Abronet

በቅድሚያ ኮሮናን ማሸነፍ፣ ቀጥሎ ወደ አገራዊ የምክክር ሂደት መሸጋገር!

ከአብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ሊካሄድ ታስቦ የነበረው አገራዊ ምርጫ በታሰበበት ጊዜ መካሄድ እንደማይችል አሳውቋል፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በጉዳዩ ላይ ውሳኔ እንዲሰጥበት ሃሳብ ማቅረቡን ገልጿል፡፡

ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አገራዊ ምርጫው ዘንድሮ ማለትም በ2012 ዓ.ም መካሄድ የማይችል መሆኑን ማሳወቁ በሁለት ምክንያቶች ተገቢ ነው ብሎ አብሮነት ያምናል፡፡ አንደኛ- የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እየተደረገ ባለው ጥረት ህዝቡ ትኩረቱ ሳይከፋፈል የሚጠበቅበትን ርብርብ በወረርሽኙ ላይ እንዲያደርግ የምርጫው አለመካሄዱ የማይተካ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ ሁለተኛ- በአሁኑ ወቅት በሁለንተናዊ መልኩ ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጁ ያልሆነችው አገራችን በቂ ጊዜ አግኝታ የተሟላ ዝግጅት እንድታደርግ የምርጫው መራዘም ዕድል ይፈጥራል፡፡ በእነዚህ ሁለት መሰረታዊ ምክኒያቶች አብሮነት የምርጫው ጊዜ መራዘሙን ይደግፋል፡፡

እንደሚታወቀው ከብዙ ወራቶች በፊት ጀምሮ አብሮነት የምርጫው ጊዜ እንዲራዘምና የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ሲጠይቅ ቆይቷል፡፡ ምርጫውን ለማራዘም የሚያስችል የህግ ድንጋጌ እንደሌለ ተደርጎ ከመንግስትና ከአንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ሲቀርብ የነበረው የመከራከሪያ ሃሳብም አገሪቱ ከምትገኝበት ልዩ ሁኔታ አንፃር ትክክል እንዳልሆነ አብሮነት ሲከራከር ቆይቷል፡፡ የአገሪቱ ህግ የማይፈቅድ ቢሆንም ” ለአገርና ለህዝብ ደህንነት ሲባል ̋ ምርጫው በአሁኑ ወቅት እንዲራዘም መደረጉ የሚያሳየውም ” ከገባንበት አገራዊ ቀውስ ለመውጣት በምናደርገው ጥረት ህግ እንቅፋት ሊሆንብን አይገባም ” የሚለው የአብሮነት አቋም ምን ያህል ትክክለኛ እንደነበረ ነው፡፡ ይህ አገራችን በአሁኑ ወቅት የገጠማት ችግር ልዩ ባህሪ ያለው በመሆኑ ሊፈታ የሚችለው በመደበኛ አሰራርና ህግ ሳይሆን መደበኛ ባልሆነ (Extra-Constitutional) የፖለቲካ ድርድርና ሂደት ነው የሚለው የአብሮነት አቋም ትናንት ብቻ ሳይሆን ዛሬም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

ቀደም ሲል ̋ ምርጫውን ለማራዘም የሚያስችል ህግ የለም ̋ እየተባለ ይቀርብ የነበረው ክርክር ከፖለቲካ ሳይሆን ከህግ አንፃር የሚያስኬድ ቢሆንም ከወቅቱ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ጋር በተያያዘ ግን ይህ የህግ መከራከሪያም ሙሉ በሙሉ ተዘግቷል፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በመበተን ወይም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በማዎጅ ምርጫን በህጋዊ መንገድ ለማራዘም እንደሚቻል በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ ወገኖች እየቀረበ ያለው ሃሳብ ፈፅሞ ህጋዊ መሰረት የሌለው መሆኑን ህዝቡ ሊገነዘብ ይገባል፡፡ ይህንን የምንለው በሚከተሉት አራት ምክንያቶች ነው፡፡

1. በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 58/3 መሰረት የአገሪቱ መንግስት የስራ ዘመን አምስት ዓመት ብቻ ነው፡፡ ይህንን የመንግስት እድሜ ለአንድም ቀን እንኳ ለማራዘም የሚያስችል ወይም የሚፈቅድ ምንም ዓይነት ድንጋጌ በህገ-መንግስቱ ውስጥ የለም፡፡

2. በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 60፣ ከተራ ቁጥር 1 እስከ 5 ድረስ ከተዘረዘሩት ድንጋጌዎች በግልፅ እንደሚታየው ምርጫ የሚካሄድበትን ጊዜ ለማራዘም ተብሎ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ለመበተን የሚያስችል ምንም ዓይነት ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌ የለም፡፡ ምክር ቤቱን ለመበተን የሚቻለው በአምስት ዓመቱ የመንግስት የስልጣን እድሜ ክልል ውስጥ በስልጣን ላይ የሚገኘው ገዥ ፓርቲ መንግስት ሆኖ ለመቀጠል የማያስችለው አስገዳጅ ሁኔታ ሲገጥመው ብቻ ነው፡፡ ይህ መብት ለመንግስት የተሰጠው በህግ የተፈቀደለትን የአምስት ዓመት ጊዜ ለመጨረስ እንዲችል ነው እንጂ ከአምስት ዓመቱ ጊዜ ውጭ ለአንድም ቀን ዕድሜውን ለማራዘም መብት አልተሰጠውም፡፡

3. በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 93/1፣ ሀ እና ለ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊታወጅባቸው የሚችል ጉዳዮች በግልፅ ተዘርዝረው ተቀምጠዋል፡፡ ” ምርጫን ለማራዘም ሲባል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊታወጅ ይችላል” የሚል ድንጋጌ በእነዚህ ዝርዝር ድንጋጌዎች ውስጥ አልተካተተም፡፡ በህገ-መንግስቱ መሰረት የምርጫውን ቀን ለማራዘም ተብሎ ሊታወጅ የሚችል ምንም ዓይነት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የለም፡፡

4. በአገሪቱ ህገ-መንግስት መሰረት በመላው አገሪቱ ምርጫን ለማስፈፀም ብቸኛ ስልጣን የተሰጠው የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ነው፡፡ ቦርዱ ምርጫውን በዚህ ዓመት ማካሄድ እንደማይችል ባሳወቀበት ሁኔታ ህገ-መንግስታዊ መፋለስ የሚገጥመው ፌደራል መንግስቱ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የአገሪቱ ክልላዊ መንግስታት ናቸው፡፡ ስለሆነም ችግሩ አገራዊ የፖለቲካ መፍትሄ በመፈለግ እንጂ ከዚህ በኋላ በመደበኛ የህግ አግባብ ሊፈታ የሚችልበት ዕድል የለውም፡፡ ምርጫ ቦርድ ምርጫ ማካሄድ አልችልም ባለበት ሁኔታም የትኛውም የአገሪቱ ክልል በተናጠል ምርጫ የማካሄድ ህገ-መንግስታዊ መብት አይኖረውም፡፡

በእነዚህ ተጨባጭ ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎች መሰረት ከአሁን በኋላ የምርጫውን መራዘም በተመለከተ ከህግ አንፃር መከራከሪያ ማቅረብ የሚቻልበት ዕድል ሙሉ በሙሉ ዝግ ሆኗል፡፡ ከአሁን በኋላ ምርጫው መቼና እንዴት ይካሄድ ? የሚለው ጥያቄ ሊመለስ የሚችለው አብሮነት ደጋግሞ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ከመደበኛ አሰራርና ከህግ ድንጋጌ ውጭ በሆነ (Extra-Constitutional) የፖለቲካ ድርድርና ውሳኔ ነው እንጂ ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌን መሰረት አድርጎ ሊወሰንበት የሚችል ምንም ዓይነት ቀዳዳ የለም፡፡

በአብሮነት እምነት ከአሁን በኋላ – ለ27 ዓመታት በተጭበረበረ ምርጫና አፈና፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ” በአሻጋሪነት ” ስም ስልጣን ይዞ አገሪቱን በአግባቡ መምራት የተሳነው የትናንቱ ኢህአዴግ፣ የዛሬው ብልፅግና ፓርቲ ከእንግዲህ በማንኛውም ሌላ ስምና ሰበብ በስልጣን ላይ የመቀጠል ዕድል ሊሰጠው አይገባም፡፡ ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ምንም ዓይነት ፖለቲካዊም ሆነ ህጋዊ ድጋፍም የለውም፡፡

በአጠቃላይ- በአንድ በኩል አገራችን ከእንዲህ ዓይነት ህገ-መንግስታዊ መፋለስ (Constitutional Crisis ) እንዴት ትውጣ? ኮሮና ቫይረስ በዜጎች ጤናና ህይወት ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት መሻገር ከቻልን በኋላስ በአገራችን ሊከሰት የሚችለውን ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዴት ልንቋቋመው እንችላለን ? የሚሉትን ጥያቄዎች፣ በሌላ በኩል ደግሞ በቂ ጊዜ አግኝተንና በቂ የሚባል ዝግጅት አድርገን ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ አካሂደን እንዴት ወደ መዋቅራዊ ዴሞክራሲ ልንሸጋገር እንችላለን ? የሚለውን ወቅታዊ ጥያቄ በብቃት ለመመለስ አብሮነት እያቀረበው የሚገኘው ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት የማቋቋም ጥያቄ ከመቼውም ጊዜ በላይ አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑ ግልፅ እየሆነ መጥቷል፡፡ ነገር ግን ምን ዓይነት የሽግግር መንግስት ይቋቋም ? የሽግግር መንግስቱ እንዴትና በማን ሊቋቋም ይችላል ? የሽግግር መንግስቱ ዋና ሃላፊነትና ተግባርስ ምን ይሆናል ? ዕድሜውስ ምን ያህል ጊዜ መሆን ይገባዋል ? የሚሉት ጥያቄዎች በመንግስት ብቻ ሳይሆን ሁሉን አቀፍ በሆነ የአገራዊ ምክክር ሂደት ( National Dialogue ) መወሰን ይኖርበታል ብሎ አብሮነት ያምናል፡፡ ስለሆነም-

1. በአሁኑ ወቅት አንገብጋቢውና ቀዳሚው የአገራችን ችግር የኮሮና ቫይረስን መከላከልና መቆጣጠር መሆን ስለሚገባው የፖለቲካውን ጉዳይ ለጊዜው ወደጎን አስቀምጠን ሙሉ ትኩረታችንን ወረርሽኙን በመከላከልና በመቆጣጠር ስራ ላይ ማድረግ እንዳለብን፤

2. ወረርሽኙን በብቃት መከላከላችንን እርግጠኞች ከሆንን በኋላ ግን በፍጥነት ሁሉን አቀፍ አገራዊ የምክክር ሂደት ( National Dialogue ) መጀመርና አገራችንን ወደፊት ሊገጥማት ከሚችል ከፍተኛ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አደጋ መታደግ የምንችልበት ሁኔታ እንዲመቻች አብሮነት ጥሪውን ያቀርባል፡፡

አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት (አብሮነት)

መጋቢት 27 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter