ስልጣንን በህገ-ወጥ መንገድ ለማራዘም የሚደረግ ሙከራ በአስቸኳይ ይቁም!

ከ አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት) የተሰጠ መግለጫ!

አገራችን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ሆና የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረገች በምትገኝበት በአሁኑ ወቅት ገዥው ብልፅግና ፓርቲ ግን የስልጣን ዘመኑን በህገ-ወጥ መንገድ ለማራዘም የሚያስችለውን ጥረት ለህዝብ ይፋ ባልሆነ መንገድ እያደረገ ስለመሆኑ መረጃዎች እየደረሱን ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ በአገሪቱ ህገ-መንግስት ከተሰጠው ስልጣንና መብት ውጭ በሶስት አማራጮች ስልጣኑን ለማራዘም እየሞከረ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡
እነዚህ አማራጮችም፤-

1. በዓመቱ መጨረሻ ላይ የአገሪቱ ፓርላማ እንዲበተን ማድረግና በ6ወር ጊዜ ውስጥ አገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ ማድረግ፤
2. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንደገና በማራዘም የመንግስትን የስራ ዘመን ለማራዘም መሞከር፤
3. የአገሪቱን ህገ-መንግስት በማሻሻል የመንግስትን የስራ ዘመን ለተወሰነ ጊዜ ማራዘም የሚሉ ናቸው፡፡ ከእነዚህ አማራጮች ውስጥ በየትኛው መንገድ የመንግስትን ስልጣን ለማራዘም እንደሚቻልም ገዥው ፓርቲ ከራሱ መዋቅሮችና በዙሪያው ከሚገኙ የህግ ባለሙያዎች ጋር እየመከረ እንደሆነ ታውቋል፡፡

አብሮነት ከዚህ ቀደም ደጋግሞ ለመግለፅ እንደሞከረው ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም በኋላ ለአንድም ቀን በስልጣን ላይ የሚገኘውን መንግስት ዕድሜ ለማራዘም የሚያስችል ምንም ዓይነት ድንጋጌ በአገራችን ህገ-መንግስት ውስጥ የለም፡፡ በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 58/3 እና አንቀፅ 72/3 መሰረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስራ ዘመን አምስት ዓመት ብቻ ስለመሆኑ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ወይም ምርጫ ማካሄድ የማይቻልበት አስገዳጅ ሁኔታ ሲገጥም የመንግስትን ዕድሜ እንዴት ማራዘም እንደሚቻል ህገ-መንግስቱ ምንም ዓይነት ድንጋጌ አላስቀመጠም፡፡ ስለሆነም ብልፅግና ፓርቲ እንዲህ ዓይነት ህገ-መንግስታዊ ቀውስ እንዲከሰት ምክንያት የሆኑትን የህገ-መንግስቱን አርቃቂዎች እና ለህገ-መንግስቱ ክፍተት መታየት ምክንያት የሆነውን ኮሮና ቫይረስን “ከመርገም” ውጭ በህጋዊ መንገድ የስልጣን ዘመኑን ለአንድም ቀን የሚያራዝምበት ምንም ዓይነት መብትና ስልጣን በህገ-መንግስቱ አልተሰጠውም፡፡
በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 60 ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በትነው በ6ወር ጊዜ ውስጥ ምርጫ እንዲያካሂዱ ስልጣን የተሰጣቸውም በህገ-መንግስቱ የተቀመጠውን አምስት ዓመት የመንግስት የስልጣን ዘመን ለመጨረስ ነው እንጂ ከአምስት ዓመት በላይ የመንግስትን የስራ ዘመን ለማራዘም አይደለም፡፡ እንዲያውም በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 60/1 ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ድጋሜ ምርጫ መካሄድ የሚችለው በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የስራ ዘመን ከመጠናቀቁ በፊት ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌ በህግ የተሰጠን የስራ ዘመን ለማጠናቀቅ ከመቻል ጋር እንጂ የስራ ዘመንን ከማራዘምና የመንግስት የስራ ዘመን ካለቀ በኋላ ከሚካሄድ ምርጫ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም፡፡

በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 93/1፣ ሀ እና ለ ላይ በግልፅ እንደተደነገገውም የመንግስትን የስልጣን ዘመን ለማራዘም ተብሎ ሊታወጅ የሚችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የለም፡፡ አሻሚና አከራካሪ ባልሆነ መንገድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለምን ዓይነት ጉዳዮች ሊታወጅ እንደሚችል ህገ-መንግስቱ በዝርዝርና በግልፅ ስላስቀመጠ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማዎጅ ስልጣኑን ለአንድም ቀን ለማራዘም የሚያስችለው ህጋዊ መብትና ስልጣን የለውም፡፡
እንደ ሶስተኛ አማራጭ እየታዬ ያለው ህገ-መንግስቱን አሻሽሎ የመንግስትን የስራ ዘመን ለማራዘም መሞከርም ህጋዊነትን የተከተለ አሰራር አይደለም፡፡ አንድ በስልጣን ላይ የሚገኝ መንግስት የራሱን የስልጣን ዘመን ለማራዘም ሲል በስራ ላይ ያለውን ህገ-መንግስት የሚያሻሽል ከሆነ፣ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት እንደ አንዳንድ አምባገነን የአፍሪካ መሪዎች በአለም ፊት መሳቂያ እና መሳለቂያ የሚያደርግ የአምባገነኖች ድርጊት እንጂ ህጋዊ አሰራር ተደርጎ ሊቆጠር አይችልም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የስልጣን ዘመንን ለማራዘም ሲባል ህገ-መንግስትን ለማሻሻል የመሞከር ዕርምጃም ከህግ መኖርና አስፈላጊነት መሰረታዊ መርህ ጋር የሚጋጭ ህገ-ወጥ ተግባር ነው፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ ሂደትም ማንኛውም የፖለቲካ ሃይል የህዝብ ቅቡልነት ሊያገኝ አይችልም፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ከባድ አገራዊ ጉዳይ አሳታፊና ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ለመወሰን መሞከርም አገራችን በአሁኑ ወቅት ምን ያህል ሁለንተናዊ የህልውና ፈተና ውስጥ እንደምትገኝ አለመረዳት ነው፡፡ ይህም እንደተለመደው የገዥውን ፓርቲ ከአገር ጥቅም ይልቅ የራሱን ስልጣን የማስቀደም ሃላፊነት የጎደለው ፍልጎት የሚያሳይ ነው፡፡

ስለዚህ በማወቅም ይሁን ባለማዎቅ የህገ-መንግስቱ አርቃቂዎች በሰሩት ስህተት እና በኮሮና ቫይረስ ወደ አገራችን መግባት ምክንያት በአሁኑ ወቅት በአገራችን የመንግስት የስራ ዘመንን አስመልክቶ ህገ-መንግስታዊ ቀውስ (Constitutional Crisis) መፈጠሩን አምኖ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ህገ-መንግስታዊ ቀውስ በአንድ አገር ሲፈጠር ደግሞ ለችግሩ መፍትሄ መስጠት የሚቻለው በመደበኛ የህግ አሰራር ሳይሆን ከመደበኛ የህግ አሰራር ውጭ (Extra Constitutional) በሆነ መንገድ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን መፍትሄ ለመስጠትም በተለየ ሁኔታ በህግ መብት የተሰጠው የፖለቲካ ፓርቲ ወይም መንግስታዊ ተቋም ስለሌለ የተፈጠረውን ህገ-መንግስታዊ ቀውስ እንዴት እንፍታው? በሚለው ጥያቄ ተነጋግሮ የመፍትሄ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ሁሉን አቀፍ አገራዊ የምክከር ሂደት (National Dialogue) መጥራት ያስፈልጋል፡፡ ከመስከረም 30/2013 ዓ.ም በኋላ በአገራችን በህጋዊም ይሁን በይስሙላ ምርጫ የተመረጠ መንግስት ስለማይኖር የወደፊቱን የአገሪቱን ዕጣ-ፈንታ በመወሰን ረገድ ገዥው ብልፅግና ፓርቲ ከማንኛችንም በአገሪቱ ከምንገኝ ፓርቲዎች የተለዬ መብትና ስልጣን ስለሌለው በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት ውሳኔ ብቻውን መዎሰን አይችልም፡፡ ገዥው ፓርቲ ይህንን ማድረግ ከሞከረ በአገራችን ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ እና ትርምስ ሊፈጠር እንደሚችል ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
ስለሆነም፤-

1ኛ. በአሁኑ ወቅት ዋናውና ቀዳሚው ትኩረታችን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን መከላከልና መቆጣጠር መሆን ስላለበት ቢያንስ እስከ ነሃሴ መጨረሻ 2012 ዓ.ም ድረስ ብልፅግና ፓርቲ የተፈጠረውን ህገ-መንግስታዊ ቀውስ በተመለከተ ምንም ዓይነት አጀንዳ ይዞ እንዳይነጋገርም ሆነ የተናጠል ውሳኔ እንዳያስተላልፍ፤
2ኛ. የትግራይ ክልላዊ መንግስት በዘንድሮው ዓመት በተናጠል ምርጫ ለማካሄድ ማሰቡ ህገ-መንግስታዊ ውሳኔ አይደለም፡፡ በአገሪቱ ህገ-መንግስት መሰረት በፌደራልም ሆነ በክልል ደረጃ ምርጫ ለማካሄድ ብቸኛ መብት የተሰጠው የኢትዮጵያ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ መሆኑን በመገንዘብ የትግራይ ክልላዊ መንግስትም ሆነ ህውሃት ከዚህ ዓይነቱ ህገ-ወጥ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ፤
3ኛ. ብልፅግና ፓርቲ ይህንን አጀንዳ በሚመለከት በድብቅ የሚፈፅማቸውን ተግባራት ሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በንቃት እንዲከታተሉ፣ ገዥው ፓርቲ ይህንን አጀንዳ በተመለከተ ህገ-ወጥ እርምጃ መውሰዱን የሚቀጥልበት ከሆነም ተቃዋሚ ፓርቲዎች አመቺ የመገናኛ መንገድ ፈጥረው በአስቸኳይ መመካከር እንዲችሉና በጉዳዩ ላይ የራሳቸውን አቋም እንዲይዙ፣ከዚህ በኋላም በአገራችን ጉዳይ አንዳችን ጋባዥ ሌላችን ተጋባዥ የምንሆንበት ምክንያት እንደሌለ ተገንዝበን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር የምናደርገው ማንኛውም ግንኙነትና ድርድር በእኩልነት መንፈስ ብቻ እንዲሆን የሚያስችል አቋም እንድንይዝ፤
4ኛ- የኢትዮጵያ ህዝብ ለአለፉት 29 ዓመታት በአፈናና በይስሙላ ምርጫ በስልጣን ላይ የኖረው ገዥው ፓርቲ ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም በኋላ ለአንድም ቀን በስልጣን ላይ ሊቀጥል የሚችልበት ምንም ዓይነት ህጋዊ መብት የሌለው መሆኑን ተገንዝቦ በህገ-ወጥ መንገድ ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚደረገውን ጥረት አጥብቆ እንዲቃወም፣ መቃወምም ብቻ ሳይሆን የገዥውን ፓርቲ ህገ-ወጥ እርምጃ በጠንካራ ህጋዊና ሰላማዊ ትግል ለማስቆም እንዲዘጋጅ አብሮነት ጥሪውን ያቀርባል፡፡

አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት)
ሚያዚያ 21 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter