“ገቢዎች ከመንግስትም በላይ ስልጣን የተሰጠው አካል ነው” አቶ ሙሼ ሠሙ – የኢዴፓ ሊቀመንበር

ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሰሞኑን በሙስና በጠረጠራቸው ትላልቅ ባለስልጣናትና ባለሃብቶች ላይ የወሠደውን እርምጃ እንዴት ይመለከቱታል? ለኛ ይሄ ነገር የተለየ እውቀት የሚጠይቅ አይደለም፡፡ ስቴት ካፒታሊዝም ወይም መንግስታዊ ከበርቴ የምትለው ስርአት አይነተኛ መገለጫው ነው፡፡ ነጋዴውን ህብረተሠብ የሚያሸማቅቅ፣ የመንግስትን ሚና የሚያጐለብት ነው፡፡ የንግዱን ማህበረሠብ የመንግስት ባለስልጣን ጥገኛም እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ጉዳዩን ለማስፈፀም፣ ስራውንም ለመስራት ሣይወድ በግዱ የመንግስት ባለስልጣናት አሽከር ይሆናል፡፡ ነጋዴውና የንግዱ ማህበረሠብ እየተዳከመ መንግስት እንዲተካው ነው ጥረት እየተደረገ ያለው፡፡ መጨረሻ ላይ ይህ ስርአት ወዴት ነው የሚሄደው? ሂደቱ የመንግስት ባለስልጣናትን ከበርቴ የሚያደርግ ነው፡፡
ምክንያቱም ነጋዴው ችግሮቹን የሚፈታበትን መንገድ የሚያመለክት አይደለም፡፡ ባለሃብቱ በጥርጣሬ ነው የሚታየው፡፡ ታማኝ አይደለም፣ ብቁ አይደለም፣ ስርአት የለውም እየተባለ ነው፡፡ ግለሠብ ነጋዴውን በጥርጣሬና በስጋት የማየት አዝማሚያ አለ፡፡ ስግብግብ፣ ሌባ፣ ወንበዴ ወዘተ— ተደርጐ ነው የሚታየው፡፡ አሁን የተያዙት ባለስልጣኖች ይሄ ሁሉ ጉድ እያለባቸው ነው ነጋዴውን ሲያስፈራሩት፣ ሲዝቱበትና ኪራይ ሠብሣቢ ሲሉት የኖሩት፡፡ ስርአቱ ለእነዚህ ባለስልጣኖች መደራደሪያ በር ከፍቶላቸዋል፡፡ የፈለጉትን ነጋዴ በፈለጉት ጊዜ ጠርተው እያሸማቀቁና ስሙን እያጠፉ ህገወጥ በሆነ መንገድ መጠቀሚያ አድርገውታል፡፡ ይሄ ለኔ ሠዎችን የማሠርና ያለማሠር ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ የስርአቱን የአስተሣሠብ ለውጥ የሚፈልግ ነው፡፡

የመንግስት ሹመኞችና ባለስልጣኖች የነጋዴውን ማህበረሠብ እንደ ሌባ፣ አታላይ፣ አጭበርባሪ፣ ኪራይ ሠብሣቢና ጠላት አድርገው የሚያዩበት ሁኔታ እስካልተለወጠ ድረስ ሙስናው ይቀጥላል፣ የመደራደሪያ በር ነው የሚከፍተው፡፡ አሁን የወሠዱት እርምጃ የሚደነቅ ነው፡፡ በሂደት ግን ውሣኔውንም የምናየው ይሆናል፡፡ አሁን የተደረገው “የበረዶ ጫፍ ነው” (Tip of the ice burg) እንደሚሉት ፈረንጆቹ፡፡ ትልቁ ጫፍ ገና ውሃው ውስጥ ነው ያለው፡፡ እንጀራ ጋግራ ከምትሸጥ ሴት ጀምሮ ገንዘብ የሚሠበሰብ መስሪያ ቤት፣ በዚህ ደረጃ መርከስና መበስበስ ውስጥ ከገባ፣ ሥርዓቱ ለአደጋ መጋለጡን ነው የሚያሳየው፡፡ በአጠቃላይ ስርአቱ የተጋረጠበት አደጋ መገለጫው ይሄ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህም በፊት ሙስና ነበረ፤ ግን በመቶ ሚሊዮኖች አልነበረም፡፡ ነጋዴው አቤት የሚልበት ነፃና ገለልተኛ አካል ነበረው፤ አሁን ግን መስሪያ ቤቱ የራሱ ፖሊስ አለው፡፡

ዳኛ ነው የፈለገውን ነገር ይፈርዳል፡፡ አቃቤ ህግ ነው፡፡ ታዲያ እንዴት ከዚህ መስሪያ ቤት ጋር መስራት ይቻላል? ይሄ እኮ ከመንግስትም በላይ ስልጣን የተሠጠው አካል ነው፡፡ እነዚህ ሠዎች ዳኛ ናቸው፣ ፍርድ ቤት ናቸው፣ አቃቤ ህግ ናቸው፣ ፖሊስ ናቸው፡፡ ስርአቱ እንደፈለጉ እንዲፈልጡ እንዲቆርጡ ስልጣን ስለሠጣቸው፣ የድፍረታቸው ድፍረት ቤታቸው በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ማስቀመጣቸው ተነግሮናል፡፡ ስርአቱን እንዳለ በገንዘብ፣ በጉቦ መቆጣጠር የሚችሉበት ደረጃ ላይ መድረሣቸውን ነው የሚያመለክተው፡፡ አንድ ሌባ የሠረቀውን ነገር ቤቱ የሚያስቀምጠው እኮ በጣም ደፋር ሲሆን ነው፡፡ ይህ እንግዲህ የስርአቱ መገለጫ ነው፡፡ የተወሠደውን እርምጃስ እንደ መልካም ጅማሮ ማየት ይቻላል? ልትወስደው ትችላለህ፡፡ ግን ዋናው ችግር ግለሠቦቹ ላይ አይደለም፤ ሥርዓቱ ላይ ነው፡፡ ማህበረሠቡ ሙስናን የሚፀየፍ ፣ የመንግስት ባለስልጣናት ደግሞ ተገቢውን ክፍያ እያገኙ ስራቸውን እንዲሠሩ ማድረግ ነው ጠቃሚው፡፡ ይሄን ሠውዬ ብታስረው ገና የእሡ ርዝራዦችና መሠሎቹ በየመስሪያ ቤቱ አሉ፡፡

ይሄ ነገር እኮ ሲባል የከረመ ጉዳይ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም አንድ እጄን ታስሬ እየሠራሁ ነው እስከማለት ደርሠው ነበር፡፡ ይሄ የሚያሣየው ምን ያህል ስር የሠደደ ችግር እንደሆነ ነው፡፡ ግለሠቦችን ማሠር ሙስናን ለመዋጋት አንድ መገለጫ ነው፤ ዋናው ነገር ግን የአስተሣሠብ ለውጥ ነው፡፡ ፍትሃዊ የሆነ የህግ ስርአት ሊበጅ ይገባል፡፡ ለአንድ መስሪያ ቤት የእግዚአብሔርን ያህል ጉልበት ተሠጥቶት እንዴት ሙስናን መዋጋት ይቻላል፡፡ ህገ ወጥ ነገር ለመስራት ሁሉም ነገር ተመቻችቶለታል፡፡ ይህ እያለ እንዴት ነው ሙስናን መታገል የሚቻለው፡፡ እርግጥ ስርአቱ በሽታውን ተረድቶ እርምጃ ለመውሠድ መነሣሣቱ የሚበረታታ ነው፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ እየተጋነነ እየተወራ ነው፡፡ አንዳንድ ነጋዴዎችም እንዲበረግጉ እየተደረገ ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ መንግስት ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል፡፡ ሠዎቹ እንደየጥፋታቸው ፍትህ ፊት ቀርበው ተመጣጣኝ ቅጣት የሚያገኙበትን መንገድ መከተል ነው እንጂ ድራማ መስራት አይጠቅምም፡፡ ማጋነን፣ ነገሩን ከሚገባው በላይ መለጠጥ፣ ማህበረሠቡ በዚህ ጉዳይ የተዛባ መረጃ ኖሮት ያልተገባ ነገር እንዲናገር ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡ እነዚህ ነጋዴዎች ተገደው የገቡ ሊሆኑም ይችላሉ፡፡ ሌሎች ደንግጠውና በርግገው ሃገር ጥለው እንዲሄዱ የሚያደርግ መሆን የለበትም፡፡ እነዚህ ሠዎች አሁንም ገና ተጠርጣሪ ናቸው፡፡ ስርአት ባለው መንገድ ተይዘው የሚቀጡ ከሆነም መቀጣት አለባቸው፡፡ አሁን ግን የሚወራው ያለቀ ጉዳይ ተደርጐ ነው፡፡ ቀድሞ በፕሮፓጋንዳ ግለሠቦቹን ወንጀለኛ አድርጐ ደምድሞ፣ ፍርዱ ትርጉም እንዲያጣ ማድረግ አይገባም፡፡ እነዚህ ሠዎች እኮ በአንድ ጊዜ ስማቸው ወርዷል፣ የፕሮፓጋንዳው ሠለባ ሆነዋል፡፡ ሌሎችም እንዲበረግጉ ሆኗል፡፡ ነገር ግን መንግስት “እነዚህ ግለሠቦች ተይዘዋል፣ ሌላው ነጋዴ ተረጋግቶ ስራውን ይስራ” ማለት ነበረበት፡፡ ጠቅለል ብሎ ሲታይ የዚህ ሁሉ መሠረታዊ ችግር ይሄ መስሪያ ቤት የተሠጠው ከእግዚአብሔር ያልተናነሠ ስልጣን ነው፡፡ መንግስት አሁንም በነጋዴው ላይ ያለውን የተዛባ አመለካከት ይለውጥ፡፡

ምንጭ – አዲስ አድማስ

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter