ስፖርትና ፖለቲካ ጨርሶ መነካካት የለባቸውም!

ከኢዴፓ የሕዝብ ግንኙነት በሀገራችን ለሚገኙ የስፓርት ፌዴሬሽኖችና ማህበራት የተላለፈ መልዕክት፤

የስፖርት ኮሚሽን አማካሪ በሆኑ ግለሰብ የተጻፈና በሀገራችን ለሚገኙ የስፖርት ፌዴሬሽኖችና ማህበራት የተጻፈ ደብዳቤ በማህበራዊ ገጾች ሲዘዋወር ተመልክተናል።

ይህ ደብዳቤ የስፖርት ፌዴሬሽኖቹን ነጻነት የሚጋፋ፤ የስፖርት ሳይሆን የፖለቲካ ዓላማ ያለው የስፖርት ኮሚሽኑ ከተቋቋመለት ዓላማም ሆነ የሥልጣን ገደብ አንጻር ተቀባይነት የሌለው ሆኖ አግኝተነዋል።

የኢትዮጽያ እግር ኳስ ወይም አትሌቲክስ እና የመሳሰሉ የስፖርት ፌዴሬሽኖች ና ማህበራት የመንግስት ሳይሆኑ የሕዝብ ተቋማት ናቸው። የፌዴራል መንግስቱ አስፈፃሚ አካል ነኝ የሚል አካል ቀርቶ ማንም በቀጥታ ሊያዛቸው የማይችላቸው ነጻነታቸው የተጠበቀ በራሳቸው ሕገደንብ የሚተዳደሩ የስፖርቱ ማህበረሰብ ተቋማት ናቸው።

እነዚህ ተቋማት ነጻነታቸው የበለጠ ተጠብቆ እንዲጠናከሩ ማገዝ እንጂ ለፖለቲካ መሳርያነት ለመጠቀም መሞከር በየትኛውም የሀገራችንም ሆነ የዓለም ዓቀፍ ተቋማት ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው። “እኩልነት”፣”ገለልተኝነት”፣ “ወንድማማችነት”፣” ሰላም” ….የመሳሰሉትን የስፓርት መርሆች እንዲዳብሩ እንጂ እንዲሸረሸሩ ማድረግ ኃላፊነተት የማይሰማቸው ፖለቲከኞች ስራ ነው።

ፌዴሬሽኖቹም ሆኑ ማህበራቱ ይህን አድርጉ ወይም አታድርጉ ሊላቸው መብት ያለው ያቋቋማቸው የስፖርት ቤተሰብ እንጂ ሌላ አካል አለመኖሩን ተገንዝበው ተቋማዊ ነጻነታቸውን በማስከበር ለቀረበው የፖለቲካ አስተያየት ራሳቸውን ዝግ በማድረግ የትግራይ የስፖርት ቤተሰብ እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ሁሉ በ ሀገርአቀፍም ሆነ አለምአቀፍ ውድድሮች ያለውን ተሳትፎ እንድታረጋግጡ በትህትና እናሳስባለን።

የስፖርት ፌዴሬሽኖቹ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነትን ፈቅደው የሀገራችን አካል የሆነን ሕዝብ ማሳተፍ ካቆሙ ድርጊቱ በሞራል፣ በፖለቲካና በሕግ የሚያስጠይቅ ብቻ ሳይሆን ሀገራችንን በአለምአቀፍ ውድድሮች እስከማሳገድ የሚደርስ ጣጣ ሊያመጣ እንደሚችል በአንክሮ ሊገነዘቡት ይገባል።

በእርግጥ ይህ ዜና በማህበራዊ ሚዲያዎች ከተሰራጨ በኋላ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተጻፈላቸውን ህገወጥ ደብዳቤ ውድቅ ማድረጋቸውን በስፖርት ዘርፍ የሚሰሩ መገናኛ ብዙሃን የዘገቡ ሲሆን ሕገወጥ ተግባር ውስጥ ራሱን በመክተት አጣብቂኝ ውስጥ የገባው ስፖርት ኮሚሽንም የጻፈውን ደብዳቤ ማንሳቱን የሚገልጽ ሌላ ደብዳቤ በ ምክትል ኮሚሽነሩ አማካኝነት ተጽፎ ሲዘዋወር ተመልክተናል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ እና አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች የስፖርት መርህንና የተቋቋሙለትን ዓላማ በውል በመገንዘብ ሕገወጡን ትዕዛዝ ውድቅ በማድረግ አርዓያነት ያለው ተግባር በመፈጸማቸው አድናቆታችንን እየገለጽን ሌሎች ፌዴሬሽኖችና ማህበራትም ይህንንው በዘላቂነት እንድትገፉበት እናበረታታለን።

ውስብስብና ተገማች ያልሆነው የሀገራችን ፖለቲካ የትኛውንም አቅጣጫ ያዘ የስፖርት ቤተሰቡ ወንድማማችነተቱን በመጠበቅ ማህበራዊ አንድነቱን የሚያጎለብት ስራ ላይ ብቻ እንዲያተኩር እያሳሰብን ፖለቲከኞች የሚፈጽሙትን የሕዝብ አንድነት የሚሸረሽር ተግባር በስፖርት የመመከት በጎ ሚና ብቻ እንዲጫወቱ ከአደራ ጭምር እናመለክታለን።

በዘላቂነትም የስፖርት ፌዴሬሽኖችና ማህበራት ከፖለቲካ ነጻ ሆነው ሊሰሩ የሚችሉት የፋይናንስ ገቢያቸውን ከመንግስት ተቋማት ጥገኝነት በማላቀቅ ህዝባዊ መሰረታቸውን በማስፋት ስለሆነ በዘርፉ ያለውን እምቅ ሀብት በማንቀሳቀስ ጠንካራ ማህበራዊ ተቋማት ሆናችሁ ለማየት ተስፋ እናደርጋለን።

የኢዴፓ የህዝብ ግንኙነት ኮሚቴ

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter