የኢዴፓ የ3ኛ አማራጭነት ሚና ግምገማ

Adane Tadesseበኢዴፓ የአዲስ አበባ ኮሚቴ በተዘጋጀ ስብሰባ ላይ

ለውይይት የቀረበ ጽሁፍ

ከአዳነ ታደሰ

የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ

ኢዴፓ ከተመሰረተ 16 አመት ያለፈው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ብዙ ውጣ ውረዶችን ያሳለፈ ፓርቲ ነው፡፡ ፓርቲው ካሳለፋቸው መጥፎ ነገር ግን ደግሞ መልካም ተሞክሮዎችን ካገኘባቸው ጊዜያቶች አንዱ 1997 ምርጫን ተከትሎ የገጠመውን የሚያህል ክፉ ግዜ ገጥሞት አያውቅም፡፡ በዛ ክፉ የታሪከ አጋጣሚ ግን ኢዴፓ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሚታዩ አሮጌ የፖለቲካ ባህሎቻችን ኢትዮጵያንና ህዘቧን ለረዥም ግዜ ዋጋ እያስከፈሉ እንደነበር በስፋት የተረዳበት ነው፡፡ ፓርቲው በ1998 .ም በትግል ውስጥ ያሳለፋቸውንና የገጠሙትን መሰናክሎች በጥልቀት ከመረመረ በኋላ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ስር ሰዶ ውስጣችንን እየበላ የሚገኘውና ለስኬት ያላበቃን ችግር ሌላ ሳይሆን የምንከተለው የትግል ስልትና አሰራራችን እንደሆነ ጠንቅቆ ለመረዳት ቻለ፡፡ ይሄንንም የቆየ አሮጌ የፖለቲካ ባህል ለመዋጋት ይቻል ዘንድም አዲስና ስልጡን የፖለቲካ ባህል ይዞ መቅረብ አስፈላጊ መሆኑን በማመን 3ኛ አማራጭ አድርጎ ራሱን ግልጽ አወጣ፡፡ ኢዴፓ ራሱን ጨምሮ በተቃውሞ ጎራ ውስጥ ያሉ ድክመቶችንና ጥንካሬዎችን አንጥሮ በመተንተንና፣ ድክመቶችንም በመቀበልና በማመን የተቃውሞው ጎራ አስተማማኝ የለውጥ አማራጭ በኢትዮጵያ እንዲሆን ሒሣዊ አቋሞችን ለማራመድ በቁርጠኝነት ተነሳ፡፡ ይሄንን የማድረግ አስፈላጊነትን ከማንም በላይ የተረዳው ደግሞ ከማንም በላይ በሴራ ፖለቲካ ዋጋ በመክፈሉ ነው፡፡ ብዙዎቹም የፖለቲካ ሃይሎች በሚያራምዱት አቋም በፍጹም ዴሞክራሲያዊ የሆነ የስርአት ለውጥ ሊያመጡ እንደማይችሉ በመረዳትም 3ኛ አማራጭ ሆኖ ወደ ህዝቡ ሊቀርብ ችሏል፡፡ በወቅቱ የሃገራችን ፖለቲካ የደረስንበት ድምዳሜ ከእንግዲህ አዲስና ምክንያታዊ የሆነ የ3ኛ የፖለቲካ አማራጭ ያስፈልጋታል ብለን በማሰብ ምክንያታዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ በሃገራችን እንዲኖር ፋና ወጊ ሁነን ወጣን፡፡ ፡ በተጨማሪም ኢዴፓ ከሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲዎችም በተለየ የትግል ስልቱ ዋኘኛ መለያ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆንም ወስኖ ነበር የተነሳው፡፡ የኢዴፓ እነዚህ ዴሞክራሲያዊ የትግል ስልቶች በባህሪያቸው ከጭፍን ጥላቻ እና ከኢምክንያታዊነት የራቁ በመሆናቸው ከተቃውሞ ትግሉ ውስጥ ካሉ ሃይሎች የተለየ የፖለቲካ አማራጭ ሆኖ ለመታየት አስችሎታል፡፡ በነገራችን ላይ 3ኛ አማራጭነት የለውጥ ፍልስፍና ሳይሆን የትግል ስልትና የአሰራር ፍልስፍና ነው፡፡ ይሄን ግልጽ ማድረግ የፈለኩት ብዙዎቹ ይሄን የትግል ስልት እንደ የፖለቲካ ፍልስፍና በመቁጠር ሲከራከሩ በማስተዋሌ ነው፡፡ ይሄ የትግል ስልት መለያ ባህሪዎቹን ከታች የምመጣበት ቢሆንም በጥቅሉ በምክንያታዊነት መቻቻልንና መከባበርን በመስቀደም መወያየትና መደራደር ናቸው፡፡ በሶስተኛ አማራጭ ስልታችን አስተሳሰብ መሰረት የተቃውሞ ትግሉ በጥላቻ ሳይሆን በአማራጭ አስተሳሰቦች ላይ በማተኮር በአንድ በኩል በኢህአዴግ ላይ የአስተሳሰብ የበላይነት በመያዝ በሌላ በኩል ተሳትፎአችንን በማጉላት በልዩነት ስር በአንድነት ለጋራ የአገር ጥቅም በመስራት ነው፡፡ ኢዴፓ ኢህአዴግን በጽኑ የሚቃወመውን ያህል አብሮ በመስራትና በመደራደር በሁለት ጽንፎች የተወጠረውን የሃገራችንን ፖለቲካ በማለዘብ ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች ወደ ሃገራዊ መግባባት የሚደርሱበትንም ሁኔታ በዚህ ስልታችን እንደሚያመጣ ተስፋ ያደርጋል፡፡ አሁን ግን ይሄ አስተሳሰባችን በሌሎች ተቃዋሚዎች ተቀባይነት ያላገኘ አስተሳሰብ በመሆኑ ለጊዜው አስከ ልዩነታችን መጓዛችን የማይቀር እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ለመሆኑ ይሄ አስተሳሰባችን በምን በምን ይገለጻል

1በአሮጌው የፖለቲካ ባህላችን እንደተለመደው በጭፍን ከመደገፍና ከመቃወም በሽተኛ የሆነ አስተሳሰብ ተላቆ ፖለቲካን በምክንያታዊነት ማራመድ ነው፡፡

2አስከዛሬ ከነበረው የጥላቻ፣ የስሜታዊነትና የኩርፊያ የፖለቲካ ባህል ተላቆ በመትኩ የመደማመጥ፣ የመቻቻል፣ እውቅና የመስጠትና አብሮ የመስራት አዲስ የፖለቲካ ባህልን በሃገራችን ማራመድ ነው፡፡

3በህዝቡ ዘንድ ጊዜያዊ ድጋፍ ለማግኘት ሲባል ብቻ ምን ብንናገር ደስ ይለዋል አያሉ የእወደድ ባይነት ፖለቲካን ማራመድ ሳይሆን ሃገርንና ህዝብን አስከጠቀመ ድረስ ጊዜያዊ የህዝብ ትችትና ተቃውሞን አየተቀበሉም ቢሆን እውነቱን ተናግሮ የመጣውን የመቀበል ፖለቲካን ማራመድ ነው፡፡

4እንደአመቺነቱ ቦታና ግዜ እየመረጡ ሳይሆን አስከመጨረሻው መደራጀት በህገመንግስቱ አስካልተፋቀ ድረስ ሰላማዊ ትግልን ብቸኛ የትግል ስልት አድርጎ ማየት ነው፡፡

5የዴሞክራሲያዊ ሂደቱን ልዩ ትኩረት በመስጠት ማጎልበት ላይ ያተኮረ፣ ባለው ላይ እየደመሩ እንጂ ያለውን እያጠፉ ከዜሮ የማይጀመርበትን የፖለቲካ ትግል የሃገሪቱን ህጎችና ተቋማት እያከበሩ ማካሄድ፡፡

6ለሃገሪቱ ሁለንተናዊ ችግሮች በስልጣን ላይ ያለውን አካል ወይም ሌሎችን ብቻ ተጠያቂ ከማድረግ ሌሎችንም ሆነ እራስን የሃገሪቱ ችግሮችና የመፍትሄውም አካል አድርጎ ማየት ነው፡፡

7በሃገራችን ስልጣን በሃይል ከሚያዝበት ባህል ተላቀን ስልጣን በሰላማዊና በምርጫ ስርአት የሚያዝበትን አዲስና ስልጡን የፖለቲካ ባህል ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ እውን እንዲሆን ማድረግ፡፡

8እንደስካሁኑ የፖለቲካ ባህላችን እንደተለመደው የፖለቲካ ተቀኛቃኝን ተገቢ ባልሆነ ፍረጃ፣ በስም ማጥፋትና በአሉባልታ ዘመቻ ሳይሆን በአጀንዳ ጥራትና በሃሳብ የበላይነት ታግሎ ማሸነፍ ነው፡፡ ግን መሰረተ ቢስ አሉባልታ በመንዛት ስም ለማጥፋት የሚሞክሩትን ሃይሎች በሃቅ ላይ የተመረኮዘ መረጃ እያቀረቡ ማጋለጥና ያለውን እውነት ማስረዳት ናቸው፡፡

ለኢዴፓ የ3ኛ አማራጭነት ሚና መጎልበት ያሉ ተግዳሮቶች

ኢዴፓ በሚከተለው የ3ኛ አማራጭነት ሚና እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉት ተግዳሮቶች ሁለት አይነት ናቸው እላለሁ፡፡ አነሱም ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶች ሊባሉ ይችላሉ፡፡

አንደኛው ውስጣዊ ተግዳሮት መገለጫው በራሱ በፓርቲው ውስጥ የሚገለጽ ሲሆን በዋናነትም በአባላቱና በአመራሩ ውስጥ የሚታየው ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከህዝቡ፣ ከተቃዋሚዎችና ከኢህአዴግ እየገጠመው ያለው ተግዳሮት ነው፡፡ በአመራሩና በአባላቱ ውስጥ ከሚታየውና ከሚስተዋለው ተግዳሮት መካከልም፣

1ፓርቲው የሚመራበትን መርሕ ጠንክሮ ያለመያዝና በአቋም መወላወል፣

2በውጫዊ ተጽዕኖዎችና አሉባልታዎች መሸበርና ስሜታዊ የመሆን፣

3ፓርቲው የሚወስዳቸው አቋሞች ከሌሎች ፓርቲዎችና ከህዝቡ ግዜያዊ ስሜቶች ጋር እንዲሄድ የመፈለግና ምክንያታዊ አለመሆን፣

4ፓርቲው በያዛቸው አቋሞች የሚደርስን ውጫዊ ተጽዕኖ መቋቋም አለመቻል፣

5ተስፋ መቁረጥና ከፓርቲው የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ውጭ መሆን፣

6በየወቅቱ በሃገሪቱ ውስጥ በሚከሰቱ ፖለቲካዊ ትኩሳቶች መዋጥና ፓርቲውም ግዜያዊ ስሜት ውስጥ እንዲገባ ግፊት ማድረግ፣

7የመቻቻል ፖለቲካን ሊያጎለብቱ የሚችሉ መድረኮች ላይ ፓርቲው የሚያደርገውን ተሳትፎ ማንቋሸሽና ከእንደዚህ አይነቶቹ መድረኮች እንዲወጣ ግፊት ማድረግ፣

8ለዚህ አስተሳሰብ ፋና ወጊ ነን ብንልም አስተሳሰባችንን በተገቢው መንገድ መሸጥ አለመቻል፣

9ፓርቲው ያለው የፋይናንስ አቅም ውሱን መሆን፣

10ለብሄራዊ መግባባት የሚጠቅሙ አቋሞች ላይ አጠቃላይ መግባባትን መፍጠር አለመቻል የመሳሰሉት ናቸው፡፡

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ተግዳሮቶች በውስጣችን የታዘብኳቸው ሲሆን ይሄ የ60ዎቹ አሮጌ የፖለቲካ ባህል ምን ያህል ስር የሰደደና ይሄ የያዝነው ስልጡን የፖለቲካ ባህል በሃገራችን ኢትዮጵያ አግሩን እንዲተክል በፓርቲያችን ውስጥም የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት ትልቅ ትግል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው፡፡

ሁለተኛው ውጫዊው ተግዳሮት በስፋት የምንጠብቀውና ስንነሳም ልንታገለው የቆረጥንበት ቢሆንም 3ቱ የሃገራችን የፖለቲካ ተዋናዮች ላይ የማየውን ውጫዊ ተግዳሮት ለውይይት እንደመነሻ ላቅርብ፡፡ እነዚህ 3ቱ ተዋናዮች ህዘቡ፣ተቃዋሚዎችና ኢህአዴግ መሆናቸውን በድጋሚ ለመግለጽ አወዳለው፡፡ በነገራችን ላይ በነዚህ ሃይሎች ላይ ይሄን ስልት በድፍረት ማራመድ ስንጀምር ያጋጠሙን ችግሮች ይሄን ስልት ለመያዝ ያስቻለን ምክንያት በቂና ትክክል ለመሆኑ ማረጋገጫ ስለሆነ ባይገጥመን ነበር ስህተት የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ወገባችንን ጠበቅ እንድናደርግ የሚያስገድዱን እና ትግሉ ምን ያህል ወሳኝ መሆኑን የሚጠቁመን ነው፡፡

፨ ለመሆኑ ውጫዊ ተግዳሮቶቹ ምንድን ናቸው

፨ ህዝቡ ጋር ያሉ ተግዳሮቶች፣

1አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍል በምክንያት መቃወማችንና መደገፋችንን ከኢህአዴግ ጋር የመለጠፍ አድርጎ የማየቱ ተገቢ ያልሆነ አተያይ፣

2የምንወስዳቸውን ተገቢ የሆኑ አቋሞች የፍርሃትና የመልመልመጥ አድርጎ የማየት፣

3ለመቻቻል ፖለቲካ የምናደርገውን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ምክንያታዊ ባልሆነ ሁኔታ መቃወምና ማውገዝ ከዛም አለፍ ሲል የኢህአዴግ አጨብጫቢ አድርጎ የመቁጠር፣

41997 በፓርቲው ላይ የተነዛውን የአሉባልታ ዘመቻ የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል አሁንም ድረስ ሊፍቀው ያለመቻል፣

5ለትግሉ መጠናከር የሚጠቅመው የተወሰነው ወጣት የህብረተሰብ ክፍል በሰላማዊ ትግሉ ላይ ያለው ተስፋ ተሟጦ ማለቁ፣

6ቀላል የማይባል የህብረተሰብ ክፍል ካልደፈረሰ አይጠራም በሚል ብሂል በማንኛውም ሁኔታ ለሚመጣ የመንግስት ለውጥ ጉጉ በመሆን ለስርአት ለውጥ ለሚደረግ ትግል ጀርባውን በመስጠት ለለውጥ ሃይልነት ዝግጁ አለመሆን የመሳሰሉት ናቸው፡፡

፨ ተቃዋሚው ጋር ያሉ ተግዳሮቶች

1 ተቃዋሚው ከ1997ቱ የፖለቲካ ቀውስ በኋላ ለፓርቲያችን የተወሰኑ ፓርቲዎች ተገቢውን እውቅና አለመስጠት፣

2በፓርቲያችን ላይ የተደራጀና ተከታታይነት ያለው መሰረተ ቢስ አሉባልታ ማሰራጨት፣

3ለመቻቻል ፖለቲካ ፓርቲው የሚከፍለውን ዋጋ በህዝቡ ዘንድ ዋጋ እንዳይኖረው ማንቋሸሽና ተገቢ ያልሆነ ስም ማጥፋት ማካሄድ፣

4አብዛኞቹ ተቃዋሚዎች አሁንም የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው ከሚል አመለካከት ወጥተው የሃሳብና የአጀንዳ ፓርቲ መሆን አለመቻላቸው፣

5አብዛኛው ተቃዋሚ በሰላማዊ ትግል በሚመጣው ለውጥ ጠቃሚነት ላይ እርግጠኛ ከመሆን ይልቅ በወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳቶች የመዋጥና የመወላወል ባህሪ ያላቸው መሆን፣

6አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ ጠንካራ አቋም ይዞ ከመታገል ይልቅ በሆነው ባልሆነው የኢህአዴግ መጠቀሚያ መሆን፣

7አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የእወደድ ባይነት ፖለቲካ አራማጅ መሆናቸው የመሳሰሉት ናቸው፡፡

፨ በኢህአዴግ ዘንድ ያለ ተግዳሮት

1የምንከተለውን ስልት ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ምንም አይነት ልዩነት እንደሌለው በመረዳት ልዩነታችንን አምኖ ያለመቀበል፣

2በተለያዩ መድረኮች ላይ የፓርቲው አመራሮች የሚሰጡትን አስተያየት እየቆራረጡ በሚዲያ በማቅረብ ትክክለኛ የሆነውን አስተሳሰባችንን አዛብቶ በማቅረብ ከህዝብ የመነጠል፣

3ለመቻቻልና ለመደማመጥ ፖለቲካ መጠናከር የተፈጠረ መድረክን ለራሱ የፖለቲካ ፍጆታ መጠቀም፣

4ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማት እንዳይኖሩ ጠንክሮ እየሰራ ያለ መሆኑ፣

5ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ለመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርአት መጠናከር ዋና ማሳያ የሆነውን የምርጫ ስርአት ማደናቀፍና ምርጫው ላይ ያለው ከለከት ያለፈ ስግብግብነት በብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ በምርጫ የስርአት ለውጥ ማምጣት እንደማይችል እንደማሳያ እንዲቆጠር ማድረጉ፣

6በተለያዩ ክፍለ ሃገር ባሉ አባላቶቹ ኢዴፓ እኮ የኛ ነው በማለት ወሬ በማሰራጨት የኛ የፓርቲ አባሎች ምክንያታዊ የፖለቲካ አቋሞቻቸውን በድፍረት ማራመድ እንዳይችሉ በማድረግ ከህብረተሰቡ የመነጠል ሴራ መስራት የመሳሰሉት ናቸው፡፡

ግን ይሄ ሁሉ ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶች የ3ኛ አማራጭነት ስልታችን ቢኖርበትም የማይናቅ ተጽዕኖ በፖለቲካው ምህዳር ውስጥ ለመፍጠር ችሏል፡፡ ከነዚህ በጎ የሆኑ ተጽዕኖዎች ውስጥም የተወሰኑ ማሳያዎችን ለመጥቀስ ካስፈለገ፣

1ፓርቲው ይሄን የምክንያታዊ ፖለቲካ አስተሳሰብ በስፋትና በጥራት በሸጠበት የ2002 ምርጫ ላይ በተናጥል ፓርቲዎች ድምጻቸው ቢታይና ቢቆጠር ብዙ የህዝብ ድምጽ በማግኘት ከኢህአዴግ ቀጥሎ ሁለተኛ ድምጽ ያገኘ ፓርቲ መሆን መቻሉ፣

21997 በኋላ በተከታታይ የተነዛበትን መሰረተ ቢስ አሉባልታ ቀንሶ አብዛኛው ህዝብ የፓርቲውን እውነት የማወቅና የመጠየቅ ሁኔታ እንዲጀምር ማስቻሉ፣

3አብዛኛው ፖለቲካውን በእውቀት ለሚገመግመው የህብረተሰብ ክፍል ፓርቲው ለነገዋ ኢትዮጵያ የሚሰራ ራዕይ ያለው ፓርቲ መሆኑን የመረዳትና ሃሳብና አጀንዳ ያለው ፓርቲ እንደሆነ የመገንዘብ ሁኔታ ማየት መጀመራችን፣

4በኢህአዴግ አባላት ሳይቀር ፓርቲው ከሌሎች ፓርቲዎች በተለየ ጽንፈኝነትንና የጥላቻ ፖለቲካን የሚጠየፍ ፓርቲ መሆኑን የማወቅና ለሌሎቹም የመመስከር ድፍረት ማየታችን፣

53ኛ አማራጭ ስልቶቻችን መገለጫ የሆኑ አስተሳሰባችንን የሚገልጹ ቋንቋዎች ሳይቀሩ በገዥው ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ሲገለጹና ሲነገሩ መስማታችን የመሳሰሉት ናቸው፡፡

ከላይ ተግዳሮቶቹንና ያገኘናቸውን የማይናቁ የአስተሳሰብ ተጽዕኖችን ስንመለከት ፓርቲያችንና አባላቱ ያለምንም መናወጽ የያዝነውን የ3ኛ አማራጭነት ስልታችንን በድፍረት ማራመድ ከቻልን ተጽዕኖውን በአጭር ግዜ መቀነስ ያገኘነውን ስኬት ደግሞ ከዚህ የበለጠ ከፍ ማድረግ የምንችል ይሆናል፡፡ በድፍረት ለዚህ አስተሳሰብ እንቅፋት የሆነውን የ1960ዎቹን አሮጌ የፖለቲካ አስተሳሰብ በመዋጋት፣ ኢምክንያታዊ አስተሳሰቦችን በመቃወም ጠንክረን ወደ ፊት የምንጓዝ ከሆነ የምንተክለውና የምናመጣው ለውጥ የማይቀለበስ ነው የሚሆነው፡፡ 3ኛ አማራጭነትን አሁን ባለው የፖለቲካ አስተሳሰብ የፖለቲካ ባህል ውስጥ ማካሄድ አልጋ በአልጋ ባይሆንም ለሃገራችንም ለመጭው ትውልድም በጎ ታሪክ ሰርቶ ከራስም በላይ መጭው ትውልድም የሚጠቀምበት የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር ከዚህ አስተሳሰብ ውጭ የተሻለ እንደሌለ ማመን እና ከበፊቱ በበለጠ ወኔ መነሳት አለብን፡፡ ሌሎች የሚያራምዱት አስተሳሰብንና የሚሄዱበት የጥላቻ ፖለቲካ ግዜያዊና ስሜታዊ የህዝብ ድጋፍ ከማስገኘት ውጭ ዘላቂ እና አስተማማኝ ለውጥ እንደማያመጣ ከልብ በመረዳት በዚህ ስልታችን እምነት በመያዝ አንገታችንን ቀና አድረግን መሄድ አለብን፡፡ በኔ እምነት ኢህአዴግን መቃወምና አምርሮ መጥላት ብቻውን የዴሞክራሲ ስርአት አፍቃሪ አያሰኝም ወይንም ከኢህአዴግ ለመሻል ማረጋገጫ አይሆንም፡፡ ይሄን እኛ የመንከተለውን የ3ኛ አማራጭነት እየጠሉና እየተቃወሙ እንደ ህዝብም እንደ ሃገርም ወደፊት መራመድና አስተማማኝ የስርአት ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል በድፍረት መመስከር መቻል አለብን፡፡ ይሄ አስተሳሰባችን አሸናፊ የሚሆነው ይሄን ምክንያታዊ የሆነ አስተሳሰብ ፓርቲያችን ወስጥ ባህል ማድረግ በመቻልና በቀጣይም የሌሎች የፖለቲካ ሃይሎችና የህዝቡ ማድረግ የቻልን ለታ ነው፡፡ ህዝቡም የመንግስት ለውጥ ናፋቂ ከመሆን ይልቅ ዘላቂ የስርአት ለውጥ ናፋቂ እንዲሆንና የስልጡን ፖለቲካ አራማጅና ትክክለኛ የለውጥ ሃይል እንዲሆን ካላስቻልን በስተቀር ለውጥ መምጣት እንደማይቻል ተረድተን ህዝቡን በለውጥ ሃይልነት ከጎናችን ማሰለፍ አለብን፡፡ ተቃዋሚዎችም ከእወደድ ባይነት ፖለቲካ ተላቀው፣ ለስልጡን ፖለቲካ ራሳቸውን ዝግጁ አድርገውና ጊዜውን የሚመጥን ፖለቲካ እንዲራመድ ለባለጊዜው ለዚህ ትውልድ አባላት የአመራርነት ሚናውን በመስጠት ያለፈ የፖለቲካ ሽንፈት ሂሳብ ማወራረጃ ወጣቱን ከማድረግ መቆጠብ እንዳለባቸው ተገቢውን መልዕክት ባገኘነው መድረክ በግልጽና በድፍረት ማስተላለፍ አለብን፡፡ መንግስትም ለመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርአት መጠናከር የራሱን ድርሻ በመወጣት በምክንያታዊነት ላይ በተመሰረተ ከጽንፈኝነት ፖለቲካ በመራቅ ትክክለኛና ዘላቂ ስርአት ለማምጣት የሚጥሩትን ሃይሎች ተገቢ ትኩረት በመስጠት፣ ተገቢውን አክብሮትና እውቅናም መቸር ካልቻለ አሱ በመጣበት መንገድ የሚመጡና በራሱ ቋንቋ ሊያናግሩት የሚችሉ ሃይሎች የሚጠናከሩበትን መንገድ እያጠናከረ እንደሆነ በማሳወቅ ከዚህ የበለጠ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት እንዳለበት ግልጽ ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ ይሄ አስተሳሰባችን የሌሎችም አስኪሆን ድረስ በአስተሳሰባችን ጠቃሚነት ላይ አርግጠኛ በመሆንና ይሄን ስልጡን ፖለቲካ በሃገራችን ላይ ለመትከል አባላት በውስጣችን የመቻቻል፣ የመደማመጥ፣ የመከባበር ዴሞክራሲያዊ ባህላችንን በፍጹም ፍቅር በማዳበርና በማጠናከር በየወንዙ የማይማማል ጓዳዊ ትስስር ማጠናከር አለብን፡፡ ለብሄራዊ መግባባት የሚያስችሉን ሃገራዊ ጉዳዮችን ጠንቅቀን በማወቅና በመረዳት በኢዴፓ መርሕ ላይ ጸንቶ የሚቆም ጠንካራ አባል በብዛት ለማፍራት መረባረብ አለብን፡፡ ያኔ ይሄ አስተሳሰብ የሁሉም የሆነ ለታ ድላችንን የምናጣጥም ይሆናል፡፡ በሃገራችን እውነተኛ የስርአት ለውጥ ማምጣት የሚችል አስተሳሰብ ይሄ እኛ የምንከተለው የ3ኛ አማራጭ የትግል ስልት ለመሆኑ ጥርጥር የለኝም፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ መሸነፍና ስልጣን መልቀቅም ካለበት ሊለቅ የሚችለው በዚህ አስተሳሰብ ተከታዮች ብቻ ነው ፡፡ ሊበቀለውና ሊያጠፋው የማይችል ዋስትናም ሊሰጠው የሚችል የትግል ስልት ይሄ የኛ ስልት ብቻ በመሆኑ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የ3ኛ አማራጭነት ስልት ለነገዋ ኢትዮጵያ የተሻለች መሆን ዋስትና ነው፡፡ ለሰለጠነ ፖለቲካም በር ከፋች ነው፡፡

አመሰግናለሁ፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter