“ዘመቻ መልካም አስተዳደር” የተሸነፍነውና የምንሸነፈው ጦርነት

Lidetu Ayalewከልደቱ አያሌ

የኢዴፓ ብሄራዊ ም/ቤት አባል

ከጥቂት ሳምንታት በፊት መልካም አስተዳደርን አስመልክቶ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ያካሄዱትን ውይይት በቴሌቪዥን ተከታትየው ነበር፡፡ ውይይቱ በባህሪው “ኢህአዴግአዊ” ስላልነበር አስገርሞኛል፡፡ ኢህአዴግ ለህዝብ ይፋ በማይሆኑ የውስጥ ድርጅታዊ ውይይቶች ላይ እንዲህ ዓይነት የሞቀ ውይይት የማድረግ የቆዬ ባህል ያለው ድርጅት ቢሆንም ለህዝብ በይፋ በሚቀርቡ ውይይቶች ላይ ግን እንዲህ ዓይነት ግልፅነት እና ድፍረት ማሳየት ባህሉ አይደለም፡፡

ኢህአዴግ በራሱ መንገድ የሚያስጠናቸው ጥናቶችም ብዙውን ጊዜ ግልፅነት፤ድፍረትና ሃቀኛነት የሚጐድላቸው ቢሆኑም በሰሞኑ የውይይት መድረክ ላይ የጥናት ውጤቶችን ያቀረቡት ተkማት ግን በሚያስገርም ሁኔታ ሙሉ ነፃነትና ድፍረት ታይቶባቸዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ በመልካም አስተዳደር ችግርነት የተጠቀሱት ነጥቦች ሙሉ በሙሉ በሚባል መጠን ላለፊት በርካታ አመታት በተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በግል መገናኛ ብዙሃንና በአገሪቱ ዜጐች በተደጋጋሚ ሲቀርቡ የነበሩ ትችቶች ቢሆኑም እነዚህ ትችቶች በገዥው ፓርቲ በኩል የ “ጠላት ወሬ” ተደርገው ሲጣጣሉ የነበሩ ናቸው፡፡

ኢህአዴግ ከእንዲህ ዓይነቱ የሌሎችን ሃሳብና ትችት በጅምላ የማጣጣል በሽታው እስከወዲያኛው መፈወስ ያለበት ድርጅት ቢሆንም የሰሞኑ የመልካም አስተዳደር ውይይት ግን ሊያስመሰግነው የሚገባና “ይልመድብህ” የሚያሰኝ ተግባር ነው፡፡ በርግጥ ይህ ዓይነቱ ውይይት በዚህ ሳይወሰን በሌሎች መሰረታዊ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎችም ላይ ቀጥሎ ማዬትን ከልባችን እንመኛለን፡፡

ኢህአዴግ ያለ አመሉና ባህሉ በመልካም አስተዳደር ጉዳይ ላይ ለምን በዚህ መጠን በግልፅነት ለመወያየት ደፈረ? የሚለው ጥያቄ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ አንዳንዶች ውይይቱን እንዲሁ “አሉ” ለመባል የተካሄደ የይስሙላ ውይይት አድርገው አይተውታል፡፡ በእኔ አመለካከት ግን ይህ ውይይት የታይታ ሳይሆን የምር ነው፡፡

የመልካም አስተዳደር ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቃለለ ከመምጣት ይልቅ ይበልጥ እየተባባሰ በመምጣት በአሁኑ ወቅት ለስርዓቱ ህልውና ተጨባጭ አደጋ እየሆነ በመምጣቱ ምክኒያት ነውኢህአዴግ በአጀንዳው ዙሪያ በዚህ መጠን ውይይት ለማድረግና መፍትሄ ለማፈላለግ የተገደደው፡፡ በርግጥም በአንድ አገር የአንድ ስርዓት መዳከምና መበስበስ አይነተኛ ምልክት በአሁኑ ወቅት በአገራችን እየተከሰተ ያለው ዓይነት ቅጥ ያጣ የመልካም አስተዳደር ችግር በመሆኑ ኢህአዴግ ይህንን አደጋ ተገንዝቦ መፍትሄ ለማፈላለግ መሞከሩ ከራሱ የስልጣን ህልውናም ሆነ ከአገሪቱ ደህንነት አንፃር ተገቢ ዕርምጃ ነው፡፡

ነገር ግን በችግሩ ዙሪያ ግልፅ ውይይት ለማድረግና መፍትሄ ለመፈለግ መሞከሩ በራሱ የሚደነቅ ተግባር ቢሆንም ውይይቱን እንደተከታተልኩት ከሆነ ግን ኢህአዴግ እሰከአሁን ድረስ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማስወገድ ባካሄዳቸው ዘመቻዎች ሁሉ ተሸናፊ የሆነውን ያህል ወደፊትም ሊያካሂድ ባሰበው ዘመቻ ተሸናፊ እንደሚሆን የሚያሳይ አንድ በቂ ምክኒያት አለ፡፡ ይኸውም የመንግስት ባለስልጣናቱ ርዕሱጉዳዩን አስመልክቶ ባካሄዱት ውይይት የችግሩን አይነት፣የችግሩን ስፋትና ጥልቀት የችግሩን ፈፃሚዎችና ተጠቂዎች በተመለከተ ሰፊና ዝርዝር ውይይት ያካሄዱ ቢሆንምለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለማስገኘት የሚያስችለውን ዋናውን ጥያቄ ግን ሳያነሱትና ሳይወያዩበት ቀርተዋል፡፡ ያ መሰረታዊ ጥያቄ “ለምንድን ነው በመልካም አስተዳደር ረገድ ስርዓቱ በዚህ ዓይነት ስፋትና ጥልቀት ችግር ውስጥ የገባው?“ የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ምክኒያቱም “ችግሩ ከጅምሩ ለምን ተከሰተ?” የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ አንስተን የችግሩን መሰረታዊ ምንጭ ከስር ከመሰረቱ ካልተረዳነው በስተቀር የቱንም ያህል ስለችግሩ ስፋትና ጥልቀት ወይም ስለችግሩ ፈጣሪዎችና ስለተጠቂዎቹ ማንነት ስናወራ ብንውል ወደ መፍትሄው ሊዎስደን አይችልም፡፡

በመንግስት ባለስልጣናቱ ውይይትም ሆነ ያን ውይይት ተከትሎ በተለያዩ መድረኮች ሲካሄዱ ባየናቸው ውይይቶች ይህ መሰረታዊ ጥያቄ ሲነሳ አልሰማንም፡፡ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ /ማለትም ለአንድ ትውልድ ዘመን/ የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመፍታት ያስችላሉ የተባሉ ለቁጥር የሚያታክቱ የመዋቅር ማሻሻያ ዘመቻዎች ተካሂደዋል፡፡ በውይይቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃ/ማርያም እንዳሉት መንግስት የመዋቅር ማሻሻያ ትምህርት ለመቅሰም ከአውሮፓ እስከ ኤዥያ ያልረገጠው አገር የለም፡፡ ቢያንስ አቶ መለስ “ድርጅታችን በስብሷል” በማለት የተሃድሶ ዘመቻ ከአዎጁበት ከ1993 .ም ጀምሮ ለተከታታይ 14 ዓመታት ኢህአዴግ በመልካም አስተዳደር ችግር ዙሪያ አታካች ግምገማና ዘመቻ አካሂዷል፡፡

በዚህ ሁሉ ዓመታት የተካሄደው ዘመቻ መፍሄት ሊያመጣ ያልቻለው የችግሩ ስፋትና ጥልቀት ወይም የችግሩ ፈፃሚዎችና ተጠቂዎች ሳይታወቁ ስለቀረ ሳይሆን ችግሩን ለመፍታት የተካሄዱት ዘመቻዎች ከችግሩ መሰረታዊ ምንጭ ጋር ፍፁም ያልተዛመዱ በመሆናቸው ነው፡፡ ካለፈው ስህተት በአግባቡ መማር ስላልተቻለ አሁንም እየተደገመ ያለው ያው ያለፈው ዓይነት ዘመቻ ነው፡፡ በእኔ በኩል “የችግሩ መሰረታዊ ምንጭ ምንድን ነው?” ለሚለው ጥያቄ የራሴን መልስ ለመስጠት ከመሞከሬ በፊት በቅድሚያ አንድ ተዛማጅ ጥያቄ እዚህ ላይ አንስቸ ልለፍ፡፡

ይህ ጥያቄየምለምንድን ነው፡፡ ኢህአዴግ የመልካም አስተዳደርን ትርጉም በቁንፅል የቢሮክራሲ ውጣውረድ ጉዳይ አድርጐ የሚያየው? የሚል ነው፡፡ ምክኒያቱም የኢህአዴግ አንዱ ችግር መልካም አስተዳደር ፈርጀ ብዙና በአጠቃለይ በመንግስትና በህዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚመለከት ፅንስሃሳብ ሆኖ እያለ ኢህአዴግ ግን የአገልግሎት አሰጣጥ /service delivery/ ጉዳይ አድርጐ ይተረጉመዋል፡፡ ነገር ግን የተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶችና በርዕሰ ጉዳዩ ላይ የተደረጉ የተለያዩ የጥናት ውጤቶች የሰጡትን ትርጉም ስናይ—መልካም አስተዳደር መንግስት ወይም መንግስታዊ ተማት የዜጐችን ሁለንተናዊ መብት ማለትም የሰብአዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መብቶች በማስከበር ረገድ ያላቸውን ፍላጐት፣አቅምና ተግባራዊ ምላሽ የሚመለከት ነው፡፡ በተለይም የሰብአዊ መብትና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቁልፍ የመልካም አስተዳደር መገለጫዎች ሆነው እያሉ በኢህአዴግ ዘንድ ግን በጨረፍታም እንዲነሱ የሚፈለጉ ርዕሱጉዳዮች አልሆኑም፡፡ ይህ ቁንፅል አተረጓጐም ኢህአዴግ የቱንም ያህል ተደጋጋሚ የተሃድሶ ዘመቻ ቢያካሂድም ችግሩን በዘላቂነት እንዳይፈታ ካደረጉት ምክኒያቶች አንዱ ነው፡፡ ምክኒያቱም ሰብአዊ መብት ባልተከበረበትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በሌለበት ሁኔታ “መልካም” ሊባል የሚችል አስተዳደር አይኖርም፡፡ በሌላ አነጋገር ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተከበሩበት አንድ አገርም ጐልቶ የሚታይና በኛ አገር በሚታየው መጠን ህዝብን ሊያማርር የሚችል የመልካም አስተዳደር ዕጦት ሊኖር አይችልም፡፡ በርግጥ ኢህአዴግ በዚህ ረገድ የጠራ አመለካከት ቢኖረው ኖሮ “ይህ ሁሉ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ባለበትና ህዝብ በተማረረበት አገር ያለፈውን ምርጫ እንዴት 100% ላሸንፍ ቻልኩ?” ብሎ እራሱን በጠየቀና የችግሩን ምንጭ ከስር መሰረቱ ለመረዳት በሞከረ ነበር፡፡ ምክኒያቱም ከፍ ሲል ለመግለፅ እንደሞከርኩት የአንድ መንግስት ድክመትም ሆነ ስርዓት አልበኛነት ዋና መገለጫ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ስለሆነ በአገራችን ለተከሰተው የመልካም አስተዳደር ችግር ቀዳሚ ተጠያቂ መሆን የሚገባው ኢህአዴግ አንድን ምርጫ 100% ይቅርና 50% የማሸነፍ ዕድል ባልነበረው ነበር፡፡

ይህ የሆነው ኢህአዴግ 100% ለመመረጥ በሚያስችል መጠን በሕዝብ የሚፈቀር መንግስት ሆኖ ሳይሆን የአገራችን ምርጫ ራሱ በመልካም አስተዳደር ችግሮች የተተበተበ በመሆኑ ነው፡፡ ምክኒያቱም ቢሮክራሲው ውስጥ ተሰግስገው ህዝብን በደጅ—ጥናትና በሙስና ሲያማርሩት የሚውሉት ካድሬዎች ናቸውበተመሳሳይ ሁኔታ በምርጫ ወቅት ተቃዋሚ ፓርቲዎችንና መራጩን ህዝቡ በተለያዩ የአፈና ስልቶች ሲያሳድዱ የሚውሉት፡፡

በመንግስት ትዕዛዝም ይሁን በራሱ ተነሳሽነት በምርጫ ወቅት በተቃዋሚ ፓርቲዎች እና በመራጩ ህዝብ ላይ የተለያዩ ተፅኖዎችን በማሳደር የፖለቲካ ሙስና ሲፈፅሙ ዝም የተባሉ /ምንአልባትም አበጀህ የተባሉ/ ካድሬዎች በተመሳሳይ ሁኔታ በህዝብ ላይ የኢኮኖሚ ሙስና ለመፈፀም መሞከራቸው አይቀሬ ነው፡፡ መንግስት የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም ሲል የፖለቲካ ሙስና እንዲፈፅሙ የተጠቀመባቸው ካድሬዎች እነሱ በተራቸው የኑሮ ህልውናቸውን ለመጠበቅ ሲሉ የኢኮኖሚ ሙስና ቢፈፅሙ ምን ሊያስደንቅ ይችላል? ራሱ በፖለቲካ ሙስና ውስጥ የተዘፈቀ አንድ መንግስት ካድሬዎቹ የኢኮኖሚ ሙስና እንዳይፈፅሙ የመከላከል የሞራል ብቃትስ ይኖረዋል? ምንጊዜም በአንድ ስርዓት ውስጥ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሙስና እርስ በራስ ተመጋጋቢ ክስተቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ የመልካም አስተዳደርን ችግር ከልቡ መፍታት ከፈለገ የችግሮችን ምንጭም ሆነ የመፍትሄውን አቅጣጫ ከአገራችን የሰብአዊ መብትና የዴሞክራሲ ሆኔታ ጋር አያይዞ ሊፈትሽ ይገባዋል፡፡ ከሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት ጋር የተያያዙ የፖለቲካ ሙስናዎች ተገቢውን ትኩረት ባላገኙበት ሁኔታ ከኢኮኖሚውና ከቢሮክራሲ ውጣውረድ ጋር የተያያዙ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት አይቻልም፡፡ ለዚህም ነው የወቅቱ የኢህአዴግ የመልካም አስተዳደር ዘመቻ ከጅምሩ ተኮላሽቷል ለማለት የምደፍረው፡፡

ስለ ኢህአዴግ ቁንፅል የመልካም አስተዳደር አተረጔጐም ይህንን ያህል ካልኩ የመልካም አስተዳደር ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት መሰረታዊ ጥያቄ ነው ላልኩትና “ለምድነው በመልካም አስተዳደር ረገድ ስርዓቱ በዚህ ዓይነት ስፋትና ጥልቀት ችግር ውስጥ የገባው?” በሚለው ጥያቄ ዙሪያ ያለኝን የግል አመለካከት ለመግለፅ ልሞክር፡፡

በእኔ አመለካከት ለአገራችን የመልካም አስተዳደር ችግር የሚከተሉት ስድስት ነጥቦች በዋና ምክኒያትነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ እነሱም

  1. በመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚሾሙት ብቻ ሳይሆን የሚቀጠሩት ሚ ሠራተኞች የሚቀጠሩበት ዋና መስፈርት የፓርቲ አባልነት ወይም ደጋፊነት መሆኑ፤

  2. የመንግስት እና የፓርቲ (ኢህአዴግ) መዋቅሮች የተደበላለቁበት ሁኔታ መኖሩ፤

  3. የዴሞክራሲ፣ የሰብአዊ መብት ተማትና መገናኛ ብዙሃን ነፃና ገለልተኛ አለመሆናቸው፤

  4. ለመንግስት ሰራተኞች የሚከፈለው ደመወዝና አበል ከወቅቱ የኑሮ ውድነት ጋር የሚመጣጠን አለመሆኑ፤

  1. የህዝብ የተዛባ አስተሳሰብና ባህል መኖር

  2. ህዝብ አቅመቢስ /አቅም የለሽ/ እንዲሆን መደረጉ ናቸው፡፡

ከላይ ከተራ ቁጥር 1 እስከ ተራ ቁጥር 3 የተዘረዘሩት ጉዳዮች እርስበርስ የተሳሰሩና ተለያይተው መታየት የማይችሉ ናቸው፡፡ ሶስቱም ችግሮች መንግስት ከምንም ነገር በላይ ለፖለቲካ ስልጣን የበላይነቱ ቀናዒ ከመሆኑ ጋር የተያያዙ ችግሮች ናቸው፡፡ ኢህአዴግ በስልጣን ላይ የመቀጠሉን ጉዳይ የሞት የሽረት ጉዳይ አድርጐ ስለሚያየው ሁሉንም ነገር በቁጥጥር ስር የማዋል አባዜ ተጠናውቶታል፡፡ በተለይም በግራ ፖለቲካ አራማጅነት ያደገና በሽምቅ ተዋጊነት ህይወት ውስጥ ያለፈ ድርጅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከተkማትም ጋር ሆነ ከህዝብ ጋር ያለው ግንኙነት በጥርጣሬ፣በስጋትና በፍርሃት የተሞላ ሆኗል፡፡ በዚህ ምክኒያት በድርጅታዊ አሰራር የራሱን ቁልፍ አባላት በአመራርነት በማስቀመጥ በአገሪቱ የሚገኙ ተቋማትን በበላይነት ተቆጣጥሮአቸዋል፡፡

አንድ ለአምስት በመባል የሚታዎቀውን የጥርነፋ አደረጃጀት ስልት በመጠቀምም ከሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ጀምሮ የአጠቃላዩን ህዝብ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በቁጥጥር ስር ለማዋል እየሞከረ ይገኛል፡፡ ይህንን በማድረግም በአጋጣሚና በአስገዳጂ ሁኔታ ሳይሆን ሆነ ብሎ በማቀድ የመንግስትንና የኢህአዴግን መዋቅር አንድና አንድ በማድረግ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የዕርስ በዕርስ ቁጥጥርና ክትትል /check and balance/—ስርዓት ፈፅሞ እንዳይኖር አድርል፡፡ እንግዲህ በመንግስት የተለያዩ መዋቅሮች መካከል የቁጥጥርና የክትትል ስርዓት እንዳይኖር በተደረገበት ሁኔታ ነው ኢህአዴግ የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመዋጋት ቆርጨ ተነስቻለሁ የሚለን፡፡ በተለያዩ የመንግስት መዋቅሮች መካከል የቁጥጥርና የክትትል ስርዓት እንዲኖር የሚደረገው ለሌላ ጉዳይ ሳይሆን የመንግስት ባለስልጣናት እና ስራተኞች ያለአግባብ እንዳይባልጉና መልካም አስተዳደር ጠፍቶ በህዝብ ላይ በደል እንዳይደርስ ዋስትና ለመስጠት ነው፡፡

ታዲያ እንዲህ ዓይነት ስርዓት ሆነ ተብሎ እንዳይኖር በተደረገበት ሁኔታ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዴት ተደርጐ ሊፈታ ይችላል? ስለዚህ ኢህአዴግ በመልካም አስተዳደር ችግር ላይ ዘመቻ ሲጀምር ጦርነቱ የሚካሄደው በማንም ውጫዊ ወይም ባዕድ አካል ላይ ሳይሆን በሌሎች ላይ አፈና እየፈፀሙ ስልጣኔን ከጥቃት ይከላከሉኛል ብሎ ራሱ ካቋቋማቸው የራሱ መዋቅሮችና ካድሬዎች ላይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቀላል ውሳኔ አይደለም ፡፡ እንዲ ዓይነት ውሳኔ በካንሰር በሽታ የተለከፈን የራስን አካል ቆርጦ እንደመጣል ከባድ ውሳኔ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ነውአያሌ የመዋቅር ማሻሻያ ዘመቻዎች ተሞክረው ሲከሽፉ የታዬው፡፡

ዞሮ ዞሮ በአሁኑ ወቅት ለኢህአዴግ ከፊቱ የቀረቡለት የውሳኔ ምርጫዎች ሁለት ናቸው፡፡ በካንሰር የተለከፉ አካላቱን ቆርጦ ጥሎ ህልውናውን ማራዘም፣ አሊያም በካንሰር ከተለከፋ አካላቶቹ ጋር አብሮ መኖርና የህልውናውን ዕድሜ ማሳጠር ነው፡፡ በርግጥ ተቆርጦ የሚጣለው አካል ከማይቆረጠው የገዘፈ ከሆነ የህልውናው አደጋ በዚህኛውም አማራጭ ሊከሰት ይችላል፡፡ ይህንን በመረዳትም ይመስላል በውይይቱ ወቅት አንዳንድ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት የቀረበውን የጥናት ውጤት ለመቀበል ሲንገራግሩ የታዬት ፡፡ አቶ መለስም በዚህ አይነቱ የሃሳብ አጣብቂኝ /dillema/ ውስጥ ስለነበሩ ይመስለኛል ጥቂት ግለሰቦችን መቀጣጫ ከማድረግ ባለፈ ችግሩን ሳይፈቱት ለህልፈት የበቁት፡፡

ዋና ምክኒያት ነው ባይባልም በተራ ቁጥር አራት ላይ የተጠቀሰው የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ ዝቅተኛነትም ለአገራችን የመልካም አስተዳደር ዕጦት አንድ ምክኒያት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁሉም ባይሆኑም በርካታ ሰዎች በመንግስት መስሪያ ቤቶች ስራ የሚቀጠሩት ህዝብን የማገልገል ዓላማ ይዘው ሳይሆን ሌላ የኑሮ አማራጭ በማጣት ነው ፡፡ ብዙውን ጊዜ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ብቃትና እድሉ ያላቸው፣ወይም የግል ሥራ ለመስራት የሚያስችል ካፒታልና እውቀት ያላቸው ሰዎች የመንግስት ስራ የመቀጠር ፍላጐት የላቸውም፡፡ እነዚህ በዕውቀትም ሆነ በካፒታል አቅማቸው ዝቅተኛ ደረጃ ያሉ ዜጐች የመንግስት ተቀጣሪ የሚሆኑት ለኑሮአቸው በቂ ደመወዝ እናገኛለን ብለው በማሰብ ሳይሆን ብዙውን ጊዜ በጉቦ ወይም በጉርሻ መልክ ተጨማሪ ጥቅም የሚያገኙበት ቀዳዳ እንደማይጠፋ በመተማመን ነው ፡፡ በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ ኢህአዴግ መለመልኩት እያለ የሚመፃደቅበት በሚሊዩን የሚቆጠር አባልም ይህንን ዓይነት የጥቅመኝነት አስተሳሰብ ይዞ የተቀላቀለ እንጂ በኢህአዴግ ፖሊሲ እምነት ያለው ወይም ህዝብን የማገልገል ዓላማ ያለው ኃይል አይደለም፡፡ ይህ በተግባር የኢህአዴግ ሆነ የህዝብ ወገንተኝነት የሌለው ፣ነገር ግን በሰልፍ የኢህዴግን የአባልነት መታዎቂያ የወሰደ ጥቅመኛ/opportunist/ ኃይል ነው በየቢሮክራሲው ውስጥ ተሰግስጐ ህዝብን እያማረረ የሚገኝው፡፡ ኢህአዴግ የፓርቲ መታዎቂያ በመያዝና በእውነተኛ እምነት የፓርቲ አባል በመሆን መካከል ያለውን ልዩነት ተረድቶ የራሱን አሰራር እስካላስተካከለ ድረስ የአገሪቱ ቢሮክራሲ መቸውንም ጊዜ ቢሆን ከሙስና የፀዳለ ሊሆን አይችልም ፡፡

አሁን በአገራችን ከሚታየው የኑሮ ውድነት አንፃር ለአንድ መንግስት ሰራተኛ (ምን ዓልባትም ቤተሰብ ላለው) ከአንድ ሺ እስከ ሁለት ሺ ብር የወር ደመወዝ እየከፈሉ ስራውን በአግባቡ እንዲሰራ መጠበቅ በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ጉቦ የመብላት ፍቃድ ከመስጠት የተለየ አይመስለኝም፡፡ በርግጥ የደመወዝ ማነስ ጉቦ ለመብላት በራሱ በቂ ምክኒያት ላይሆን ይችላል፡፡ ትንሻ ደመወዛቸውን እንደምንም አብቃቅተው በድህነት እየኖሩ ያለሙስና ጥሩ አገለልሎት ለህዝብ የሚሰጡ አንዳንድ የመንግስት ሰራተኞች የመኖራቸውን ያህል በቄ በሚባል ደመወዝና የገቢ ምንጭ እያላቸውም ጉቦ ሲያባርሩ የሚውሉ የመንግስት ሰራተኞች ብዙዎች ናቸው፡፡ ከፍ— ሲል በተራ ቁጥር አምስት የተጠቀሰው የህዝብ የተዛባ አስተሳሰብና ባህል መኖርም ለመልካም አስተዳደር ዕጦት አንድ ምክኒያት የሚሆነው ከዚሁ ጋር ተያይዞ ነው፡፡

በመንግስት ኃላፊነት የያዙትን የአገልግሎት ወንበር እንደ አንድ አትራፊ የንግድ ድርጅት በመቁጠር ጉቦ ካልበሉ በስተቀር የዜጐችን ጉዳይ ላለመፈፀም የሚፈልጉ በርካታ የመንግስት ሰራተኞች የመኖራቸውን ያህል መብታቸውን በትክክለኛው መንገድ ለማስከበር ከመሞከር ይልቅ ማንም ገና ሳይጠይቃቸው ጉቦ ለመስጠት ተዘጋጅተው ወደ መንግስት ቢሮ የሚሄዱ ዜጎች ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡ ሙስና በአሁኑ ወቅት በአገራችን ወደዚህ የከፋ ደረጃ የደረሰው እንዲሁ ከመሬት ተነስቶ ሳይሆን በቆየው ታሪካችንም ጉቦ የመቀበልና የመስጠት ባህላዊ ዕርሾ በውስጣችን ስለነበረ ጭምር ነው፡፡ ለአገራችን መልካም አስተዳደር ችግር እየተባባሰ መምጣት ዋናው ተጠያቂ መንግስታዎ ስርዓቱ ቢሆንም ትውልዱን በጥሩ ስነምግባር ኮትኩተው የማሳደግ ኃላፊነት የሚጠበቅባቸው ወላጆች፣መምህራን፣ጋዜጠኞችና መንፈሳዊ አባቶች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ጭምር የተከሰተ ችግር ነው ፡፡

ከፍ ሲል ከተራ ቁርጥ 1 እስከ ተራ ቁጥር 5 የተዘረዘሩት ነጥቦች ለመልካም አስተዳደር አለመኖር ዋና ዋና ምክናያቶች መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከሁሉም በላይ ግን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ታግለን ማሸነፍ እንዳንችል ያደረገን ዋና ምክኒያት ህዝቡ አቅምአልባ የመደረጉ ዕውነታ ነው፡፡ ከማንም በላይ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ተዋግቶ ማሸነፍ ያለበት ህዝቡ ሆኖ እያለ ነገር ግን ህዝቡ በቢሮክራሲው ወይም በሙሰኞች የተሸነፈ አቅመ ቢስ ህዝብ ሆኗል፡፡ ዜጐች ጉዳያቸው በአግባቡ አልፈፀም ሲል፣ወይም ማንኛውም ዓይነት በደል ሲደርስባቸው ለበላይ አካል አቤቱታ ወይም ክስ አቅርበው የሚያገኙት መፍትሄ እንደሌለ ስለሚያውቁ ችግሩ እንዲፈታ የሚታገሉ ሳይሆን እራሳቸው የችግሩ አካል ሆነዋል:: ህዝቡ በመንግስት የመደመጥ መብት፣ወይም በመንግስት ላይ ተፅዕኖ የመፍጠር ጉልበት እስከሌለው ድረስ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ሊመጣ አይችልም፡፡ አንድ ህዝብ ተገቢውን ጉልበት አግኝቶ የለውጥ ኃይል ሊሆን የሚችለው ደግሞ ከምንም በላይ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቱ ተከብሮ እውነተኛ የፖለቲካ ስልጣን ባለቤት ሊሆን ነው ፡፡ ህዝቡ በተግባር የፖለቲካ ስልጣን ባለቤት ለሆን የሚችለውም ከአካባቢው አስተዳደሮዎች ጀምሮ እስከ ማዕከላዊው መንግስት ድረስ ያሉ ባለስልጣናትን በቀጥታ ምርጫ ወይም በውክልና የመምረጥና የመሻር እውነተኛ መብት ሲኖረው ብቻ ነው፡፡

አሁን ባለው የአገራችን ተጨባጭ ሆኔታህዝብ እንኳንስ የመንግስት አለቃ ሆኖ የአገሩን ዕጣፋንታ ሊወስን ይቅርና ከዕለትተዕለት ኑሮው ጋር የተያየያዙ ጥቃቅን አገልግሎቶችን እንኳን ማስፈፀም የማይችል አቅመቢስ ህዝብ ሆናል፡፡ ህዝብ ሲናገር በማይደመጥበትና ሲቆጣ በማይፈራበት አገር የመልካም አስተዳደር ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት ማሰብ ዘበት ነው፡

ስለዚህ ካለፋት ዘመቻዎች በተለዬና በተሻለ አህአዴግ የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት ከልብ ካሰበ የህዝቡን የሰብዓዊና የዴሞክራሲ መብት ጥያቄዎች በአግባቡ በመመለስ እራሱን ሳይሆን ህዝቡን እውነተኛ የስልጣን ባሌቤት በማድረግ የመልካም አስተዳደርን ችግር ከምንጩ ለማድረቅ መወሰን አለበት ፡፡ይህ ውሳኔ የራስን አካል ቆርጦ እንደመጣል ከባድ ውሳኔ ቢሆንም አማራጭ የሌለው መፍትሄነው፡፡ አለዚያ የመልካም አስተዳደር ዘመቻዎችን ባለፈው የተሸነፍነው ብቻ ሳይሆን ወደፊትም የምንሸነፈው ጦርነት እንደሚሆን ከወዲሁ የታወቀ ነው፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter