እውን ኢዴፓ “ወያኔ” ነው? በምን መስፈርት? “ወያኔነትስ” ወንጀል ነው?

(ከፍቅሩ አየለ በላይ)

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ ሰሞኑን የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች “እየደረሰብኝ ነው” ያለውን “የመገለል” ሁኔታ በመቃወም ያወጣው መግለጫ ነው። መግለጫውን ከሬዲዮ፣ ከቴሌቪዥንና ከጋዜጦች ተከታትያለሁ። ኢዴፓ ከተመሰረተበት ዕለት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ባሉት አስር ዓመታት ገደማ አንድ ተለይቶት የማያውቅ ቅፅል “ኢዴፓ ወያኔ ነው” ወይም “ኢዴፓ የኢህአዴግ ተለጣፊ ነው” የሚል ሲሆን፤ ይህ አባባል አንዳንድ ጊዜ “ልደቱ ወያኔ ነው፣ ሰርጎ ገብ ነው” ወደሚል ደረጃ ዝቅ ተደርጎ ሲነገር ይሰማል። “ለመሆኑ ኢዴፓን በእንዲህ ያለ ፍረጃ የሚወነጅለው ማን ነው?” የሚለውን ጥያቄ ማንሳቱ ተገቢ ነው። መልሱ በአጭሩ “አንዳንድ ተቃዋሚዎችና አንዳንድ የገዥው ፓርቲ አባላት ናቸው” የሚል ነው። አሁንም “ለምን ይህንን አደረጉ?” የሚል ተጨማሪ ጥያቄ ማስከተል ይቻላል። ለዚህ ጥያቄ መልስ ከማቅረቤ በፊት፣ በአጠቃላይ በሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪክ “ፍረጃና የፈጠራ ስም መለጠፍ” አሰራር ምን እንደሚመስል በአጭሩ መመልከቱ ተገቢነት ስላለው እሱን ላስቀድም።

በሀገራችን ፓርቲዎችን መሰረት ያደረገ (party politics) ፖለቲካዊ አደረጃጀት የተጀመረው በ1960ዎቹ አጋማሽ ገደማ መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ። በዚህ ወቅት ብቅ ብቅ ካሉት ድርጅቶች መካከል ኢህአፓ፣ መኢሶን፣ ኦነግ፣ ተሓህት፣ ሰደድ፣ ኢጭአት፣ ወዘተ. የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ድርጅቶች (ሁሉም ማለት ይቻላል) የግራ ፖለቲካዊ ርዕዮት የሚያራምዱ ቢሆኑም፤ አንዱ ለሌላው እንደ ትልቅ ተቀናቃኝ አልፎ ተርፎም እንደ ጠላት የሚታይበት ሁኔታ ነበር። እናም፣ የአንዱ ድርጅት አባል ከሌላው ድርጅት አባል ወንድሙ፣ እህቱ፣ ዘመዱ ወይም ጓደኛው ጋር አብሮ ከታየ፤ አባል የሆነበት ፓርቲ እከሌ/እከሊት “ዲሞ” (የኢህአፓ አባል) ሆነ ወይም “ፊዲስት” (የመኢሶኑ ኃይሌ ፊዳ) አባል ሆነ የሚል ስም ተሰጥቶት ዕድለኛ ከሆነ፤ እጣ ፈንታው ካለበት ፓርቲ መባረር ብቻ ይሆናል። ዕድለኛ ካልሆነ በድርጅቶቹ ገዳይ ቡድኖች “እርምጃ” ይወሰድበታል።

ይህ ዓይነቱ የፖለቲካ አስተሳሰብና አሰራር በሀገራችን በአንድ ወቅት ስራ ላይ የዋለ የታሪካችን አካል እንደሆነ በጊዜ መርዘም የሚዘነጋ አይመስለኝም። ዛሬ ዕድሜአቸው በአርባዎቹ መጨረሻና ከዚያ በላይ የሆናቸው በህይወት ያሉ ዜጎች ሁሉ ያለፉበትና የዓይን ምስክር ሆነው የሚቀርቡበት ጉዳይ እንደሆነ ይታወቃል። በዚያ ወቅት “ፍረጃ” እንደዋነኛ የግምገማ ስልት የተወሰደበት ምክንያት አንዱ ፓርቲ አባሉን ወደ ሌላው ፓርቲ አስርጎ የማስገባት ሁኔታና ፖለቲካችን በመቻቻልና በመነጋገር ላይ የተመሰረተ ባለመሆኑ ነበር። ይኸው አስተሳሰብና አሰራር ዛሬም ቢሆን በዚያ ዘመን ፖለቲከኞች የሚዘወተር ተግባር በመሆኑ እንደ ኢዴፓ ያለ በዚህ ዘመን ትውልድ የሚመራ ፓርቲ በዚያ ዘመን ስልት መከራውን የሚያይ የአሉባልታ ሰለባ ሆኗል።

ቀደም ሲል ወዳነሳሁት ጥያቄ ልመለስ። አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኢዴፓን “ወያኔ” ብለው የሚፈርጁት በርግጥም የኢዴፓ የፖለቲካ መስመር፣ አደረጃጀት፣ መርህም ሆነ አሰራር ከ”ወያኔ” ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ሳይሆን፤ “ኢዴፓ በፖለቲካ አጀንዳነት ይዞት የተነሳው ዓላማ ከእኔ አደረጃጀትም ሆነ ዓላማ የተሻለ በመሆኑ በህዝብ ተቀባይነት ካገኘ እኔን ተቀባይነት ያሳጣኛል ከሚል ስጋት በመነሳት፤ ‘ወያኔ በህዝብ የተጠላ’ ስለሆነ ኢዴፓን የ‘ወያኔ’ አጋርና ተለጣፊ እንደሆነ አድርገን ካስወራንበት፣ እኛ ባለን ታዋቂነትና ተደማጭነት ህዝቡ ሳያመዛዝን አምኖ ይቀበለናል” በሚል ተራ የፖለቲካ ግብ ምክንየት ነው። ይህንን ተራ የፖለቲካ ግብ አንዳንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆኑ፤ አንዳንድ ደካማ የኢህአዴግ አባላትም “ኢዴፓማ የኛው ነው” በሚል አገላለጽ እንደሚጠቀሙበትም ይነገራል። ሁለቱም ኃይሎች ይህንን የሚያደርጉት “ኢዴፓን በህዝብ በማስጠላት” ተራ የፖለቲካ ትርፍ ለማትረፍ ነው።

እንግዲህ “ኢዴፓ ወያኔ ነው፣ ተለጣፊ ነው” የሚለው አባባል በፓርቲው ላይ በከረረ መልኩ የሚወራበት ከላይ በተገለጸው ምክንያት ሲሆን፤ ይህ አባባል ተራ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ከሚደረግ ሩጫ በላይ ቅንጣት ታህል እውነትነት የሌለው መሆኑን በሁለት መንገዶች ማረጋገጥ ይቻላል። ይኸውም፣ አንደኛ እነዚያው “ኢዴፓ ወያኔ፣ ተለጣፊ ነው” የሚሉት አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸው እንዲህ ማለታቸውን ይረሱትና (ከልባቸው ስላልሆነ) ከኢዴፓ ጋር ውህደት ወይም ህብረት ወይም ቅንጅት ፈጥረው አብረው ሲሰሩ መታየታቸው ነው። ኢዴፓ እነሱ ጋር አብሮ ሲሰራ ወይም ሲዋሃድ “ወያኔነቱ” የሚቀር ከሆነ ከእነርሱ ጋር ሳይሆንም “ወያኔ” ሊሆን አይችልም ማለት ነው። የሚያስወሩበትም ለሌላ የፖለቲካ ግብ ስለሆነ የተባለው ሁሉ በሀቅ ላይ የተመሰረተ አለመሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል። የኢዴፓን የኢህአዴግ ተለጣፊ አለመሆን የሚያረጋግጠው ሁለተኛውና ዋነኛው ምክንያት  የሁለቱ ድርጅቶች (የኢህአዴግና የኢዴፓ) የፖለቲካ መስመር፣ ፖሊሲ፣ መርሖ፣ አሰራርና አደረጃጀት ነው። ኢህአዴግ የሚያራምደው አብዮታዊ ዴሞክራሲ የግራ ፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም ሲሆን፤ ኢዴፓ ደግሞ በመሀከለኛ ቀኝ የሊበራል ዴሞክራሲ ርዕዮ-ዓለም ተከታይ መሆኑ ይታወቃል። እነዚህ ሁለት ፖለቲካዊ አሰላለፎች ደግሞ የሰማይንና የምድርን ያህል የተራራቁ መሆናቸው የሚያጠራጥር አይደለም። በመሆኑም፣ የሁለቱን ድርጅቶች ሰነዶች ያነበበ ሁሉ ይህንን ልዩነት ማረጋገጥ ይችላል።

ከላይ በአጭሩ ካቀረብኩት ትንታኔ ኢዴፓ ከኢህአዴግ ያለውን ልዩነት ብቻ ሳይሆን፤ ይህ ፍረጃ በኢዴፓ ላይ ለምን እንደሚለጠፍበት ለመረዳት የሚቻል ይመስለኛል። ይህ እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ኢዴፓ የተለያየ ርዕዮተ-ዓለም፣ አደረጃጀት፣ መርህና አሰራር ካላቸው በሀገሪቱ ካሉ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር አንድ በሚያደርጉትና በሚያግባቡት አጀንዳዎች ዙሪያ መስራት ከቻለ፣ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ድርጀት የሚያግባባቸው አጀንዳ ካለ ኢዴፓ እና ኢህአዴግ አንድ ላይ ቢሰሩስ ነውሩ ምኑ ላይ ነው? ስህተትስ የሚሆነው ምኑ ላይ ነው? ሀጢያቱስ ምንድነው? ኢዴፓም ሆነ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሀገር በመምራት ላይ ካለው ከኢህአዴግ ጋር በጋራ አጀንዳ ዙሪያ አንድ ላይ ካልሰሩ ከማን ጋር ሊሰሩ ነው? ከታንዛንያው ቻማ ቻማ ፑንዱዚ፣ ከዚምባብዌው ዛኑ ፒኤፍ፣ ከደቡብ አፍሪካው ኤኤንሲ፣ ከእስራኤሉ ካዲማ፣ ከፍልስጤሙ ሃማስ፣… ጋር ይሆን መስራት ያለባቸው? ፍርዱን ለአንባቢ ልተወውና ወደ ሌላ ጉዳይ ላምራ።

ሌላው በአንዳንድ ኢዴፓን በሚከሱና በሚወነጅሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚነሳው ጉዳይ “የኢህአዴግ አባልነትን” ወይም በነሱ አጠራር “ወያኔነትን” ዝቅ ሲል ‘ሀጢያት’ ከፍ ሲል ‘ወንጀል’ አድርጎ የማየትና ሌሎችም “በነሱ ዓይን” እንዲያዩትና እንዲገነዘቡት የማድረጉ አመለካከት ነው። በኔ እምነት የኢህአዴግ “አባልነት” ሀጢያትም፣ ወንጀልም፣ እርግማንም፣ መቅሰፍትም፣… አይደለም። የኢህአዴግ አባልነት የሌላ ፓርቲ አባል እንደመሆን መብት ነው።

እኛ የኢዴፓ አባላት ኢህአዴግን የምንታገለው ወንጀለኛ ወይም ሀጢያተኛ ወይም የተረገመ ስለሆነ ሳይሆን፤ ኢህአዴግ የሚከተለው የፖለቲካ ርዕዮ-ዓለምና ፖሊሲ ለሀገሪቱና ለህዝቧ መልካም አስተዳደርን አላጎናጸፈም፣ ድህነትን አስወግዶ ሁሉንም ተጠቃሚ ያደረገና ቀጣይነት ያለው አስተማማኝ ልማት አላመጣም፣ ለሀገሪቱ ልማትና ደህንነት አስፈላጊ የሆነ የባህር በር እንዲኖራት አላደረገም፣ ወዘተ. በሚል መሰረታዊ የዓላማ ልዩነት በህዝብ ይሁንታ ስልጣን ተረክቦ ለውጥ ለማምጣት ነው።

በርግጥ ይህ የኢዴፓ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የፖለቲካ አስተሳሰብ ከዚያኛው ዘመን የፖለቲካ ሰዎች አስታሳሰብም ሆነ አሰራር በብዙ ሺህ ማይሎች ስለሚርቅ፤ ለአንዳንዶቹ በግራ ፖለቲካ የተቃኙ ፖለቲከኞች በቀላሉ የሚገባቸው አልሆነም። ለመሆኑ እነዚህ ኢዴፓን በፍረጃ ፖለቲካ “ለማሸነፍ” ከሚታትሩ ኃይሎችና ከኢዴፓ (በአደረጃጀትም ሆነ በዓላማ) ለኢህአዴግ የሚቀርበው ማን ነው? እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ከኢህአዴግ ጋር ልቡ እስኪጠፋ ሲሰራስ የነበረው ማን ነው? ለነዚህ ጥያቄዎች ያለኝን መልስ በቀጣዩ ጽሑፍ አቀርባለሁ።

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter