የአምንስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት ልዩ ትኩረት ያሻዋል!

የአምንስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት ልዩ ትኩረት ያሻዋል!

ከአብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት) የተሰጠ መግለጫ

አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት) በአሁኑ ወቅት በስልጣን ላይ የሚገኘው መንግስት በአገሪቱ ሰላምና የህግ የበላይነት ማስከበር እንዳልቻለና በዚህም ምክንያት የዜጎች ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች በከፍተኛ ደረጃ እየተጣሱ እንደሚገኙ በተደጋጋሚ መግለፁ ይታወሳል፡፡ በቅርቡ የወጣው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም ሆነ ሰሞኑን በአምንስቲ ኢንተርናሽናል የወጣው አስደንጋጭ ሪፖርት ይህንኑ ዕውነታ በከፍተኛ ደረጃ የሚያጠናክር ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

በስልጣን ላይ የሚገኘው መንግስት እነዚህ ሁለት የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ለአዎጧቸው መግለጫዎች ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ማጣራትና የዕርምት ዕርምጃ ለመውሰድ ከመጣር ይልቅ ባለፈው 27 ዓመት ሲሆን እንደታየው ሪፖርቶቹን በጭፍን ማጣጣል እና ማውገዝን ሲመርጥ ታይቷል፡፡ ይህ የሚያሳየን ከአሁን ቀደም ደጋግመን ለመግለፅ እንደሞከርነው የወቅቱ መንግስት በይዘት ካለፈው የ27 ዓመት ስርዓት ያልተለየና አካሂደዋለው የሚለው የለውጥ ሂደትም የከሸፈ መሆኑን ነው፡፡

ይህ ሁኔታ ተገቢ ትኩረት ሳይሰጠውና አስተማማኝ የዕርምት እርምጃ ሳይወሰድ የሚቀጥል ከሆነ አገራችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ከፋ የፖለቲካ ቀውስ ልትገባ ትችላለች የሚል ስጋት አለን፡፡ ስለሆነም መንግስት በእነዚህ ሁለት የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የቀረበውን ሪፖርት በአስቸኳይ የሚያጣራ ገለልተኛ ኮሚሽን እንዲያቋቁም፣ ገለልተኛ ኮሚሽኑ የሚደርስበትን ውጤት መሰረት አድርጎም ተገቢውን የዕርምት ዕርምጃ እንዲወስድ፣ በዜጎች ላይ ወንጀል የፈፀሙ ግለሰቦችና ተቋማትም በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑና የማጣራት ሂደቱንም ለህዝብ በግልፅና በይፋ እንዲያሳውቅ አብሮነት በአፅንኦት ይጠይቃል፡፡

አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት)
ግንቦት 23 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ

ቅድሚያ ትኩረት፤
ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል!
ህዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ!
ውጤታማ የፖለቲካ ሽግግር ለማካሄድ!

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter