ኢዴፓ በዛሬው እለት አቅዶት የነበረው የባህር ዳር ህዝባዊ ስብሰባ ለሁለተኛ ጊዜ ተሰናከለ

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በዛሬው እለት አቅዶት የነበረው ህዝባዊ ስብሰባ ለሁለተኛ ጊዜ መሰናከሉን የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ኤርሚያስ ባልከው ገለጹ፡፡

ስብሰባው የተሰናከለበት ምክንያት የአማራ ክልል የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ህዝባዊ ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል ህዝባዊ ስብሰባውን ለማካሔድ የሚያስችለውን የእውቅና ደብዳቤ ለመስጠት ባለመቻሉ እንደሆነ አቶ ኤርሚያስ ገልጸዋል፡፡

ሕዝባዊ ስብሰባውን ለማካሄድ ከታቀደ ጊዜ ጀምሮ ፓርቲው በተደጋጋሚ የእውቅና ደብዳቤ እንዲሰጠው ሲጠባበቅ የቆየ ቢሆንም እስከዛሬው የህዝባዊ ስብሰባው እለት ድረስ ደብዳቤው ሊሰጠው እንዳልተቻለ ታውቋል፡፡ በዚህም የተነሳ ህዝባዊ ስብሰባውን በአስገዳጅ ሁኔታ ለማካሄድ አለመቻሉን ገልጾ ፓርቲው ለደረሰበት ከፍተኛ ኪሳራ የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት ሀላፊነቱን እንደሚወስዱ አቶ ኤርሚያስ ገልጸዋል፡፡

ኢዴፓ የሚከተለው ሶስተኛ አማራጭ በሰላማዊ እና በህጋዊ መንገድ የተከተለ ቢሆንም ከመንግስት በኩል ግን የአገሪቷን የዴሞክራሲ እና ሰላማዊ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያዳክሙ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ አቶ ኤርሚያስ አክለው ገልጸዋል፡፡ከሶስት ወር በፊት የፓርቲው አባላት በአዲስ አበባ ለህዝባዊ ስብሰባ በቅስቀሳ ላይ እንዳሉ ይህንን “የቅስቀሳ እውቅና ደብዳቤ አልያዛችሁም” በሚል ለሁለት ቀናት ታስረው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter