በእርስ-በርስ ጦርነት የበለጠ የሚባባስ እንጂ የሚፈታ ችግር የለም!

ከአብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት (አብሮነት) የተሰጠ መግለጫ

ቢያንስ ላለፈው አንድ ዓመት አገራችን እጅግ አሳሳቢ ወደሆነ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ እየገባች እንደሆነ አብሮነት አበክሮ ሲያሳስብ ቆይቷል፡፡ አገሪቱ ውስጥ እየተፈጠረ ባለው አሳሳቢ የፖለቲካ ችግር ፈጣንና አስተማማኝ የሆነ የፖለቲካ መፍትሄ ካልተሰጠ በስተቀር አገሪቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደለየለት የእርስ በርስ ጦርነት ወይም መንግስት የለሽ ሁኔታ ልትገባ እንደምትችል ያለውን ስጋት ደጋግሞ ሲገልፅ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ስጋት መውጣት የሚቻለውም ሁሉን አቀፍ የሆነ የፖለቲካ ውይይትና ድርድር በማካሄድና ለነፃና ፍትሃዊ ምርጫ በቂ ዝግጅት ለማድረግ የሚያስችል የእርቅና የአንድነት የሽግግር መንግስት በማቋቋም መሆኑንም በተደጋጋሚ ገልጿል፡፡

አብሮነት ይሄንን የመፍትሄ ሃሳቡን በጥቅሉ ከማቅረቡም በላይ ምን ዓይነት የሽግግር መንግስት ሊቋቋም እንደሚችል በዝርዝር የሚያሳይ አማራጭ ሰነድ በማዘጋጀትም ለውይይት አቅርቧል፡፡ ነገር ግን የአገሪቱ የፖለቲካ መሪዎች ካለፉት የአገሪቱ መሪዎች ታሪካዊ ስህተቶች ተገቢ ትምህርት ያልቀሰሙና በአስተሳሰብም የተሻሉ ባለመሆናቸው ከአገሪቱ ጥቅምና ደህንነት በላይ ለራሳቸው የፖለቲካ ስልጣን የበላይነት የሚጨነቁ በመሆናቸው ምክንያት አብሮነት ያቀረበው የሰላም ሰነድ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ ይህም በመሆኑ አብሮነት ሊከሰት ይችላል ብሎ የገመተው ስጋት እውን ሆኖ አገሪቱ ግልፅ የሆነ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የገባችበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
ይህ በአሁኑ ወቅት አገራችን እየገባችበት ያለው የእርስ በርስ ጦርነት በታሪካችን አይተነው በማናውቅ መጠን እጅግ አውዳሚ የሚሆን፣ ወደ ባሰ ድህነት እና የሰላም እጦት ብቻ ሳይሆን አገራዊ ህልውናችንን ወደሚያሳጣ አደጋ ሊያስገባን የሚችል ሊሆን ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮብናል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ በረዥም ዘመን የመንግስትነት ታሪኳ ከውጭ ወራሪዎች ጋር ካደረገቻቸው ጦርነቶች ውጭ በእርስ በርስ ጦርነት አንድም ጊዜ ተጠቃሚ ሆና አታውቅም፡፡ እንዲያውም የእርስ በርስ ጦርነት ነባር ስልጣኔዋን በማጥፋት፣ የህዝቦቿን አንድነት በመሸርሸር፣ በኢኮኖሚና በልማት እድገት ላይ ትኩረት እንዳታደርግ በማድረግ ለድህነትና ለሁለንተናዊ ኋላቀርነት እንድትጋለጥ አደረጋት እንጂ የጠቀማት ነገር የለም፡፡ ዛሬም ሆነ ወደፊት አገራችን በማንኛውም ዓይነት የእርስ በርስ ጦርነት ችግሮቹን የበለጠ ከማባባስና ከማወሳሰብ፣ ምን አልባትም አጠቃላይ አገራዊ ህልውናዋን ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ከማስገባት ባለፈ ልታገኘው የምትችለው ጥቅምም ሆነ ልትፈታው የምትችለው ችግር አይኖርም፡፡ የፖለቲካ ችግራችንን በውይይት እና በድርድር መፍታት እየተቻለም ወደ አውዳሚ ጦርነት ውስጥ መግባትም አመለካከት ብስለትን፣ ጀግንነትን ወይም አገር ወዳድነትን የሚያሳይ ሳይሆን በተቃራኒው የአመራር ድክመትን፣ ለአገር ደህንነት ደንታቢስ መሆንና ኋላቀርነትን የሚያሳይ ነው፡፡ ዓለም ከፍተኛ የስልጣኔ ደረጃ በደረሰበትና የእርስ በርስ ጦርነት የጥቂት በጣት የሚቆጠሩ ኋላቀር የዓለም አገሮች መገለጫ ሆኖ በሚታይበት የ21ኛው ክፍለ ዘመን የፖለቲካ ችግራችንን በእርስ በርስ ጦርነት ለመፍታት መሞከራችን በአለም ፊት አሳንሶ የሚያሳየንና የሚያስንቀን ድርጊት ነው፡፡

ስለሆነም፣ አገራችን በአሁኑ ወቅት የገጠማትን ይህንን እጅግ አሳሳቢ የሆነ ፈተናና ችግር በተመለከተ አብሮነት ባደረገው ሰፊ ውይይት የሚከተሉትን አቋሞች ወስዷል፡፡
በእኛ እምነት በአሁኑ ወቅት አገሪቱ እየገባችበት የምትገኘው የእርስ በርስ ጦርነት የአገሪቱን አንድነትና ቀጣይ ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል፣ ከአገሪቱም አልፎ የአፍሪካ ቀንድ አገራትን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል እጅግ አሳሳቢና አደገኛ ክስተት ነው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግስት፣ ገዥው ፓርቲም ሆነ በአገሪቱ የምንገኝ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የመገናኛ ብዙሃን የጉዳዩን ክብደት እና አሳሳቢነት በአግባቡ በመገንዘብ ጉዳዩን ከማንኛውም የፖለቲካ ቡድን ጥቅም፣ ከጥላቻ፣ ከጀብደኝነት እና ከጊዜያዊ ስሜት በጸዳ አገራዊ ሃላፊነት የአገሪቱን ጥቅም ባስቀደመ አግባብ በስክነት ልናጤነው ይገባል፡፡ በተለይም መንግስት ይህ ጦርነት እየተባበሰ ከመጣ በወቅቱም ሆነ በወደፊቱ የአገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ሰላምና መረጋጋት፣ ከዚያም በላይ በአገሪቱ አጠቃላይ ህልውና ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ በውል በመገንዘብ ጉዳዩን ስክነትና ሆደ ሰፊነት በተሞላበት የሃላፊነት ስሜት ለመፍታት የሚያስችለውን አቅጣጫ መያዝ ይገባዋል፡፡

ህዝቡ ይህ ጉዳይ ከማንም በላይ የራሱንና የልጆቹን የወደፊት ህልውና የሚመለከት እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ የማንኛውም የፖለቲካ ሃይል የፕሮፖጋንዳ ሰለባ ሳይሆን፣ በብሄርም ሆነ በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳይከፋፈል ለአገሩ ደህንነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት በመቆም የተፈጠረው ችግር ዘላቂ የፖለቲካ መፍትሄ እንዲያገኝ የበኩሉን የማይተካ ድርሻ መወጣት አለበት፡፡ በተለይም ጦርነቱ በማንኛውም መመዘኛ የህዝብ ለህዝብ እንዳይሆን ከፍተኛ ጥንቃቄና ጥረት ሊያደርግ ይገባል፡፡ በህዝቡ ውስጥ ተደማጭነት ያላቸው የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና ታዋቂነት ያላቸው ዜጎችም ችግሩ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲያገኝ በፍጥነት ርብርብ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
የአገራችን መከላከያ ሰራዊት ከማንም በላይ የአገሪቱን አንድነትና ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ሃላፊነት አለብት፡፡ ይህንን ታላቅ ህዝባዊ ሃላፊነት በአግባቡ መወጣት ይችል ዘንድም ከማንኛውም የፖለቲካም ሆነ የብሄር ክፍፍል ራሱን በማቀብ ለአገሪቱ ህልውና መከበር እና መቀጠል በአንድነት መቆም ይገባዋል፡፡ ህዝቡም አገሪቱን ከጥፋት ለመታደግ ሰራዊቱ ያለውን የማይተካ ወሳኝ ሚና በመገንዘብ ሁለንተናዊ ድጋፉን ሊሰጠው ይገባል፡፡

በረዥም ዘመናት የአገራችን የመንግስትነት ታሪክ ሲሆን እንደታየው የእርስ በርስ ጦርነት የዜጎችን ህይወት ከመቅጠፍና የአገርን ሃብት ከማውደም ባለፈ ለየትኛውም ዓይነት የፖለቲካ ችግራችን መፍትሄ ሆኖ አያውቅም፡፡ ዛሬም ሆነ ወደፊት መፍትሄ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለሆነም ማንኛውም የሃይል አማራጭም ሆነ ግጭት በአስቸኳይ ሊቆምና በፍጥነት ወደ ሰላማዊ የውይይት እና የድርድር ሂደት መገባት አለበት፡፡
ህዝቡ በሙሉ ልብ ሊደግፈው የሚችል ሰላማዊ የውይይት እና የድርድር ሂደት እንዲኖርም በአገሪቱ ያሉ የፖለቲካ እስረኞች ሊፈቱና የአገሪቱ የፖለቲካ ችግሮች የመፍትሄ አካል እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የአፍሪካ ህብረትና የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆኑ የአፍሪካ አገራትም ይህ ችግር እጅግ አሳሳቢና ከኢትዮጵያም አልፎ የአካባቢው አገራትን የሚመለከት ከባድ ችግር መሆኑን በመገንዘብ ጉዳዩ በሰላማዊ ውይይትና ድርድር እንዲፈታ የበኩላቸውን ጥረት በአስቸኳይ መጀመር ይገባቸዋል፡፡

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሃይሎች ካለፉት ታሪካዊ ስህተቶቻችን ለመማር ፍላጎት ካላጣን በስተቀር በጠረጴዛ ዙሪያ ውይይትና ድርድር መፈታት የማይችልና ከሌላው ዓለም የተለየ የፖለቲካ ችግር የለብንም፡፡ ከራስና ከቡድን የፖለቲካ ስልጣን በላይ የአገርና የህዝብን ፍላጎትና ጥቅምን ማስቀደም እስከቻልን ድረስ ማንኛውንም ዓይነት ቅራኔአችንን በሰላማዊ ውይይት እና ድርድር መፍታት እንችላለን፡፡ ካለፉት ትውልዶች የተሻልን እና ለዘመኑ የሚመጥን አስተሳሰብ ያለን መሆኑን ማሳየት የምንችለውም በእርስ በርስ መገዳደል ሳይሆን በውይይት እና በድርድር ሂደት የጋራ አሸናፊ ለመሆን በመብቃት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ያለው አማራጭ አውዳሚ፣ እርባና ቢስና የኋላ ቀርነት መገለጫ ነው፡፡ ማንኛውም የእርስ በርስ ጦርነት ሄዶ ሄዶ ዘላቂ መቋጫና መፍትሄ የሚያገኘው በውይይት እና በድርድር መሆኑ እየታወቀ ፋይዳ ቢስ በሆነ ጦርነት ውስጥ ገብቶ የዜጎችን ውድ ህይወት መቅጠፍና የአገርን ሃብት ማውደም ቢያንስ ከቅርቡ የባድመ ጦርነት መማር አለመቻላችንን የሚያሳይ የተሳሳተ ድርጊት ነው፡፡ ስለሆነም ከአሁን ቀደምም ደጋግመን እንዳልነው አሁንም ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ አቅጣጫ ከመሳታቸው እና ከቁጥጥር ውጭ ከመሆናቸው በፊት አስተማማኝ የፖለቲካ መፍትሄ ለማስገኘት የሚያስችለን አገራዊ የሰላም የውይይት ሂደትና ድርድር በአስቸኳይ እንዲጀመር አብሮነት በአፅንኦት ይጠይቃል፡፡

አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት)
ጥቅምት 28/2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter