ሁሉን አቀፍ አገራዊ የውይይት መድረክ አሁኑኑ!

በተለመደ መንገድ የተለየ ውጤት ላይ መድረስ አይቻልም!
ሁሉን አቀፍ አገራዊ የውይይት መድረክ አሁኑኑ!

ከአብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት) የተሰጠ መግለጫ

በዚህ ሣምንት በአገራችን የተለያዩ አበይት የፖለቲካ ጉዳዮች ተስተናግደዋል፡፡ ከእነዚህ አበይት ክንውኖች መካከል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ንግግር፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ከሃላፊነት መልቀቅ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገደብ ለሌለው ጊዜ የመንግስትን የስልጣን ዘመን የማራዘም ውሳኔና የደቡብ ክልል የዞኖች የ “ ክልልነት ” ጥያቄ ይገኙበታል፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር አገሪቱ በገጠሟት አሳሳቢ ጉዳዮች ዙሪያ አሳማኝ መፍትሄ ከማመላከት ይልቅ የተለመደውን የተጋነነ የ“ስኬት” ትርክት ሲያቀርቡ ውለዋል፡፡ በዚህም ህዝቡ ከፍተኛ ተስፋ ጥሎበት የነበረው የለውጥ ሂደት ህወሃት/ኢህአዴግ ወደ ብልጽግና/ኢህአዴግ ከመሸጋገሩ የተለየ ትርጉም እንደሌለው ታይቷል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግስትን የስልጣን ዘመን ያለገደብ ለማራዘም የሰጠው ውሳኔም በአገራችን የህግ የበላይነት ዛሬም እንደትናንቱ ቦታ የሌለው መሆኑን አሳይቶናል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በማንኛውም ህግ ያልተሰጠውን መብት ተጠቅሞ በስልጣን ላይ የሚገኘውን መንግስት የስልጣን ዘመን ገደብ ለሌለው ጊዜ እንዲራዘም የሰጠው ውሳኔ አገራችን ምን ያህል ወደ ለየለት አንባገነናዊ ስርዓት እየተሸጋገረች ስለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ በድንገት ከሃላፊነታቸው መልቀቃቸው እና ስለመልቀቃቸው ያቀረቡት በሃይለ ቃል የተሞላ ምክንያት በብልፅግና እና በህውሃት መካከል ያለው ልዩነት እና ቅራኔ የአገርን ህልውና በሚፈታተን መጠን ምን ያህል አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰ በግልፅ ያሳያል፡፡
በደቡብ ክልል የሚገኙ ዞኖች ያነሷቸውን የክልልነት ጥያቄ በሚመለከት ተደረጉ የተባሉ ጥናቶች እና እየቀረቡ ያሉ የመፍትሄ ሃሳቦች የክልሉን ህዝብ ታሪካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትስስር እና አንድነት በአግባቡ ያላገናዘቡና ዛሬም እንደትናንቱ መፍትሄዎች ከላይ ወደታች በህዝብ ላይ የሚጫኑ መሆኑን በግልፅ የሚያሳይ ነው፡፡
በአጠቃላይ ወቅታዊውን የአገራችንን ሁኔታ በጥልቀት የገመገመው አብሮነት የሚከተሉትን አቋሞች ወስዷል፡፡

1- የሰሞኑ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ የሁለት ዓመቱ የለውጥ ሂደት መክሸፍ የመጨረሻ ማህተም ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ከእንግዲህ ከብልፅግና ፓርቲ ዓመራር ከ27 ዓመቱ አንባገነናዊ ስርዓት የተለየ አዲስ የሚጠበቅ ለውጥ የለም፡፡

2- ይህ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ብልፅግና ፓርቲ ላለፉት ሁለት ዓመታት ለህዝብ ከገባው ቃል-ኪዳን እና ከጠየቀው ይቅርታ በተፃራሪ አገሪቱን ወደ አደገኛ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ የሚያስገባ ውሳኔ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

3- በዚህ ውሳኔ መሰረት አገሪቱ ወደፊት ለሚያጋጥማት ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ተጠያቂዎቹ- ብልፅግና ፓርቲ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የህገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔና ብልፅግና ፓርቲ በህገ-ወጥ መንገድ ስልጣኑን ያለገደብ እንዲያራዝም ድጋፋቸውን የሰጡ የፖለቲካ ሃይሎች ናቸው፡፡

4- ከአሁን በኋላ ብልፅግና ፓርቲ በስልጣን ላይ የሚቀጥለው በህዝብ ይሁንታ እና በህጋዊነት ሳይሆን በኃይል እና በአፈና መንገድ ብቻ ነው፡፡

5- ህዝቡ ብልፅግና ፓርቲ ወደለየለት አንባገነናዊ ሃይልነት መቀየሩን ተገንዝቦ አገሪቱን ከህልውና አደጋ ለመታደግ ህጋዊና ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ከመስከረም 25/2013 ዓ.ም በፊት የአገራችንን የወደፊት እድል ለመወሰን የሚያስችል ሁሉን አቀፍ አገራዊ የምክክር መድረክ በአስቸኳይ እንዲጠራ የሚያስችል ጫና ህዝቡ በመንግስት ላይ እንዲያሳድር አብሮነት ጥሪውን ያቀርባል፡፡

👉ኮሮና የሁላችንን ርብርብ የሚጠይቅ የቅድሚያ ትኩረት ነው!
👉የፖለቲካ ልዩነታችን ለታላቁ የህዳሴ ግድባችን በምናደርገው ጥረት አይከፋፍለንም!

አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (##አብሮነት)
ሰኔ 4 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter