መንግስት የአገሪቱን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ብቻውን የመፍታት አቅም የለውም!

ከአብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት) የተሰጠ መግለጫ

አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት) ባለፉት ጊዜያት የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታዎች እየተከታተለ እና እየገመገመ አቅጣጫ የሚያሳዩ መግለጫዎችን ሲያወጣ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ አብሮነት በነዛ ሁሉ ጊዜያት የለውጥ ሂደቱ ሃዲዱን እየሳተ መሆኑን እና አገራችን የህልውና አደጋ ውስጥ ከመውደቋ በፊት ተጨባጭ የመፍትሄ እርምጃዎች እንዲወሰዱ አማራጭ መፍትሄ ጭምር በማስቀመጥ ሲወተውት ቆይቷል፡፡ ነገር ግን የለውጥ ሃይል ነኝ ባዩ መንግስት ከኔ ውጭ መፍትሄ ላሳር፤ የማሻግራችሁም እኔ ብቻ ነኝ በሚል መታበይ የቁልቁለት ጉዞን መርጧል፡፡ በዚህ የመንግስት ፍፁም የሆነ አንባገነናዊ ባህሪም የተነሳ አገራችን አሁን የምትገኝበት ሁኔታ ለውጡ ከመምጣቱ በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር እጅግ ተመሳሳይ ነው፡፡ ከዚህም የከፋ የህልውና አደጋ ተጋርጦብናል፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት ህግና ስርዓትን ማስፈን እየተሳነው በየአካባቢው ንፁሃን ኢትዮጵያዊያን ማንነትን እና ሃይማኖትን ማዕከል ባደረገ ጥቃት ህይወታቸውን እያጡ ነው፣ አካላቸው እየጎደለ ነው፣ ጥሪታቸውን አሟጠው ያፈሩት ሃብትና ንብረት እየወደመ ነው፡፡ በአገር ውስጥና በአለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዘር ጭፍጨፋ/ጄኖሳይድ ነው ብለው በገለፁት በዚህ አሰቃቂ ድርጊት ዜጎች ተንቀሳቅሶ ሃብትና ንብረት የማፍራት ህገ-መንግስታዊ መብታቸው አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ የዜጎች ለዘመናት የተገነባው የመቻቻል፣ የመከባበር፣ የመተዛዘን አኩሪ ባህላችን እየተደፈቀ ዘረኝነት፣ ጎጠኝነትና መንደርተኝነት ከምንግዜውም በላይ ነግሷል፡፡
መንግስት ይሄንን እኩይ ድርጊት የፈፀሙትን ሃይሎች እየተከታተለ ለፍርድ ማቅረብ ሲገባው ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ንፁሃን የፖለቲካ አመራሮችን በማሰር በህግ ማስከበር ሰበብ ህጉን ተቀናቃኞችን ለማጥፋት እንደመሳሪያ እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡ በተለይ የአብሮነት አመራሮች የእስር አያያዝ ፍፁም አደገኛ እንዲሆን እየተደረገ ነው፡፡ አቶ ልደቱ አያሌው ያለባቸው የልብ ህመም እና የአስም በሽታ ለኮሮና ተጋላጭ እንደሚያደርጋቸው የህክምና ሰርተፍኬት አቅርበው ጭምር አቤቱታ ቢያቀርቡም ተቀባይነት ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት የታሰሩበት እስር ቤት 3 እስረኞች በኮሮና መያዛቸውን ገልፀው ለፍርድ ቤት አመልክተው የነበረ ቢሆንም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በጋራ እንዲታሰሩ ተደርጓል፡፡ የባልደራስ አመራሮችም የፍርድ ሂደት በዝግ እንዲሆን፣ ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ቃላቸውን እንዲሰጡ መደረጉም የፍትህ ሂደቱ ነፃ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው፡፡

የአርቲስት ሃጫሉን ሞት ተከትሎ በኦሮሚያ የተነሳው ሁከትና ብጥብጥ የፀጥታ ሃይሉም ሆነ ተጎጂዎች እንደገለፁት ቀድሞ የታቀደ፣ ስም ዝርዝር ተይዞ ሰውን ማንነቱንና ሃይማኖቱን ለይቶ የተፈፀመ ጥቃት መሆኑን ነው፡፡ እንደውም በብዙ ቦታዎች ላይ የአካባቢው ተወላጆች ለብዙ የጥቃቱ ተጋላጮች ከለላ ባይሰጡ ኖሮ ችግሩ ከዚህ የከፋ ይሆን ነበር፡፡ ለነዚህ የአኩሪ ስነ-ምግባር ባለቤት ለሆኑ ዜጎች ለሰሩት በጎ ተግባር አብሮነት ምስጋናውን ያቀርባል፡፡ ነገርግን አሁንም የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ ዳግም የአደጋ ስጋት እንዳለ ጠቁሟል፡፡ በመሆኑም መንግስት ለአደጋ የተጋለጡ ዜጎችን ከለላ እና ጥበቃ እንዲያደርግ እንጠይቃለን፡፡ መንግስት ሁከቱን ተከትሎ በሃሳብ የሚለዩትን የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችንና ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ዜጎች በጅምላ ማሰሩ የመንግስትን አንባገነናዊ ባህሪ ከማሳየት በስተቀር የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም፡፡ ስለዚህ መንግስት ጊዜው ሳይመሽበት አብሮነት ከዚህ በፊት አቅርቦት የነበረውን የሽግግር መንግስት ጥያቄን ተቀብሎ ለሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት ራሱን እንዲያዘጋጅ በድጋሚ ጥሪያችንን ለማስተላለፍ እንወዳለን፡፡

የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ የገመገመው አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት) በተለይ የወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄን ተከትሎ የተፈጠረው ችግርና መንግስት ችግሩን ለመፍታት የወሰደውን የሃይል እርምጃ ፍፁም ተገቢ አለመሆኑን ተገንዝቧል፡፡ መንግስት ይሄን ጥያቄ ያነሱ የዞን አመራሮች፣ የአገር ሽማግሌዎችን፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችንና አክቲቪስቶችን ማሰሩ እና እሱን በተቃወሙ ዜጎች ላይ የወሰደውን እርምጃም አብሮነት አጥብቆ ያወግዛል፡፡ መንግስት በህገ-መንግስቱ መሰረት ለሚነሱ ሰላማዊ የህዝብ ጥያቄዎች በሰከነ፣ በሰለጠነና በህጋዊ አግባብ መልስ መስጠት ሲገባው በሃይል ለማፈን መሞከሩ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው አንባገነናዊ ድርጊት ነው፡፡ ትናንት በኦሮሚያ የዘር ፍጅት/ጄኖሳይድ ሲፈፀም በጊዜ ያልደረሰ መከላከያ ሰራዊት የወላይታ ህዝብ ተወካዮች በውይይት ላይ እያሉ የወሰደው የሃይል እርምጃ ፍፁም ተገቢ አይደለም፡፡ ህዝቡም የሚያነሳው የመብት ጥያቄ መልስ እስኪያገኝ ድረስ በትዕግስት በመጠበቅ ተጨማሪ የህይወት እና የንብረት ኪሳራ ሳያጋጥመው ጥያቄው እንዲመለስለት የበኩሉን ግዴታ እንዲወጣ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች አብሮነት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለፀ ለሟች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶቻቸውም መፅናናትን ይመኛል፡፡

በተጨማሪ ከሰሞኑ መነጋገሪያ የሆነው በብልፅግና አመራሮች በኩል ያለው የፖለቲካ ውጥረት ዳፋው ለአገር እንዳይተርፍ አብሮነት ስጋት አድሮበታል፡፡ የአቶ ሽመልስም ንግግር ተራ የግለሰብ አቋም ብቻ ነው ተብሎ ሊወሰድ የሚችል አይደለም፡፡ አሁን ያለው የለውጥ ሃይል የአመራርነት ብቃት ኢትዮጵያን ሊያሻግር እንደማይችል በአገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ስንናገር መቆየታችን የሚታወስ ነው፡፡ ከሰሞኑም በአንድ ከፍተኛ የብልፅግና አመራሩ በኩል የተሰጠው እና ይፋ የሆነው መረጃም የሚያረጋግጠው የስርዓቱን እውነተኛ ማንነትና ይሄ “ የለውጥ ሃይል ” አገር ብቻውን የመምራት ብቃትም ሆነ ቅንነት እንደሌለው የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን ከቀደመው ህገ-ወጥ የአፈና ተግባር ለመላቀቅ ፍላጎት እንደሌለው በተጨባጭ የሚያሳይ ድርጊት ነው፡፡ የመንግስት እና የብልፅግና አመራሮች የህዝቡን አንድነት፣ አብሮ የመኖር የቆየ ባህል ከሚንዱና የአገራችንን ህልውና አደጋ ውስጥ ከሚጥሉ ንግግሮች እና ፕሮፖጋንዳዎች እንዲሁም የፖለቲካ ሴራዎች እንዲቆጠቡ እንጠይቃለን፡፡ በተጨማሪም ህውሃት የተናጥል ምርጫ ማድረጉ ከህግም ከመፍትሄም አንፃር ተገቢ ባይሆንም ከብልፅግና ጋር ያለው ውጥረት በውይይት መፈታት ሲገባው እየተካረረ መሄዱ በአገር ህልውና ላይ ስጋት የሚፈጥር በመሆኑ ሁለቱም ሃይሎች ውጥረቱን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ እንጠይቃለን፡፡ በሌላም በኩል ይሄን የለውጥ ሃይል ተማምኖ እሱ ያሻግረናል ብሎ መቀመጥ በአገር ህልውና ላይ እንደመቀለድ የሚቆጠር ከባድ ስህተት ነው፡፡ በዚህ መሰረት ለአገራችን ህልውና ሲባል የአንድነት ሃይል የሆናችሁ ከዚህ በፊት የያዛችሁትን አቋም ዳግም በመፈተሸ ከምንግዜውም በበለጠ አብሮነቱን አጠናክረን በጋራ እንድንታገል አገራዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
በአገሪቱ እየታየ ያለው ዘርፈ ብዙ የፖለቲካ ውጥረት እየተባባሰ የሚገኘው ዘላቂ መፍትሔ የሚሹ ህገ-መንግስታዊ መዋቅራዊ ችግሮቻችንን መፍታት ባለመቻላችን ነው፡፡ አብሮነት ይሄን መሰረታዊ፣ መዋቅራዊ እና ስር የሰደደ ችግራችን ሊፈታ የሚችለው ደግሞ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግሰት ሲቋቋም ነው ብሎ ያምናል፡፡

በመሆኑም መንግስት የአገሪቱን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ብቻውን የመፍታት አቅም እንደሌለው ተረድቶ በአስቸኳይ ሁሉን አቀፍ የውይይት እና የምክክር መድረክ እንዲያዘጋጅ፤ የመፍትሄ ሃሳቡ ላይም የሚመለከተው ሁሉ እንዲመክር እየጠየቀን፦

1ኛ- የአርቲስት ሃጫሉን ሞት ተከትሎ በፖለቲካ አመለካከታቸው ከመንግስት በመለየታቸው ብቻ የታሰሩ የአብሮነት ከፍተኛ አመራሮች እና የባልደራስ አመራሮች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፤

2ኛ- በኦሮሚያ የተፈጠረውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸውን አመራሮች ማሰሩን መግለፁ የሚታወስ ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም በስልጣን ላይ ያሉት የኦሮሚያ ከፍተኛ አመራሮች እነሱ በሚመሩት ክልል ሰው በማንነቱና በሃይማኖቱ እየተለየ ጥቃት ሲደርስበት መከላከል ባለመቻላቸው ይቅርታ ጠይቀው ቢያንስ ከስልጣናቸው ሊነሱ ይገባል፤

3ኛ- የአገራችን ፖለቲካዊ ውጥረት ሊረግብ የሚችለው በአንድ ወገን እኔ አውቅልሃለው ባይነት ሳይሆን ሁሉን የሚያሳትፍ የሽግግር መንግስት ሲቋቋም መሆኑ ታውቆ በአማራጭ ሃሳቦች ላይ የሚመክር ሁሉን አቀፍ የውይይት እና የምክክር መድረክ በአስቸኳይ እንዲዘጋጅ፤

4ኛ- የወላይታውን የህዝብ ጥያቄዎችን ተከትሎ የጠፋውን የሰው ህይወት፣ የወደመውን ሀብትና ንበረት፣ የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች የወሰዱትን እርምጃ ተመጣጣኝነት የሚያጣራ፣ የደረሰበትንም የምርመራ ውጤት ለህዝብ ይፋ የሚያደርግ፣ አጥፊዎችንና ተጠያቂዎችን ግልፅ በማድረግ ፍትህ ፊት እንዲቀርቡ የሚያደርግ ገለልተኛ የሆነ አጣሪ ኮሚሽን እንዲቋቋም፣ ለተጎጂ ቤተሰቦችም መንግስት ተመጣጣኝ ካሳ እንዲከፍል፤

5ኛ- አሁን እየተፈጠሩ ያሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ዋነኛው መንስዔ ህገ-መንግስቱ ቢሆንም መንግስት ለአንድ ክልል ተብሎ ህገ-መንግስቱ አይሻሻልም ማለቱ የሚታወስ ነው፡፡ ነገር ግን ህገ-መንግስቱ እስካልተሻሻለ ድረስ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን በዘላቂነት መፍታት እንደማይቻል ተረድቶ ህገ-መንግስቱን ላለማሻሻል የያዘውን ግትር አቋም እንዲፈትሽ፤

6ኛ- አገራችን ከዕለት ወደ ዕለት ከፍተኛ የሆነ የህልውና አደጋ ውስጥ እየገባች ትገኛለች፡፡ የኢትዮጵያን የህልውና አደጋ መቀልበስ የሚቻለው ደግሞ በተናጥል በሚደረግ ትግል አይደለም ብሎ አብሮነት ያምናል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ላይ የተጋረጠውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ እንዲቻል ሁሉም የአንድነት የፖለቲካ ሃይል በአንድ እንዲተባበር አብሮነት ጥሪውን ያስተላልፋል፤

7ኛ- የመብት ጥያቄዎችን የሚያነሳው ዜጋ ተቃውሞውን ንብረት በማቃጠል ሰውን በመግደል ሳይሆን መግለፅ ያለበት ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ መሆን አለበት ብለን እናምናለን፡፡ በተቃውሞ ስም የህዝቡን አንድነት፣ የመቻቻልና አብሮ የመኖር ባህል የሚያቆሽሹ ድርጊቶችን አጥብቆ በመጠየፍ የአገራችንን ህልውና አደጋ ላይ ከሚጥሉ እንቅስቃሴዎች እራሱን እየጠበቀ ተቃውሞውን እንዲያቀርብ እንጠይቃለን፤

8ኛ- መንግስት የያዘውን አንባገነናዊ ግትር አቋም ትቶ ሁሉን ባለድርሻ አካላት የሚያሳትፍ የውይይት መድረክ እንዲያመቻች የፖለቲካ ሃይሎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሚዲያ ተቋማት እና አክቲቪስቶች በአጠቃላይም ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አገርና ህዝብን ባማከለና ባስቀደመ ፍፁም በሆነ ኢትዮጵያዊ ተቆርቋሪነት ስሜት የዜግነት ግዴታችሁን እንድትወጡ አብሮነት ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት)
ነሐሴ 10/ 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ

 
Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter