ሦስተኛው መንገድ

በኤርሚያስ ባልከው
(የኢ.ዴ.ፓ ድርጅት ጉዳይ ኃላፊ)

PDF ለዚህ ፅሁፍ ምክንያት የሆነኝ ማክሰኞ ታህሳስ 16 ቀን 2006 ዓ.ም ቅፅ 02 ቁጥር 50 ኢትዮ- ምህድር ጋዜጣ ላይ የኢዴፓ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” በሚል ርዕስ አቶ ጌታነህ አስቻለው የተባሉ ፀሐፊ የፃፉትን ፅሁፍ ካነበብኩ በኋላ ነው፡፡ በኔ በኩል የፅሁፍ መፃፍ ሀሳቡን የበለጠ ለማብራራት እድል የሚሰጥ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ፡፡ ነገር ግን ፀሀፊው ሃሳቡ ላይ ከማተኮር ይልቅ የግለሰብ ስም ለማጥፋት መሞከር ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ የሆነው ሆኖ አቶ ጌታነህ ኢዴፓ የሚለውን ሦስተኛ አማራጭን ያዩበት ወይም የተረዱበት መንገድ ድብልቅልቅ ያለ ነው፡፡

ኢዴፓ ወይም የኢዴፓ አመራሮች ሦስተኛ አማራጭን በተመለከተ በሚገልፁበት ወቅት አንዳቸውም ዕርዮት አለም ነው ብለው አያውቁም፡፡ አቶ ጌታነህም በጹሁፋቸው እንዲህ ብለዋል  “በእርግጥ ኢ.ዴ.ፓ ሦስተኛ አማራጭን በስም ደረጃ ወስደው እንጂ ከዕርዮት ጋር አያይዘውም፡፡ የእሱ አማራጭነት በትግል ስልትነት ብቻ ነው፡፡ የኢዴፓ ሦስተኛው አማራጭ እርስ በእርሳቸው አይተቻቹም የሚላቸውን ተቃዋሚዎችን በመተቸትና ተቃዋሚዎች አያደንቁትም የሚላቸውም የገዥው ፓርቲ የአስፋልትና የግንባታ ሥራዎች በማድነቅ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ “አማራጭ” ነው፡፡ ሌላው ስህተት ደግሞ ኢ.ዴ.ፓ ይህን “የፖለቲካ አማራጭ” ለመጀመሪያ ጊዜ በአገራችን የጀመረው መሆኑን መነገሩ ነው፡፡”

ከላይ በተገለፀው የአቶ ጌታነህ አጭር ፅሁፍ ላይ አሳባቸው ምን ያህል ድብልቅልቅ እንዳለ ማየት ይቻላል፡፡ በአንድ በኩል ኢዴፓ ሦስተኛው አማራጭን እንደ ስልት እንጂ ዕርዮት አለም ነው እንደማይል ይገልፃሉ ነገሩን ተቃዋሚን ከመተቸትና የኢህአዴግን አስፓልት ከማድነቅ ጋር አያይዘው እንደገና ስልቱን “የፖለቲካ አማራጭ” ያደርጉታል፡፡

በመጀመሪያ ለአቶ ጌታነህ ግልፅ መሆን ያለበት ነገር የሚመስለኝ ኢ.ዴ.ፓ የሚከተለው ዕርዮት አለም   ነው፡፡ ኢዴፓ የሚከተለው ዕርዮት አለም ደግሞ ሊብራል ዴሞክራሲ ነው፡፡ ከዚህም አንፃር የግለሰብ መብትን ያስቀደመ የቡድን መብት የሚያከብር በገበያም ላይ የመንግስት ጣልቃ ገብነት የማይፈቅድ ነገር ግን በግል ሴክተሩ መሸፈን ካልቻሉ በገበያ ላይ በህግ የተገደበ ጣልቃ ገብነትን የሚፈቅድ ነው፡፡ ከዚህ አስተሳሰብ አንፃር ኢ.ዴ.ፓን ካየነው መሀከል ቀኝ ዘመም መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡
ስለዚህ በመጀመሪያ አቶ ጌታነህ እነደገለፁት የኢ.ዴ.ፓ የፖለቲካ አማራጭ ሊብራል ዴሞክራሲ እንጂ ሦስተኛ አማራጭ አይደለም፡፡

ሁለተኛ “ሦስተኛ አማራጭ” ማለት ከኢ.ዴ.ፓ አንፃር ምን ማለት ነው የሚለውን እንይ፡፡ ሦስተኛ አማራጭ ስልት ሲሆን የዚህ ስልት መገለጫዎች እውቅና በመስጠት፣ በምክንያት መቃወም፣ ከእወደድ ባይነት ፖለቲካ መራቅ ወ.ዘ.ተ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከዚህ አንፃር ካየነው የኢህአዴግን አስፋልት ከማድነቅና ተቃዋሚዎችን ከመተቸት የዘለለ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡

ሦስተኛ አማራጭ ለመረዳት ሁለቱን አማራጭ በደንብ ማየት ይገባል ሁለቱ አማራጮች በአግባቡ ማየት ከቻልን ኢዴፓ የሚከተለው ሦስተኛ አማራጭ ምን ማለት እንደሆነ አዲስ ነው ወይስ የነበረ የሚለውን ነገር በግልፅ መረዳት ይቻላል፡፡
አንደውኛ አማራጭ ኢህአዴግን ነው፡፡ ኢህአዴግ የሚነግረን ከሱ በላይ ዴሞክራት እንደሌላ፤ከሱ ውጭ አማራጭ እንደሌለ ተቃዋሚዎች ህዝቡን ወዳለፈው ስርዓት የሚመልሱ እንደሆነ፤ አገሪቷንም እንደምንኖርባት እስኪያጠራጥረን ድረስ የሰማይ ገነት ያደረግልናል፡፡ አንዳንዴ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የሚተላለፉ ፕሮፓጋንዳዎች እውነት እየኖርንበት ስላለችው ኢትዮጵያ ነው እሚነግረን እስክንል ድረስ ጫፍ የወጣ ነው፡፡

ሁለተኛው አማራጭ በተቃዋሚ ዙሪያ ያለው አማራጭ ነው፡፡ ኢህአዴግ አገር እያፈረሰ እንደሆነ ለአንዳንድ ተቃዋሚዊችም በአገሪቷ ህግ እየተዳደሩና እየተገዙ የአገሪቱ ተቋም የሰጠውን እውቅና እንኳን መቀበል የማይፈልጉ ጭፍን የሆነ ጥላቻ ላይ የተመሰረተ ከምክንያታዊነት የራቀ አማራጭ ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱ አማራጮችን አንድ የሚያደርጋቸው መሰረታዊ ነገር አለ ይህውም ምክንያታዊ ያለመሆናቸው ነው፡፡

ሦስተኛ አማራጭ ከላይ ከተጠቀሰው ሁለት አማራጮች የተለየ ነው ወይ? የሚል ከሆነ ኢዴፓ የያዘው ስልት ከሁለቱ መንገዶች የተለየ መሆኑን እስካሁን የሄደባቸው መንገዶች ማረጋገጫ ናቸው፡፡ በምክንያት   መደገፍ፣ በምክንያት መቃወም፣ ለሌሎች እውቅና መስጠትና ከእወደደወ ባይነት ፖለቲካ የነፃ ነው፡፡ ኢ.ዴ.ፓ እሰካሁን በመጣባቸው መንገዶች የወሰናቸውን ትላልቅ ውሳኔዎች ብናይ ምክንያታዊ ስለመሆን ማረጋገጫ ነው፡፡

ለምሳሌ በኢትዮጵያና በሱማሊያ ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስት በአልሸባብ ላይ የወሰደውን እርምጃ ከአገር እና ከህዝብ ደህንነት አንፃር በመደገፍ፤ የአባይ ወንዝ ላይ እየተሰራ ያለውን የህዳሴ ግድብ ከህብረተሰብ ጥቅም አንፃር በመደገፍ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከኢዴፓ ርዕዮት አለም አንፃር  በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ትችት በማቅረብ ያለውን ልዩነት በግልፅ ማሳየት የቻለ ፓርቲ ነው፡፡ኢህአዴግ በ2005 ዓ.ም ምርጫ ሚዲያ ለምርጫ ቅስቀሳ በበቂ ሁኔታ እንዲከፋፈል ፍላጓት ባለመኖሩ ከዚህ ቀደም የነበሩ ክርክር መድረኮችና መንግስት ለፓርቲዎች የሚያደርገው የፋይናንስ ድጋፍ እንዳይኖር በመደረጉ ኢዴፓ በምርጫ የመሳተፍ አስፈላጊነት መርሁ እንደተጠበቀ ከምርጫ ሳይወጣ ነገር ግን ምርጫውን በአንድ ሰው ብቻ መሳተፍ የሚታወስ ነው፡፡እነዚ ሁሉም ውሳኔዎች በቂ ምክንያት ያላቸውና በጥላቻ ላይ ያልተመሰረቱ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡

ከላይ ያሉትን ሁለት አማራጮች ካየናቸው የኢዴፓ ሦስተኛ አማራጭ ምን ያህል አስፈላጊና ግልፅ መሆኑን እንረዳለን ከዚህ አንፃር ይህንን ስልት የሚከተል ሌላ ተቃዋሚ ከዘጠና ስምንት በፊት ማንም የለም ከዘጠና ስምንት በኃላ ግን ኢ.ዴ.ፓ ግልፅ አቋም ወስዶ ወጥቷል፡፡አሁን ላይ ይህን ስልት የሚከተሉ ተቃዋሚዎች ካሉ እሰየው የሚያሰብል ነው፡፡ በድፍረት እራሳቸውን ገምግመው ከስህተቶቻቸው ተምረው እንደሚያዋጣ አውቀው ይህን ስልት ከተጠቀሙ በጣም አስደሳች ነው፡፡ ኢዴፓም እሚተቻቸው ወደ ትክክለኛው መንገድ እንዲመጡ ነው፡፡ ነገር ግን እስካሁን እራሱን ገምግሞ የሄድኩበት መንገድ ስህተት ነው ብሎ አቋም ወስዶ አካሄዱን ያስተካከለ ፓርቲ አላየንም፡፡መጀመሪያ ኢዴፓ ሲል የነበረው እነሱ ወደኛ ይመጣሉ እኛ ወደነሱ አንሄድም የተሻለው አማራጭ ይሄ ነው የሚል እምነት ነበረን፡፡ ስለዚህ ተቃዋሚዎች ካለፈው ስህተቶች ተምረው አቋም ወስደው ይህን ስልት ቢከተሉ የተሻለ ነገር መፍጠር እንደሚቻል ጥርጥር የለውም፡፡

አቶ ጌታነህ ሌላው ያነሱት ሀሳብ “ሦስተኛው አማራጭ የስልት አማራጭ ነው ከተባለ ደግሞ ይህን መንገድ እነ መኢሶን በስፋት የሰሩበት እንደመሆን ኢ.ዴ.ፓ መስራችነቱን ሊወስድ አይችልም፡፡” የሚል ነው፡፡ ከላይ የተገለፀውን የአቶ ጌታነህ ሀሳብ ካየነው ሦስተኛ አማራጭ ስልት ከሆነ ከኢዴፓ ቀድሞ መኢሶን ተጠቅሞበታል ነው የሚሉን፡፡ በዚህ ሀሳብ ላይ አስተያየቴን ከመስጠቴ በፊት ይሄ አባባል የፈጠረብኝን በጎ ነገር ልግለፅ፡፡

እንደዚ አይነት የታሪክ ሽሚይ ከተጀመረ ሦስተኛው አማራጭ በህብረተሰቡ ላይ በጎ የሆነ ተፅዕኖ እየፈጠረ ያለ ስልት መሆኑን ማሳያም ይሆናል፡፡ ምክንያቱም አሁን በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚያስፈልገው የመነቋቋርና የጥላቻ ፖለቲካ ሳይሆን፤ የመከባበር፣ የመደማመጥና የድርድር ፖለቲካ ነው፡፡ ስለዚህ ህዝቡም ይሄን አካሄድ እየተቀበለው መሆኑን ብዙ ማሳያዎች አሉት የአቶ ጌታነህም ክርክር የዚህ ተፅዕኖ አንዱ ማሳያ ነው፡፡
ይህን ካልኩ የመኢሶን “ሂሳዊ ድጋፍ” እና የኢ.ዴ.ፓ ሦስተኛ አማራጭ በምን እንደሚለያይ ልግለፅ፡፡ መኢሶን ከደርግ ጋር አብሮ ሊሰራ ሲወስን ከወሰነባቸው ምክንያቶች አንዱ ደርግን ተራማጅ ነው ብሎ በማመኑ ነው፡፡ ስለዚህ ህዝባዊ መንግስት አሁን ከማለት ይልቅ አብሮ በመስራት በውስጥ ሆኖ መታገል አስፈላጊ መሆኑን በማመኑ ነው፡፡ በአስተሳሰብ ደረጃ ልዩነት ስለሌላቸው ደርግና መኢሶን በአንድ መንግስታዊ መዋቀር ውስጥ መስርታቸው ችግር የለውም፡፡

የኢዴፓን ሦስተኛ አማራጭ ካየነው ኢ.ዴ.ፓና ኢህአዴግ በአንድ መንግስታዊ መዋቀር ላይ ሊሰሩባቸው የሚችሉበት አንድ አይነት አስተሳሰባዊ መአቀፍ የላቸውም የኢ.ዴ.ፓን ሊብራል ዴሞክራሲ አስተሳሰብና የኢህአዴግን አብዮታዊ ዴሞክራሲ አብረን ካየነው “ዱባና ቅል ለየቅል” ነው የሚሆነው፡፡   ኢ.ዴ.ፓ በግለሰብ መብት ሲጀምር ኢህአዴግ በቡድን በገበያ ላይም ያለው የአመለካከት ልዩነት ሰፋ ያለ ነው፡፡ ስለዚህ እንደ ደርግና መኢሶን በአንድ መንግስት አብሮ ሊያሰራ የሚችል የአስተሳሰብም ሆነ የአደረጃጀት መዋቀር አንድነት የለም፡፡ ስለዚ ኢዴፓ ኢህአዴግን በምርጫ ለማሸነፍ የአስተሳሰብ አማራጮቹ በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ እና አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ኢዴፓ እንደ መኢሶንና ደርግ አብሮ መስራት ባይቻልም፡፡ በአገራዊ የጋራ ጉዳይ ላይ አብሮ ይሰራል መንግስት እየሰራ ያለው በጎ ነገር ካለም ጥቅሙ ለህዝቡ ነውና፡፡ ለተሰራው ነገር እውቅና ይሰጣል ድጋፍ ያደርጋል፡፡ይሄ ስልትና የመኢሶን “ሂሳዊ ድጋፍ” ይለያያል፡፡ እስከ አሁን እንደ ኢዴፓ በግልፅ አቋም ወስዶ ሦስተኛ አማራጭ ባይል የሦስተኛ አማራጭ መገለጫ የሆኑትን ምክንያታዊነት እውቅና መስጠት በድርድር ማመን ወ.ዘ.ተ በስራ ላይ እየተጠቀመ ያለ ፓርቲ አይቼ አላውቅም ነገር ግን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ስለነዚህ ነገር አስፈላጊነት አልፎ አልፎ መናገር ጀምረዋል፡፡ ይህ የተጀመረው ደግሞ ኢዴፓ በግልፅ ይህንን አማራጭ ስልት ይዞ ከመጣ በኋላ ነው፡፡

አቶ ጌታነህ ኢዴፓ ጀማሪ አይደለም በዛ ላይ ደግሞ “አንድነትም መኢአድም፣ሰማያዊ ፓርቲም ሂስም ድጋፍም ነው፡፡ እሚያደርጉት ኢዴፓ ብቻ አይደለም” የሚል ሃሳብ አንስተዋል፡፡ እንደዛ ከሆነ ማን ጀመረው በእርግጥ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዚህ አይነት ድጋፍ መስጠት ላለባቸው ነገር ድጋፍ በመስጠት መተቸት ያለበትን ነገር ይተቻሉ ወይ? የሚለውን ጥያቄ ወደ ጎን ትተን አቶ ጌታነህ የገለፅዋቸው ፓርቲዎች ኢዴፓ የሦስተኛ አማራጭ መርሆች የሆኑትን ነገሮች በተናጥል መሪዎች አስፈላጊ እንደሆኑ ያነሶቸዋል እንጂ እንደፓርቲ አቋም ወስደው መርሀቸው አድርገው ሲሰሩባቸው አላየንም፡፡ ወደፊት ወደዚህ መንገድ እንደሚመጡ የታወቀ ነው፡፡ ምክንያቱም አለም ሁሉ የተቀበለው መንገድ ስለሆነ ነው፡፡

መኢሶን ከደርግ ጋር ሲሰራ የነበረው በአንድ መንግስት ውስጥ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የኢዴፓ ሦስተኛ አማራጭ ስልት ግን እንደ መኢሶን ከኢህአዴግ ጋር በአንድ መንግስት መዋቅር ውስጥ ለመስራት ሳይሆን ከዛ በመለስ ባሉ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት ማለት ነው፡፡
በመጨረሻ አቶ ጌታነህ የፃፉት ነገር ይሄን ይመስላል “መለስ ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስራች ወይም ብቸኛው “ደብተራ ተደርገው እንደሚወሰዱት ሁሉ አቶ ልደቱ በቅጥ ያልተተረጎመውንና ከፓርቲያቸው ጋር ግንኙነት የሌለው  “ሦስተኛ አማራጭ” መሀንዲስ ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ ምርጫ አብቅቶ ወይም ለትምህርት ወደ ውጭ ወጥተው በነበሩበት ወቅት ደግሞ አማራጭነቱ ይረሳል፡፡ አሁን ደግሞ አቶ ልደቱ ወደ ፖለቲካ ሲመለሱ ልክ እንደ አብዮታዊ ዴሞክራሲ በስም ደረጃ ብቻ “ሦስተኛ አማራጭ አብሯቸው ብቅ ብሏል፡፡”

ከላይ ያለውን የአቶ ጌታነህ ሀሳብ ካየነው ሁለት ነገር እንረዳለን አንደኛው ሦስተኛ አማራጭ በቅጥ እንዳልተተረጎመ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አቶ ልደቱ ሳይኖሩ ሦስተኛ አማራጭ አብሯቸው እንደሚጠፋ ሲመለሱ አብሯቸው እንደሚመለስ፡፡

አቶ ጌታነህ በቅጥ ያልተተረጎመ ያሉት ሦስተኛ አማራጭ ስልት በአግባቡ እደተተነተነ ላረጋግጥልዎት እወዳለሁ የኢንተርኔት አክሰስ ካሎት www.edponline.org ቢገቡ የኢዴፓን መረጃዎች ያገኛሉ ሦስተኛ አማራጭም በደንቡ እንደተተነተነ ይረዳሉ፡፡ ይህ አማራጭ ከሌሎት ጊዮን ፋርማሲ አካባቢ ያለው የኢዴፓ ጽ/ቤት ቢመጡ ሰነዶቹን ልንሰጥዎ እንችላለን፡፡

ሳያነቡት ወይም አንብበውት ስላልገባዎት ነገር በድፍረት መፃፍ የእርሶን ማንነት የሚያሳንስ እንዳይሆንብዎት ለሌላም ጊዜ ጥንቃቄ ቢያደርጉ መልካም ነው፡፡ሌላው ሦስተኛ አማራጭ አቶ ልደቱ ሲኖሩ የሚነሳ አቶ ልደቱ ሳይኖሩ የሚጠፋ አድርገው የገለፁበት መንገድ ነው፡፡

ሦስተኛ አማራጭ የኢዴፓ የትግል ስልት ነው፡፡ ማለት የኢዴፓ ጠቅላላ ጉብኤ አምኖበት በዚህ የትግል ስልት አማካኝነት ትግሉ መቀጠል እንዳለበት ለአመራሮቹ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ስለሆነም የትኛውም የኢዴፓ አመራር ከዚህ ቀደም የነበረውም አሁንም ያለው በሦስተኛ አማራጭ ስልት ትክክለኛነት ጥርጥር የለውም፡፡ ለዚህ ህብረተሰቡ ስለሦስተኛ አማራጭ ከዚህ የበለጠ እንዲረዳ አሁን ያለውም አመራር ጥረት ያደርጋል፡፡ አቶ ልደቱም ቢኖሩም ባይኖሩም አመራሩ የሚከተለው የትግል ስልት እንደሆነ ሊረዱት ይገባል፡፡ነገር ግን አቶ ልደቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ካላቸው ከፍተኛ ቦታ አንፃር ስለ ሦስተኛ አማራጭ ስልት ሲናገሩ የበለጠ የሚሰሙ ከሆነ አሁንም የኢዴፓ አላማ የሦስተኛ አማራጭ ስልት ከዚህ የበለጠ ህብረተሰቡ እንዲረዳው ነውና መ
ካም አጋጣሚ ነው፡፡

በመጨረሻም አንብበው ተረድተው እንደዚ አይነት ድብልቅልቅ ያለ አቀራረብ ሳይሆን ሦስተኛ አማራጭ የሚለው ስልት አያዋጣም የሚል ክርክር ቢያነሱ በጎ ነው፡፡አሁንም ላረጋግጥልዎት የምፈልገው ኢዴፓ አንድም ቀን ሦስተኛ አማራጭ የምከተለው የፖለቲካ ዕርዮት ነው ብሎ አያውቅም፡፡ እርሶም እንዳሉት ኢዴፓ ስልት ነው ይላል ብለዋል ስለዚህ ክርክሩ መሆን ያለበት ይህ ስልት ያዋጣል ወይም አያዋጣም  የሚል ነው፡፡ ሃሳቡ መነሳቱ በጥቅሉ ክፋት የለውም ነገር ግን ፁሁፍዎት ከጥላቻ የፀዳ ቢሆንና ሀሳቦቹ ላይ ቢያተኩሩ የበለጠ ለመማማር እድል ይሰጣል ሦስተኛ አማራጭ ወደ ውጤት የሚወስደን ብቸኛው የፖለቲካ የትግል ስልት ነው፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter