Ethiopian Democratic Party

የኢዴፓ ኦዲትና ኢንስፔክሽን አባላት በኢዴፓ ብሄራዊ ምክር ቤት ላይ የተጣለው እገዳ እንዲነሳ ጠይቁ

የኢዴፓ ኦዲትና ኢንስፔክሽን 3 አባላት በጋራ ለምርጫ ቦርድ ደብዳቤ አስገቡ፡፡ በደብዳቤያቸው በኢዴፓ ብሄራዊ ምክር ቤት ላይ የተጣለው እገዳ እንዲነሳ ጠይቀዋል፡፡ ሙሉ ደብዳቤያቸውን ከዚህ በታች አቅርቤዋለው፡፡
ቀን- 19/09/2011 ዓ.ም

ቀን- 19/09/2011 ዓ.ም
ለክብርት ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ
አዲስ አበባ

ጉዳዩ፤- ላለፉት አንድ ዓመታት የኢዴፓ ብሔራዊ ምክር ቤት ላይ ተጥሎ የቆየው እገዳ እንዲነሳ ስለመጠየቅ

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴ በፓርቲያችን መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ተጠሪነታቸው ለጠቅላላ ጉባዔ በሆነ ሶስት አባላት የሚቋቋም ነው፡፡

እኛም ስማችን ከታች የተዘረዘረውና በጠቅላላ ጉባዔ ተመርጠን እና በቦርዱም ህጋዊ እውቅና ተሰጥቶን ያለን 3 አባላት በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የፓርቲውን የብሔራዊ ምክር ቤት እንቅስቃሴ በመከታተልና በመቆጣጠር ለጠቅላላ ጉባዔው ሪፖርት የማድረግ ሃላፊነት ተሰጥቶናል፡፡ በዚህ መሰረት በፓርቲያችን ውስጥ ተፈጥሮ የነበረውን ችግርና የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት በፓርቲው ውስጥ የነበሩ የመርህ ጥሰት የፈጠሩ አመራሮችን ችግር ለመፍታት የሄደበትን ርቀት ሁሉ በቅርበት ተከታትለናል፡፡

በመጨረሻም የፓርቲውን ህገ-ደንብ ተከትሎ የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት ፍጹም የሆነ ህጋዊ ውሳኔ ወስኖ እነዚህ የመርህ ጥሰት የፈፀሙ አመራሮቹን ከሃላፊነት አንስቶ በሌላ ተክቷል፡፡ እኛም በቦታው በመገኘት የተወሰነው ውሳኔ የፓርቲውን ህገ-ደንብ ተከትሎ መከናወኑን አረጋግጠን ለምርጫ ቦርድ በደብዳቤ አሳውቀናል፡፡ ሆኖም በጊዜው የነበረው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተለይም አንድ ግለሰብ ቦርዱ ከተሰጠው ስልጣንና ሃላፊነት ውጭ የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት የወስናቸውን ውሳኔዎች እኛም በአካል ተገኝተን ያረጋገጥነውን ውሳኔ በፍፁም እንደማይቀበል ገለፀ፡፡

ይባስ ብሎ የብሔራዊ ምክር ቤቱን ስብሰባ ዶ/ር ጫኔ ካልጠሩት በስተቀር ብሔራዊ ምክር ቤቱ የሚወስናቸውን ማናቸውም ውሳኔዎች እንደማይቀበል በመግለፅ በብሔራዊ ምክር ቤቱ ላይ እገዳ ጣለ፡፡ ከጠቅላላ ጉባዔው ቀጥሎ የፓርቲያችን ከፍተኛው የስልጣን አካል የሆነው የብሔራዊ ምክር ቤት በዚህ እገዳ ውስጥ ሆኖ የፖለቲካ ስራ መስራት ስለማይችል ሃምሌ 29 ቀን 2010 ዓ.ም የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፓርቲው የውስጥ ጉዳይ ገብቶ ኢዴፓን እንዳፈረሰው ለመንግስት እና ለህዝብ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ ከዚህ መግለጫ በኋላ የመንግስት አካላት በተለይ ዶ/ር አብይ የጉዳዩን አሳሳቢነት ተረድተው ጉዳችን ተጣርቶ ውሳኔ እንዲሰጠን ከእርስዎ በፊት ለነበሩት የቦርዱ ሰብሳቢ መመሪያ በመስጠት ጉዳያችን እንደገና እየታየ ነበር፡፡ እርስዎም ከመጡ በኋላ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት እየተከታተሉ እንደሆነ እና የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ግን የቦርዱን መቋቋም እየጠበቁ መሆኑን ገልፀው የፓርቲያችን አመራሮች ቀጠሮ ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

ነገር ግን ይሄ ሁኔታ እልባት ሳያገኝ ፓርቲው እንደከሰመ እና ከኢዜማ ጋር እንደተዋሃደ ተደርጎ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እየተገለፀ ነው፡፡ አንደኛ- ከሃምሌ ወር 2010 ዓ.ም ጀምሮ የፓርቲው ብሄራዊ ም/ቤት ተሰብስቦ ውሳኔ ወስኖ እንደማያውቅ፡፡ ሁለተኛ- በፓርቲያችን መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 10 በዝርዝር በተሰጠን ስልጣን መሰረት የኦዲት እና ኢንስፔክሽን አበላት ባልተገኘንበት እና ባልታዘብንበት፣ ለጉባኤው የሂሳብ እና የስራ ኦዲት ሪፖርት ባላደረግንበት፣ የጠቅላላ ጉባኤ አባላቱ የኢዴፓ አባላት ይሁኑ አይሁኑ ባላረጋገጥንበት ሁኔታ ተደረገ የተባለው ጠቅላላ ጉባኤ ህገ-ወጥ ነው፡፡ ሶስተኛ- በፓርቲያችን መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 9.4.2 መሰረት የብሔራዊ ምክር ቤቱ የጠቅላላ ጉባዔውን መደበኛ፣ ልዩና አስቸኳይ ስብሰባዎችን ይጠራል ቢልም የብሔራዊ ምክር ቤቱ ያልጠራው ጠቅላላ ጉባኤ በመሆኑ ፍፁም ህገ-ወጥ ነው፡፡ አራተኛ- በፓርቲያችን መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 9.4.13 መሰረት ብሔራዊ ምክር ቤቱ ከመሰልና አቻ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ሊኖር ስለሚገባ ማናቸውም የትግል ግንኙነት ላይ መመሪያ እና ውሳኔ ይሰጣል ቢልም ግንኙነቱም ሆነ የውህደቱ ውሳኔ በጥቂት ግለሰቦች ፈቃደኝነት ብቻ የተፈጸመ ድርጊት በመሆኑ ፍጹም ተቀባይነት የለውም፡፡ ስለሆነም ክቡርነትዎ ፓርቲያችን ኢዴፓ አደረገ የተባለው እና በጠቅላላ ጉባዔው ተወሰነ የሚባለው ውሳኔ ሁሉ ፍፁም የፓርቲያችንን ህገ-ደንብ ያልተከተለ እና ህገ-ወጥ በመሆኑ የፓርቲያችንን ደንብ በመመርመር አስቸኳይ መፍትሄ እንድትሰጡንና ህጋዊው የኢዴፓ ብሔራዊ ምክር ቤት የተጣለበት እገዳ እንዲነሳ ስንል ከታች ስማችን የተዘረዘረው የኢዴፓ ኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴ አባላት እንጠይቃለን፡፡
ከሰላምታ ጋር!


የኦዲትና ኢንስፔክሽን አባላት
1ኛ- አቶ የኔመንግስት ጌታቸው-
2ኛ- አቶ ተስፋ መስፍን –
3ኛ- አቶ ሰለሞን ሰንደቁ-
ግልባጭ፤- ለመገናኛ ብዙሃን

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter