Ethiopian Democratic Party

ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ

ቀን- 02/09/2011

Ethiopian Democratic Partyለክብርት ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ
አዲስ አበባ

ጉዳዩ፡- አቤቱታን ማቅረብን ይመለከታል
ቀደም ሲል በስራ ላይ የነበረው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በህግ ከተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት ውጭ በኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የብሔራዊ ምክር ቤት የስራ እንቅስቃሴ ላይ እገዳ መጣሉ ይታወቃል፡፡ በዚህም ምክንያት የፓርቲው ከፍተኛ የስልጣን አካል የሆነው የኢዴፓ ብሔራዊ ምክር ቤት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና በተነፈገበት ሁኔታ የፓርቲው ህልውና ሊቀጥል ስለማይችል በምርጫ ቦርዱ ህገ-ወጥ ጣልቃ ገብነት ምክንያት ኢዴፓ ህልውናውን እንዲያጣ መደረጉን ለህዝብ እና ለመንግስት በሐምሌ 29 ቀን 2010ዓ.ም በሰጠነው ጋዜጣዊ መግለጫ ማሳወቃችን ይታወቃል፡፡

ሆኖም በሀገራችን ከተከሰተው አዲስ የፖለቲካ ሂደት ለውጥ ጋር ተያይዞ ቀደም ሲል ምርጫ ቦርዱ በወሰደው እርምጃ ህጋዊነት ላይ በእርስዎ በኩል እንደ አዲስ የማጣራት ሂደት ተካሂዷል፡፡ ይህንን በእርስዎ በኩል የተካሄደውን የማጣራት ሂደት መሰረት በማድረግም በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መቋቋምን እየጠበቁ እንደሆነ በእርስዎ በኩል ተገልፆልናል፡፡

ነገር ግን – አንደኛ ይህ ጉዳይ በሂደት ላይ እያለና የኢዴፓ ከፍተኛ የስልጣን አካል የሆነው የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት በፓርቲው ህገ-ደንብ አንቀፅ 9.4.13 መሰረት ምንም አይነት ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የመዋሃድ ውሳኔ ባላስተላለፈበት ሁኔታ፤ ሁለተኛ በአሁኑ ወቅት እነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እያደረጉት የሚገኘው እንቅስቃሴ አዲስ ፓርቲ የማቋቋም እንጂ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህግ በሚፈቅደው መሰረት ነባር ፓርቲዎችን የማዋሃድ እንቅስቃሴ አለመሆኑ እየታወቀ (ይሄም የምርጫ ቦርድ ደብዳቤ በፃፈላቸው በግልፅ ተቀምጧል) ነገር ግን ኢዴፓ ከስሞ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር እንደተዋሃደ ተደርጎ ሰሞኑን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን እየተገለፀ ይገኛል፡፡

ይህ ድርጊት ፍፁም ህገ-ወጥ እና ህዝብን በተዛባ መረጃ የሚያሳስት በመሆኑ ክቡርነትዎ ትክክለኛውን መረጃ ህዝብ እንዲያውቀው የሚያደርግ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስዱ በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡

ከሰላምታ ጋር!

የኢዴፓ ብሔራዊ ምክር ቤት አባላት
ግልባጭ፤- ለመገናኛ ብዙሃን

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter