ሰንደቅ አላም ከህዝብ ሀብትነትና ከብሔራዊ ምልክትነት ደረጃ ወርዶ የሥርዓቱ መግለጫ በመደረጉ ምክንያት የሚገባውን ህዝባዊ ክብር እንዳይጎናፀፍ ሥርዓቱ የተጫወረው አሉታዊ ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡ የአፄውን ተሞክሮ የተከተለው የደርግ ሶሻሊስታዊ ስርዓት ሠንደቅ አላማ ላይ ማረሻና ሞፈር በኋላም የኢህዴሪን አርማ በምልክትነት ማስቀመጡ ጉዳዩን የበለጠ አጉልቶ ሠንደቅ አላማን ለርዕዮተ አለም ማራጃ መሣሪያነት ሲያውለው ታይታል፡፡ የአሁኑ “የኢህአዴግን ሰንደቅ ዓላማ” እንደሚባለው በደርግ ወቅትም የሶሻሊስት ሥርዓትን የሚቃወም ህብረተሰብ ክፍል ሠንደቅ አላማው ላይ የተቀመጠውን ማረሻና ሞፈር የሚያይበት ጊዜ ለሠንደቅ አላማው የሚሠጠው ክብር አነስተኛ እንደነበር የሚጠቅሱ መረጃዎች አሉ፡፡ እንደ ቅድመ አያቶቹ ሁሉ ሠንደቅ አላማን ለርዕየተ ዓለም /ፖለቲካ ፕሮግራም/ ማራመጃነት መጠቀምን አሜን ብሎ የተቀበለው የኢህአዴግ አገዛዝ ገና እግሩ አዲስ አበባ እንደገባ በአቶ መለስ በተሠጠ ጋዜጣዊ መግለጫ “ ጠባችን ከጨርቁ ሣይሆን ከበስተጀርባው ባለው ድርጊት ነው፡፡” ተብሎ መታወጁ ከዚህ በፊት ይደረግ እንደነበረው ምልክት ማስቀመጥና ሠንደቅ አላማን ወደ ርዕዮተ አለም ማራመጃነት ደረጃ ከማውረድም አልፎ ወደ “ጨርቅነት” የቀየረ አሣፋሪ ድርጊት ተፈፅሟል፡፡ ኢህአዴግ በሠንደቅ አላማ ላይ የፈፀመው አኩይ ተግባር “ጨርቅ” በማለት ብቻ የሚያበቃ አልነበረም፡፡ ገና በትግል ላይ እያለ “ነፃ ባወጣቸው” የትግራይና የአማራ መሬቶች ላይ የኢዮትጵያ ሠንደቅ አላማ እንዳይውለበለብ በኢህአዴግ አበላት ተፅዕኖ ሲደረግ እንደነበር የአፍሪካ ቀንድ መፅሄት የነሃሴ 10,1985 እትም ቃል በቃል ያስነብባል፡፡ ኢህአዴግ መላ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረ በኋላም ከክልል ሶስት በስተቀር ( በዚም ህዝቡ ስለታገላቸው ነው) እንዲሁም አፋርና አዲስ አበባ በስተቀር በሌሎች አካባቢዊች የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ሆን ተብሎ ደብዛው እንዲጠፋ ከላይ የተጠቀሰው መፅሔት በግልፅ አስፍራል፡፡ በወቅቱ በአንድንድ ቦታዎች የኢትዮጵያ ባንዲራ ተዘቅዝቆ ( ቀዩ ወደ ላይ) ተሠቅሎ ይታይ በነበረበት ወቅት የሽግግር መንግስቱ የብሔራዊ ሠንደቅ ዓላማን ለማስከበር የነበረው ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት አዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ ኢህአዴግ በተለመደው ሠንደቅ አላማ ላይ ምልክትን በማስቀመጥ በታሪክ ካየናቸው የመጨረሻው የአገዛዝ ሥርዓት ሲሆን ቢያንስ ቢያንስ ካለፉት ሥርዓቶች ተሞክሮ በመውሰድ ከማንኛውም ምልክት ነፃ የሆነ ሠንደቅ አላማ በሥራ ላይ ባዋለ ነበር፡፡ ግን ሳይሆን ቀረ፤ ሠንደቅ አላማም “ጨርቅ” ሆነ፡፡ ከ303 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያን ያስተዳደቱ የአገዛዝ ሥርዓቶች የራሳቸውን የፖለቲካና የርዕዮተ ዓለም አቅጣጫ የሚያንፀባርቅ ምልክት በሰንደቅ አላማ ላይ እንዲያስቀምጡ የሚስገድዳቸው ዋናው ምክንያት ( በእኔ እምነት) የኢትዮጵያ ህዝብ ለሠንደቅ አላማው ያለው ወሰን የለሽ ፍቅር ነው፡፡ የአገዝዙ ሥርዓቶች ይህንን የህዝብ ፍቅር ስለተረዱም ይመስላል ሠንደቅ አላማን ለአስተሣሠባቸው ማራመጃነት ለመጠቀም ወደኃላ ያላሉት፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በሚወደው ነገር መጠቀም መቻልና በቀላሉ ተቀባይነትን ለማግኝት መሞከር የአገዛዝ ሥርዓቶቹ አንዱ ሥልት ነበር፡፡ አሁንም ኢህአዴግ ለማድረግ እየሞከረ ነው፡፡ ለዛውም በአዋጅ አስገዳጅነት ፡፡ ሠንደቅ ዓላማ የአንድ ሀገር ህዝብ ወካይ ብሔራዊ ምልክት መሆኑና ሀገር እስካለ ድረስ ደግሞ ህዝብ በቋሚነት ሊገለገልበት የሚችል ቋሚ ባንዲራ ማስፈለጉ እንዳለ ሆኖ ሥልጣን በጨበጡ ማግስት የራስን ለሃገርና ለህዝብ በእኩልነት ሊወልክ የማይችል ምልክት ሠንደቅ አላማ ላይ ማስቀመጥ ትልቁ የሥግብግብት መግለጫ ባህሪ ነው፡፡ ለ1700 አመታት ያህል የተለያዩ ምልክቶችን በሠንደቅ ዓላማ ላይ ማስቀመጥ እየተለመደ መምጣቱና ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ የዜጎችን የሃገር ፍቅር ስሜት እየሸረሸረ ወደ መጨረሻው የአሁኑ ወቅት መድረሱ የጉዳዩ ባለቤት የሆኑ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ ርዕሰ ጉዳይ / issue/ ለመሆን በቅቷል፡፡ በዚህ ፅሑፍ አቅራቢ እምነት የኢትዮጵያ ሠንደቅ አላማ የሀገር ፍቅር ማጠናከሪ መሣሪያ ሆኖ በማገልገል በኩል የሚጫወተውን ጉልህ ሚና በመረዳት በሌላ በኩል ደግሞ የጥቁር ህዝብ የነፃነት ተምሳሌት በመሆን የሚያበረክተውን የድል አድራጊነት ስሜትና ኩራት በማጤን ከትውልድ ትውልድ በቋሚነት ሊሸጋገር የሚችል፤ ከአገዛዝ ሥርዓቶች ሠለባ ነፃ የሆነ፤ ምንም አይነት ምልክት ያልተጨመረበት አረንጓዴ -ቢጫ- ቀይ ሠንደቅ አላማ እንዲኖረን ከሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን አንዱ ነኝ፡፡ ይህ እንዲሆን መታገል የዚህ ትውልድ እንዱ የቤት ስራ ይመስለኛል!!!

 

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter