የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ

EDP_Manifesto_Coverየኢዴፓ ሦስተኛ አማራጭነት

ኢዴፓ የራሱን ጨምሮ በተቃውሞ ጐራ ውስጥ ያሉ ድክመቶችንና ጥንካሬዎችን አንጥሮ በመተንተን፣ ድክመቶችን በግልፅ በመቀበልና በማመን፣ የተቃዋሚው ጐራ በኢትዮጵያ አስተማማኝ የለውጥ አማራጭ እንዲሆን የሚያግዙ ሂሣዊ አቋሞችን ያራምዳል፡፡ ኢዴፓ ይህን የማድረግ አስፈላጊነትን ያረጋገጠው በተቃውሞ ጐራ ውስጥ ያሉ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችን ፖለቲካዊ ባሕርይ በመተንተንና ከብዙዎቹም ጋር አብሮ በመሥራት በኢትዮጵያ የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማምጣት ያላቸውን ውስንነት በማየት ነው፡፡ በኢዴፓ እምነት ኢህአዴግን መቃወም ብቻውን ዴሞክራሲያዊ መሆንን ወይም ከኢህአዴግ የተሻለ መሆንን አያረጋግጥም፡፡ ኢዴፓ በተቃውሞ ጐራ ውስጥ ያሉ በርካታ ችግሮችን በመተንተን ከሌሎች በተለየ ሁኔታ የሱ የትግል ስልት ዋነኛ መለያ ስልት ዴሞክራሲያዊ መሆን እንዳለበት ወስኗል፡፡ የኢዴፓ የትግል ስልቶች በባህሪያቸው ከጭፍን ጥላቻ እና ኢ-ምክንያታዊነት የራቁ በመሆናቸው ኢዴፓ እራሱን በተቃውሞ ትግሉ ውስጥ ካሉ ብዙ ኃይሎች የተለየ አማራጭ አድርጐ ለማቅረብ መርጧል፡፡ ኢዴፓ የኢህአዴግንም ማንአለብኝነትና ጭፍንነት ይቃወማል፣ ይታገላልም፡፡ ኢህአዴግ በአገራችን የዴሞክራሲ ስርአት መገንባት ያቃተው መሆኑንም ኢዴፓ በሚገባ ይረዳል፡፡

በመሆኑም ራሱን ከሁለቱ ኃይሎች የተለየ ሦስተኛ የለውጥ ትግል አማራጭ አድርጐ ለሕብረተሰቡ ያቀርባል፡፡ ሦስተኛ አማራጭነት የለውጥ ፍልስፍና ሳይሆን የትግል ስልትና የአሠራር ፍልስፍና ነው፡፡ መለያ ባሕሪዎቹም በምክንያታዊነት እውነተኛነት መቻቻልንና መከባበርን በማስቀደም መወያየትና መደራደር ናቸው፡፡ በሦስተኛ አማራጭ ስልታችን አስተሳሰብ መሠረት የተቃውሞ ትግሉ በጥላቻ ሳይሆን በአማራጭ አስተሳሰቦች ላይ በማተኮር በአንድ በኩል በኢህአዴግ ላይ የአስተሳሰብ የበላይነት እያገኘ በሌላ በኩል የተሣትፎ ፖለቲካን በማስቀደም በልዩነት ስር በአንድነት ለጋራ የአገር ጥቅም መሥራት ተገቢ ነው፡፡ ኢዴፓ ኢህአዴግን በፅኑ የሚቃወመውን ያህል አብሮ በመሥራትና በመደራደር ሂደት በብሄራዊ ፖለቲካችን ውስጥ በሁለት ፅንፎች የተወጠረውን የአክራሪነት ዝንባሌ በማለዘብ አጠቃላይ ወደ ሆነ አገራዊ መግባባት ላይ እንድንደርስ ተስፋ ያደርጋል፡፡ ይህ በተቃውሞ ጐራ ውስጥ ገና አጠቃላይ ተቀባይነት ያገኘ ባለመሆኑ በኢዴፓና በሌሎች ተቃዋሚዎች መካከል የልዩነት ምንጭ ሆኖ ይገኛል፡፡

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የኢዴፓ አቋም

ኢዴፓ በአለፉት ዓመታት የኢህአዴግ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎችን ሃገራዊ ፋይዳ እየመዘነ በጥብቅ ሲተች ብቻ ሳይሆን የተሻሉ ያላቸውን የፖሊሲ አማራጮችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ኢዴፓ ኢህአዴግ አጋኖ የሚያቀርበው የኢኮኖሚ እድገት እጅግ መሠረታዊ ችግሮች ያሉበት መሆኑን በመግለፅ ሲተች ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለሕዝባችን እጅግ ፈተና ሆነው ከሚገኙ ችግሮች መካከል ዋነኛው የዋጋ መናር ነው፡፡ የዋጋ መናር የፈጠረው የኑሮ ውድነት ከኢህአዴግ ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲና አመራር ድክመት የሚመነጭ ሲሆን ኢህአዴግ ይህን ለማስወገድ ተደጋጋሚ ጥረቶች ቢያደርግም የወሰዳቸው እርምጃዎች የፖሊሲውን ስህተት ያላረሙ በመሆናቸው ችግሩን የሚያባብሱ እንጂ የሚያቃልሉ አልሆኑም፡፡

በፖለቲካው መስክ ኢህአዴግ አገሪቱን በብቸኝነት ለመግዛት ያለውን አላማ ለማሳካት ሲል የአንድ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ዋነኛ መገለጫ የሆነውን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት በአገራችን እንዳይፈጠር አፍኖ ይገኛል፡፡ በሱ የበላይነትና ብቸኛ ቁጥጥር ላይ የመሠረተው የፖለቲካ ስርዓት ለስሙ ዴሞክራሲያዊ ነው ቢባልም በሃገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ሊኖር በሚገባው ስምምነት፣ ትብብርና ተሳትፎ ላይ የተመሠረተ ሊሆን አልቻለም፡፡

ኢህአዴግ የገዢ ፓርቲነቱን ሚና ከመንግሥትነት በላይ በማድረግ የአገሪቱን መንግሥታዊ መዋቅሮችና የሕዝብ ተቋማትን ጭምር የፓርቲው መዋቅር አድርጐ በመጠቀም ዜጐች ሁሉ ለኢህአዴግ የስልጣን አላማና ፍላጐት ብቻ እንዲገዙ እያስገደደ ይገኛል፡፡ የልማትና እድገት አጀንዳዎች ሁሉ በዜጐች ላይ የፓርቲ ስልጣኑን መጫኛ መሳሪያ ሊሆኑ በሚችሉበት መንገድ ብቻ ሥራ ላይ ያውላቸዋል፡፡ ዜጐችን ቀጥተኛና ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ በራሱ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ሥር እንዲወድቁ በማስገደድ በሕገ- መንግስቱ የተረጋገጡላቸውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶቻቸውን በሚጥስ መልኩ ከፍላጐታቸው ውጪ የራሱ የፖለቲካ መጠቀሚያ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡ በአገሪቱ አሉ የሚባሉ ዴሞክራሲያዊ ተቋሞች ሁሉ የኢህአዴግ ሥልጣን መጠቀሚያና መጠበቂያ ብቻ እንዲሆኑ በማድረጉ ተቋማቱ በገለልተኝነት እንዳይሰሩና አላማቸውን ለማሳካት የሚያስችል ነፃነት ብቻ ሳይሆን አቅምም እንዳይኖራቸው አድርጓል፡፡

የሕግ የበላይነት፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የመንግሥት አሠራር ባለመኖሩ በስልጣን መባለግ፣ የመልካም አስተዳደር እጦት ዛሬም የአገራችን ዋነኛ የፖለቲካ ችግሮች ናቸው፡፡ ኢህአዴግ በእለት ተእለት የመንግሥት እንቅስቃሴ ውስጥ የሕዝቡን መብትና ጥቅም የማያከብር መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በብቸኝነት የተቆጣጠረውን ፓርላማ እንዳሻው በመጠቀም በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉ የሕዝብ መብቶችንና ነፃነቶችን መሠረት ያደረጉ ድንጋጌዎች በማን አለብኝነት በመጣስ ከአገርና ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ የራሱን ሥልጣን ለማጠናከር ዋነኛ አላማ ያደረጉ አዋጆችን እያፀደቀ መተግበርን ሥራዬ ብሎ ተያይዞታል፡፡

መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅና የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጐች የዚህ ዋነኛ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ኢዴፓ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ካገር ጥቅም ይልቅ የኢህአዴግን የሥልጣን የበላይነት ለማረጋገጥና ለማስቀጠል ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉም ቢሆን ከሌሎች የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ካላቸው አገሮች ተቀዳሚ ነው ቢባልም በአገራችን የዜጐች መብትና ነፃነትን የሚጠብቁ የዳበሩ ተቋማት ባለመኖራቸው መንግሥት ሕጉን ሽብርተኛ ያልሆኑትን ዜጐችን ጭምር ማጥቂያ ለማድረግ አለማሰቡን በአግባቡ ለመረዳት በሚያስቸግር ሁኔታ ተግባራዊ እየሆነ በመሆኑ በዜጐች ላይ አላስፈላጊ የሆነ ፍርሃትንና ስጋትን የሚፈጥር ሆኗል፡፡

የጥላቻ ፖለቲካን እንጠየፋለን!

ኢዴፓ የዛሬውና የወደፊቱ ትውልድ ፓርቲ ነው!

የምርጫ ምልክታችን አበባ ነው!

ኢዴፓን ምረጡ አበባን ምረጡ!

የፓርቲው የአዲስ አበባ አድራሻ

ቁጥር 1 ጊዮን መድሃኒት ቤት አጠገብ፤ ቁጥር 2 በቅሎ ቤት ሃዊ ሆቴል ፊት ለፊት

ስልክ ቁጥር 0115-508727/28 ወይንም ደግሞ 0114-655765 የፖስታ ሣጥን ቁጥር 101458
ምንጭ – አዲስ ዘመን

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter