ግልፅ ደብዳቤ ለኢፌዴሪ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር

ግልፅ ደብዳቤ ከኢ.ዴ.ፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ

ለኢፌዴሪ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ

ፓርቲያችን ኢ.ዴ.ፓ እና አባል የሆነበት አብሮነት አገራችን ኢትዮጵያ በሕዳሴው ግድብ አሞላልና ክንዋኔ (Filling and Operation) ጉዳይ ከሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ ሀገሮች (ሱዳን እና ግብጽ) ጋር የምታደርገው ድርድር በይዘቱም ሆነ በአደራዳሪዎች ማንነት ላይ ያለውን ግልጽ ተቃውሞ በተደጋጋሚ ሲገልጽ መቆየቱ ይታወቃል።

ጉዳዩ ያሳሰባቸው ዜጎችና የፖለቲካ ኃይሎች ባደረጉት ጫና እና በድርድሩ የተሳተፉ ባለሞያዎች ጥረት ሀገራችን በዋሽንግቶን ከሚደረገው ድርድር ራሷን እንድታገልና የአደራዳሪነቱን ሚና የአፍሪካ ህብረት እንዲተገብር ማድረግ ተችሏል።

ኢ.ዴ.ፓ – አብሮነት እና ሌሎች ኃይሎች በዋሽንግቶን የሚደረገው ድርድር የኢትዮጵያን ጥቅም አያስከብርም ብለው እንዲከራከሩ ካደረጋቸው ጉዳዮች አንዱ በአደራዳሪነት የተሰየመው የአሜሪካ መንግስት ለስትራቴጂክ ጥቅሞቹ ሲል ለግብጽ ያደላል የሚል ሲሆን ከዚህም አልፎ የግድቡን ጉዳይ ለመካከለኛው ምስራቅ ችግር መፍቻነት ይጠቀምበታል የሚል ነበር።

ይህ ስጋታችን በርግጥም ዕውን ሆኖ አሜሪካ ለግብጽ የምታደላ አደራዳሪ ብቻ ሳትሆን አስገዳጅ ውል አዘጋጅ ሆና በድርድሩ መሳተፏን ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ከእስራኤልና ሱዳን ጠቅላይ ሚንስትሮች ጋር ባደረጉት የስልክ ቆይታ መናገራቸውን ዓለም ሰምቷል።

ፕሬዚደንቱ በዚህም ሳያበቁ ኢትዮጵያ የዘላቂ ትውልዶች ሀብት የሆነውን ዓባይን አሳልፎ የሚሰጠውን ውል ካልፈረመች ወዳጃችን የሆነው የዩናይትድ ስቴትስ ሕዝብ እንደ ወዳጅ ሕዝብነቱ ለሀገራችን ሰጥቶት የነበረውን እርዳታ በፕሬዚደንታዊ ውሳኔ (excutive order) እንዲታጠፍ ማድረጋቸውን በይፋ ገልጸዋል።

የሦስትዮሽ ድርድሩ ሌላኛው አደራዳሪ የነበረው የዓለም ባንክም ኢትዮጵያ በአባይ ተፋሰስ ላይ ለምትሰራቸው የልማት ስራዎች ምንም አይነት ብድር ባለመፍቀድ የሚታወቅ እንደሆነ ግልጽ ነው።

እነዚህ ሁለት በጉዳዩ ላይ አድሏዊ መሆናቸው በማያከራክር ሁኔታ የሚታወቁ አካላት በሕዝብ ጥረት ከዋና አደራዳሪነት ገለል እንዲሉ ቢደረግም የአፍሪካ ሕብረት በሚያደራድረው መድረክ ግን በታሳቢነት በመሳተፍ ላይ ናቸው።

እነዚህ ሁለት አካላት ከዚህ ቀደም በዋሽንግቶን ይደረግ የነበረው ድርድር ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ የተደረገው በታዛቢነት ስም እንደነበርና በስተመጨረሻ ታዛቢ ወይም ገለልተኛ አደራዳሪ ሳይሆኑ ፍጹም አድሏዊ የድርድር ውጤት ወሳኝ የመሆን ፍላጎት ያላቸው መሆኑ በሂደት በማያሻማ ሁኔታ ማንም ተመልካች ሊያየው በሚችለው መጠን ተረጋግጧል።

ስለሆነም የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት በነገው ዕለት ካቆመበት ይቀጥላል በተባለው የአፍሪካ ሕብረቱ ድርድር እነዚህ አድሏዊና ዕጅ ጠምዛዥ “ታዛቢዎች” መገኘታቸው ለሀገራችን ጥቅም መከበርም ሆነ ለተደራዳሪዎች ነጻነት አሉታዊ ተጽዕኖ ያለው በመሆኑ ሁለቱ ታዛቢዎች ተነስተው በጉዳዩ ላይ አንጻራዊ ገለልተኝነት ያላቸው ታዛቢዎች እንዲሰየሙ እንዲጠይቅ በአጽንዖት እናሳስባለን።

የኢዴፓ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ጥቅምት 17 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter