ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርላማ አባልና መፅሀፋቸው

Ermias Balkewኤርሜያስ ባልከው  የኢዴፓ ድርጅት ጉዳይ ኃላፊ

PDF በአገራችን ከተካሄዱት ምርጫዎች መካከል ምርጫ 1997 ዓ.ም የተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ልዩ ታሪካዊ ምርጫ ነበረ ማለት ይቻላል፡፡  በዚህ ታሪካዊ ምርጫ ከሚነሱ የምርጫ ሀይሎች አንዱ ደግሞ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ የተባለው የአራት ፓርቲዎች ስብስብ ነው፡፡ ይህ ምርጫ ብዙ አስተማሪ አሳዛኝ ክስተቶችን ያስተናገደ ምርጫ እንደመሆኑ በዚህ ዙሪያ የተለያዩ መጽሀፎችና ፁሁፎች ተፅፈዋል፡፡ ወደፊትም ሊፃፍ ይችላል፡፡ ለዛሬም ፁሁፍም ምክንያት የሆነው የነፃነት ዋጋው ስንት ነው በሚል እርእስ በአገራችን ፓርላማ ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ የፃፉትን መፅሀፍ ሳነብ ስለ 97 ምርጫ  ያሰፈሩት አስተያየት አይቼ ነው፡፡

አቶ ግርማ ካሰፈሮቸው አስተያየት ውስጥ በተለይ አቶ ልደቱ አያሌውን ለብዙ ጊዜ ደጋግመው አንስተዋል በጣም ያሳዘነኝ ነገር ግን አቶ ግርማ ብዙ ጊዜ ፖለቲካውን ስለ ማዘመን ያወሩ ይፅፉ ስለነበር ማዘመኛ መንገዳችን እራሳቸው እንኳን ወይ አያውቁትም አልያም ስላልገባቸው ነገር እንደሚያወሩ ሳውቅ አዘንኩ ስለ አቶ ልደቱ ሲፅፉ በመረጃ ወይም በአመክንዬ አቶ ልደቱ የወሰዱት አቋም ተገቢ እንዳልነበረ ከማስረዳት ይልቅ ስለማያውቁት ነገር ተራራ አሉባል ለቃቅሞ መፅሀፍ አድርጎ ማውጣት የማይጠበቅ ሆኖ ስላገኘሁት ነው፡፡ በመፃሀፋ ላይ የሰፈሩት የአቶ ግርማን አስተያየት መተቸት የሚመጥን ነው ብዬ ባላምንም አቶ ግርማ በመጥፎ የታሪክ አጋጣሚ ብቸኛው የህዝብ ተወካዬች ምክር ቤት ተቃዋሚ አባል እንደመሆናቸው መጠን ሰውየውን አማራጭ ከማጣት የሚያዬቸው ሰዎች እንደሚኖሩ በመገመት ይችን ፁሁፍ ለመፃፍ ወሰንኩ፡፡

እኔ በተቻለ መጠን መፅሀፋቸውን በትግስት በፅሞና አንብቤ ተራ ዘለፋ ሳይሆን ፅሑፋቸው ላይ ያቀረቡትን አስተያየት ጠቅሼ የኔን አስተያየት ለመፃፍ ወደድኩ፡፡ አንዳንድ ቃላቶችን በቀጥታ በመጠቀም ያስቀመጥኩኝ ሲሆን እነዚ ቃላቶችን የተጠቀምኩት አካፋን አካፋ ማለት ይገባል ብዬ ስላሰብኩ ነው፡፡

አቶ ግርማ ከየት የመጡ ሰው ኖት የሚል ጥያቄ በዝቶባቸዋል መሰለኝ አዲስ አይደለሁም ሀረግ የሚመዘዘው ከቅንጅት ነው፡፡ ብለው ለማስረዳት ጥረት አድርገዋል፡፡ የቅንጅት አመራር ለመሆን በጥቂት ነውያመለጥኩት ለዛውም በነ ዶ/ር አለማየሁ አረደ ሴራ መሆኑን ነግረውናል በእጩነትም ልቀርብ ብዬ በመስፈርቱ ተሸነፍኩ ከማለት ይልቅ ሌላ ምክንያት ለመፈለግ ጥረዋል፡፡ አቶ ግርማ መፅሀፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፡፡ ‹ዘግይቼ በሂደት እንደተረዳሁት ዶ/ር አለማየሁ በቅንጅቱ የሥራ አስፈፃሚ የመጨረሻ አራቱ ውስጥ ለመግባት ወስኖል፡፡› በዚህ ጉዳይ ላይ ከአቶ ልደቱ ጋር ስለሚይዙት ሁለት የአመራር ቦታዎች ድርድር ጀምረዋል፡፡ በተለይ የተቀዳሚ ሊቀመንበርነት እና የፓርቲው ዋና ፀሀፊነት ቦታ ከያዙ የቅንጅት ሁሉ ነገር እንደያዙ በማሰብ ዶ/ር አለማየሁ ምርጫ ባለመወዳደር ያጡትን ቦታ ከልደቱ ጋር በመስማማት የፖለቲካ ስልጣን በመያዝ መሪውን ለመዘወር ወስኗል፡፡ልደቱም ከዶ/ር አለማየሁ ጋር ከተስማማ ቅንጅት ውስጥ አድራጊ ፈጣሪ ለመሆን የሚከለክለው እንደሌለ አምኗል፡፡›› (ገፅ 31)

ከላይ አቶ ግርማን አስተያየት ሳናይ በመጀመሪያ ስለራሳቸው የቅንጅት ታሪክ ተጋሪነት ስለ ፖለቲካ ተሳትፎቸው ሲነግሩን ይቆዩና እንደምንም ብለው እሳቸው ከኢድሊ ወደ ቅንጅት ከ12 ሰዎች አንዱ ሆነው መሄድ አለመቻላቸውንና የአቶ ቸኮል ከአምስቱ የኢድሊ ቅንጅት ስራ አስፈፃሚ አለመሆን ጋር አገናኝተውት ይሄን ከአቶ ልደቱ ጋር አገናኙት፡፡ ይሄ አቶ ግርማ እኔም በታሪኩ ውስጥ አለሁበት የሚል የታሪክ ሽሚያ ውስጥ ነው ያሉት ወይ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል በሌላ መንገድ አቶ ልደቱ ከኢዴፓ ወደ ቅንጅት በመጨረሻ መስከረም 1998 ዓ.ም በሰሜን ሆቴል በተደረገው ጠቅላላ ጉባኤ አቶ ልደቱ ወደ ቅንጅት ኢዴፓን ወክሎ የመጀመሪያ ሰው ሆኖ እንዲሄድ የተደረገው በስንት ልመናና ለቅሶ ጭምር ነበር፡፡

ይሄንንም ለ2002 ምርጫ ኢዴፓ ለምርጫ ቅስቀሳ ከተጠቀመባቸው ሲዲዎች መመልከት እንደሚቻል አቶ አንዶለም አራጌ የመድረክ /አንድነት አመራር ሳይቀር በወቅቱ ደም ከሆነ ደም ትከፍላለህ እባ ከሆነም እዲ ታለቅሳለህ ከዚህ በኋላ ጥያቄህን ማሳካት አለብ እሰ ከማለት ደርሰው በጉባኤው ጫና ያለፍላጎታቸው በጉባኤው ውሳኔ ነው፡ ወደ ቅንጅት አመራር ሆነው የሄዱት፡፡ አቶ ልደቱ ከዶ/ር አለማየሁ ጋር የቅርብ ወዳጅ እንዳልነበሩ በቅንጅት ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸው ሰዎች በደንብ የሚያውቁት ነው፡፡ እሄ እንግዲህ አቶ ግርማ የፈጠሩት አዲስ አሉባልታ መሆኑ ነው፡፡   አቶ ግርማ በሌላ በኩል ‹ዶ/ር ብርሃኑ፣በሙሉነህ፣ስለሺ አቀናባሪነት በተሰራ ሴራ ዶ/ር አለማየሁ የፈለጉትን በቅንጅት ከፍተኛ የፖለቲካ ቦታ የማግኘት ምኞት ምናልባት ከልደቱ ጋር ቁልፍ ቦታዎች በጋራ ለመቆጣጠር እና ቅንጅቱን በተለየ አቅጣጫ ለመውሰድ ያወጡት እቅድ ሳይሳካ እንዲቀር ተደረገ፡፡

ልደቱ በምርጫው ለብቻው ቅንጅት ዕውን እንዳይሆን በታሪክ አሳፋሪ የሆነውን ተግባር ፈፀመ፡፡( ገፅ 35-36) አቶ ግርማ በገባቸው ልክ አቶ ልደቱና የዶ/ር አለማየሁ ሴራ ከሸፈ ብለው የተሰማቸውን ፅፈዋል እንደሚታወቀው አቶ ልደቱ በኢዴፓ በኩል ወደ ቅንጅት የተላኩት እንዴት እንደሆና ለመግለፅ ሞክሪያለሁ ከላይ ያለውን ብቻም ሳይሆን ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም አጋቱኒ በሚል መፅሀፋቸው ስለ አቶ ልደቱ ሲገልፁ አቶ ልደቱ የድርጅቱን ስራ እንደማሰሩ ዶ/ር ብርሃኑ ያንን ቀድመው ቢመስራታቸው ብዙ ውሳኔ ማስወሰን እንደቻሉ ገልፀዋል፡፡ እዚህ ላይ ከአቶ ግርማም እንደሚሉት   አቶ ልደቱ ድርጅታዊ ስራ ሰርተው ቢሆን ኖሮ ለነ ዶ/ር ብርሃኑ ልክ የሆነው ለአቶ ልደቱ ሲሆን ስህተት ሊሆን የሚችልበት አሳማኝ ምክንያት ማቅረብ እሚቻል አይመስለኝም፡፡ ሌላው አቶ ግርማ እንደሚሉት አቶ ልደቱ ለብቻቸው ቅንጅት እውን እንዳይሆን ማድረጋቸውን ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ አቶ ልደቱ በደማቅ ቀለም የሚፃፍ ታሪክ በመስራት ለኢትዮጵያ ህዝብ ባለውለታ ናቸው ማለት ነው፡፡ ትውልድ የሚዘክራቸው ቅንጅት በጣም ትልቅ የተባለ ስብሰባና በብዙ ህዝብ ዘንድም እምነት የተጣለበት ነበር ይህ ስብሰባ በአንድ በአቶ ልደቱ የሚፈርስ ከሆነ ጠንካራ መዋቀር ያለውን ኢህአዴግን እንዴት መቋቋም ይችላል፡፡ አቶ ግርማ አፈረሰው ያሉት አንድ ልደቱን ነው ቅንጅት በመጨረሻዎቹ ስብሰባ ላይ አቶ ልደቱንና አቶ ሙሼን አባርሪያለሁ ብሎ ነበር ያውሳኔ ታዲያ ለምን ቅንጅትን ከመፍረስ አላዳነም ነበር ከእስሩስ በኋላ መለያየቱ ለምን ቀጠለ?  አንድነት ከተመሰረተም በኋላ የተፈጠረው ነገር ሁሉምክንያት ምን ይሆን? አቶ ልደቱ ይሆኑ? ድሮም መፍረስ ነበረበት አቶ ልደቱም ጎሽ አበጀህ ተብለው ሊሸለሙ ነበር የሚገባው እኔ አቶ ግርማ በአንድ ሰው የሚፈርስ ያን አይነት እንቅስቃሴ የፈጠረ ስብሰባ መንግስት ሆኖ አገርን እንዴት ሊያስተዳድር ይችላል ብለው ምን አይነት መከራከሪያ ሀሳብ እንደሚያቀርብ አይገባኝም፡፡ በመቀጠል በፓርላማ ውስጥ ብቸኛው ተቃዋሚ አቶ ግርማ በመፃሀፋቸው ካቀረቡት ሀሳብ አንዱ ከአቶ ልደቱ መፅሀፍ የተወሰደ ነበር፡፡ “በምርጫ 97 ወቅት ቅንጅት በእርግጠኝነት ካሸነፋቸው በርካታ የፓርላማና የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች በተጨማሪ የአዲ አበባ መስተዳደርን ለመረከብ ፍቃደኛ ሆኖ ቢሆን ኖሮ የመንግስት ስልጣን ከያዘው ከኢህአዴግ መንግስት ጋር እየተመካከሩ መስራት መብቱ ብቻም ሳይሆን ግዴታም ይሆን ነበር፡፡” (መፅሄት ገፅ14) ይህ ከላይ የተጠቀሰው የአቶ ልደቱ መፅሃፍ ውስጥ የሰፈረው ነገር ውሸት ነው ቅንጅት ፓርላማ ላለመግባት አልወሰነም ይሉናል፡፡ “ሃቁ ግን ቅንጅት ግን የወሰነው ፓርላማ እንግባ አዲስ አበባ እንረከብ የሚል ነው፡፡› ‹በግልባጩ ግን ኢህአዴግ ፓርላማ እንዳይገቡ አጥር ያጥርባትና አዲስ አበባን አላስረክብም ያለበት መሆኑ ነው፡፡› ኢህአዴግ ይህንን በህዝቡ ዘንድ ለማስረፅ በስፋት የተጠቀመበት በሞኖፖል በያዘው ሚዲያ አማካኝነት ነው፡፡ (ገፅ 42) አቶ ግርማ ይሄንን ብለው ዝቅ ብለውም ለኢህአዴግ የቀረበው 8 ጥያቄ ብቻ እንደሆነና እነዛን ስምንት ነጥቦች አስፈረቀል እንደኔ ግን አቶ ግርማ የመረዳት ችግር ከሌለብቸው በስተቀር ፓርላማ እገባለው ማለት እና ስምንት ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጦ እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ካልተሙዋሉ ፓርላማ አልገባም ማለት ያላቸው ልዩነት ለአቶ ግርማ ካልሆነ በስተቀር ለሁሉም ሰው ግልፅ ነው፡፡

ስለዚህ አቶ ልደቱ መድሎት ላይ የፃፉት አቶ ግርማ የጠቀሱትን ሀሳብ የቱ ጋር እንደሆነ ስህተቱ ቃል በቃል እያነበብኩ ብፈልግ ላገኝ አልቻልኩም ስህተት ሆኖ ያገኘሁት የአቶ ግርማ የመረዳት ችሎታን ነው፡፡ በተጨማሪ አቶ ግርማ ከላይ እንደገለፁት ኢህአዴግ ፓርላማ እንዳይገባ አጥር እንደሚያጥር ይህንንም ያሰረፀው በሞኖፖል በያዘው ሚዲያ እንደነበር ይነግሩናል፡፡እንደዚህ ከሆነ ኢህአዴግ ቅንጅት ፓርላማ እንዲገባ አይፈልግም ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ኢሄንን ቀድሞ ተረድቶ አቅጣጫ ማስቀመጥ የተሸለ ውሳኔ መወሰን ተገቢ እንደነበር አቶ ግርማ የሚያምኑ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን አቶ ግርማ ከፍተኛ የሆነ የመረዳት ችግር ስላለባቸው ፓርላማ መግባት እና አለመግባት ህዝቡን ማማከር ትክክል ነው ብለው እንዲህ ሊሞግቱን ይሞክራሉ መከራከሪያ ሀሳባቸውም ይህንን ይመስላል፡፡ ‹‹ፓርላማ እንግባ ወይም አንግባ በሚል ከህዝብ ጋር ሲደረግ የነበረው የህዝብ ውይይት አስመልክቶ በመጀመሪያ ህዝብ ለውሳኔ ማሳተፍ ለቅንጅት ሲሆን ወንጀል ይሆናል፡፡›› ኢህአዴግ ግን ቡርትካን ሚደቅሳን ማሰር ተገቢ ነበር በሚል ለህዝብ ግንዛቤ ለማስጨበጥ በመላው ሃገሪቱ ውይይት ሲያደርግ ነበር፡፡ ነገር ግን ለኢህአዴግ ሲሆን ዴሞክራሲያዊ ነው፡፡

ለማንኛውም በእኔ እምነት “ፓርላማ እንግባ ወይስ አንግባ›› የሚለው ውይይት የተካሄደበት መሰረታዊ ምክንያት ልክ ነበር” (ገፅ 46) ከላይ የአቶ ግርማን ሃሳብ ሳነብ በጣም አፈርኩ ምክንያቱ ደሞ ከላይ የተፃፈው ነገር የተለየ ስለሆነ ነው፡፡   ምን ልወስን ብሎ ህዝብን ማማከርና አንድን ውሳኔ ወስኖ ስለውሳኔው ለማስወዳት ህዝብን ማናገር ሁለቱ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ከላይ ከአቶ ግርማ ሃሳብ ስንረዳ ኢህአዴግ ቡርትካንን ስለማሰሩ ተገቢነት ነው ግንዛቤ ለማስጨበጥ ውይይት አደረገ ያሉት ይህ ማለት ከውሳኔ በኋላ፡፡ ቅንጅት ደግሞ ፓርላማ ልግባ ወይስ አልግባ በማለት ነው ህዝብን ያወያየው ይህ ማለት ከውሳኔ በፊት እንደ ፖለቲካ መሪ የትኛውንም ውሳኔ መዝኖ እንደየ ተጨባጭ ሁኔታው መወሰንና ከውሳኔ በኋላ ህዝብን ስለ ውሳኔው ማስረዳት ተገቢም ትክክለኛም ነው፡፡ ከውሳኔ በፊት ግን ምልወስን ብሎ ማማከር ልክ ሊሆን የሚችለው ለአቶ ግርማ ብቻ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች አሁን ላይ የሚስማሙበት ቅንጅት ከሰራቸው ስህተቶች እንደ ፓርላማ መግባት እና አለመግባት ህዝቡን ማማከሩ ነው፡፡

አንድ የቅንጅት እጩ በብዙ ሺ ሰው ተመርጦ አዳራሽ ውስጥ በተደረገ ስብሰባ ሁለት ሺ ሰው ለዛውም እነዛ ሰዎች የማን እንደሆኑ በማይታወቅበት ሁኔታ ኢህአዴግ ያሰማራቸው ስለመሆኑም ማረጋገጥ በማይቻልበት ሁኔታ ውሳኔው የመራጩ ህዝብ ነው ማለት ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ ቅንጅት እሄንን ያገንዘበ ትግሉን ወደፊት ሊያስኬድ የሚችል ውሳኔ መወሰን ይገባው ነበር አቶ ግርማ ስለ ልደቱ ፓርላማ መግባት አለመግባትውሳኔ ሁለት ነገር አቅርበዋል አንደኛው “አቶ ልደቱ መፅሄት በተባለው መፅሀፍ ቅንጅት ፓርላማ ቢገባ ጥሩ ነበር ብሎ እኔ እንግባ ብዬ ነበር የሚል መልዕክት ያስተላልፋል፡፡ ”ትንሽ ወረድ ይሉና ሁለተኛውን ሀሳብ እንዲህ ይጠቅሳሉ “ከዚህ በተጨማሪ በጋዜጣ ላይ ፓርላማ የሚገባው በቅንጅቱ ውሳኔ ነው ብሎ መግለጫ ሲሰጥ ነበር እንጂ በግሌ የተለየ ሃሳብ ነበረኝ ብሎ አያውቅም፡፡” (ገፅ 49) በመጀመሪያ ላይ የጠቀስኩት ሃሳብ ላይ በእርግጥም አቶ ልደቱ ፓርላማ መግባት ላይ የነበራቸው አቋም ፓርላማ መግባት እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ ፓርላማ መግባት አለመግባት ክርክር ላይ ኢዴፓን ወከወለው ቅንጅት ስራ አስፈፃሚ ከሆኑት ከ5 ሰዎች ውስጥ 3ስቱ ማለትም አቶ ሙሼ ሰሙ  አቶ አብድራማን  አህመዲን እና ዶ/ር ሙላላለም ታረቀኝ ሲከራከሩ የነበርው ፓርላማ መግባት የተሸለ ጥቅም እንዳለው ነው፡፡ በተለይ አቶ ሙሼ ዶ/ር ብርሃኑ ነፃነት ጎህ ሲቀድ ብለው በፃፉትም መፅሀፍ ሻይ ቡና እረፍት ላይ አቶ ሙሼ አግዘን እንጂ ብለዋቸው እንደነበር ፅፈዋል ዶ/ር ብርሃኑ ለአቶ ሙሼ የሰጡት መልስ ምንም መፀሀፋቸው ላይ ዋሽተው ቢያስቀምጡም የቅንጅት ሌሎች አመራሮች ለሚዲያ ከስብሰባ እያቆረጡ እየወጡ ይሰጡት የነበረውም አስተያየት እነ ልደቱ ፓርላማ ካልገባን እያሉ ነው የሚል ነበር፡፡

ስለዚህ በወቅቱ የአቶ ልደቱም ሆነ የኢዴፓ አመራር አቆም ፓርላማ መግባት ነበር፡፡ በሁለተኛው የአቶ ግርማ ሀሳብ አቶ ልደቱ በቅንጅት ውሳኔ ነው፡፡ ፓርላማ የገባሁት እያለ በሚዲያ ያወራ ነበር ይሉናል፡፡ አቶ ግርማ የትኛው ጋዜጣ ላይ አቶ ልደቱ ፓርላማ የምገባው በቅንጅት ውሳኔ እንዳሉ አልገለፁም አቶ ልደቱም እንደዚህ አይነት መግለጫም ሰጥተው አያውቁም አቶ ልደቱ ወደ ፓርላማ የገቡት ከታህሳስ በኋላ ነው፡፡ ፓርላማ የሚከፈተው ደግሞ መስከረም ላይ ነው አቶ ልደቱ እስከዛ ድረስ ሳይገቡ የቆዩት የቅንጅት ውሳኔ ፓርላማ ላለመግባት በመሆኑ ነው፡፡ የኢዴፓ አመራሮች ፓርላማ እንዲገቡ የተወሰነው ኢዴፓ በጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ ነው፡፡ ውሳኔው ፓርላማ እንዲገባ በ3ወር ጊዜ ውስጥ ፓርላማ በመገባቱ የተገኘው ውጤት ታይቶ ውጤቱ የሌለው ከሆነ ተመልሰው እንዲወጡ በመወሰኑ ነው፡፡ በሂደቱም ኢህአዴግ ለመደራደር ፍቃደኛ ሆኖ በመገኘቱ በፓርላማ ለመቀጠል ተወስኗል፡፡ አቶ ግርማ ያላነበቡት በእርግጠኛነት ከሌሎች በወቅቱ ከነበሩ አመራሮች ያልሰሙትን ነጭ ውሸት መፅሀፍ አድርጎ መፃፍ እሚያሳፍር ነው፡፡ ከማለት ውጪ ምን ይባላል፡፡ በመጨረሻ አቶ ግርማ ፓርላማ መግባት ላይ ቅንጅት ስለወሰነው ውሳኔ እንዲ ይሉናል “ በግሌ ቅንጅት በወቅቱ በነበረው ነባራዊ ሁኔታ ኃላፊነት የሚሰማው ውሳኔ እንደወሰነ አምናለሁ ምንም ስህተት የለውም ልል ግን አልችልም፡፡” አንዳንድ ነገሮች ከኩነታ በኋላ እንዲ ቢሆን ማለት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ቅንጅት ያስቀመጣቸውን ስምንት ነጥቦች ፓርላማ ገብተው ቢያነሳቸው ሊባል ይችላል፡፡ ይህንን ግን ማነፃፀር የሚኖርበት በዚያን ጊዜ ከነበረው ከህብረተሰቡ ድምፃችን ይከበር ከሚለው ስሜት ጋር በቅርብ መታየት ይኖርበታል፡፡›› (ገፅ 51) ከላይ ያለውን የአቶ ግርማን ሃሳብ ስናይ ቅንጅት የወሰነው ውሳኔ ከህዝብ ድምፅ ይከበር ከሚለው ስሜት አንፃር ተገቢ ነው ስህተት ሊባል ግን አይችልም የሚል ቃና አለው አቶ ግርማ አሁንም ብዙ የቅንጅት አመራሮች ዶ/ር ያእቆብ ሃይለማርያምን ጨምሮ ስህተት ሰርተናል ብለው የተቀበሉነትን ነገር አቶ ግርማ አሁን ድረስ ለሳቸው ገና እንደተምታታባቸው ነው፡፡ ስህተት ነበር ለማለት ተናንቆቸዋል፡፡

ከፖለቲካ አመራሮች የሚጠበቀው በተቻለ መጠን የወደፊቱን ገምቶ የተሸለ ውሳኔ ወስኖ ደጋፊዎቻቸውን በዛ አግባብ መምራት ነው፡፡ እነ አቶ ልደቱ ያደረጉት አሁን ላይም ሁነን ስናየው የተሸለ ደረጃ ላይ ሊያደርስ የሚችል ውሳኔ እንዲወስን ነበር ጥረታቸው አልተሳካላቸውም እንጂ፡፡ በመጨረሻ የምለው ነገር ቢኖር አቶ ግርማ በፃፉት መፀሃፍ ውስጥ የተገነዘብኩት እርሳቸውም በመግቢያው ላይ እንዳሉት ከየት የመጣነህ የሚል ጥያቄ ጭንቅላታቸውን ያዞረው ይመሰለኛል ስለዚህ በዚህ ጡዘት ተነስተው በቅንጅት ውስጥ አለሁበት እከሌ ያቀኛል እከሌ እንደዚህ ባይል የቅንጅት መሪ እሆን ነበር የሚል ነገር ውስጥ ገብተዋል፡፡ ከዛም አልፈው ስለማያውቁት የነበሩ ሰዎች እንኳን በአግባቡ ያልጠየቁበትን ወይም ስለዛ ነገር በበቂ ሁኔታ ባለነበቡበት ሁኔታ እኔ ትልቅ ነኝ በሚል እሳቤ በጭፍን የሰውን ስም ለማጥፋት ወስነዋል፡፡ በሂደቱ ውስጡ የነበሩት የቅንጀት አመራሮች የተለያዩ መፀሃፍ እንደየ ሃሳባቸው ፅፈዋል እንደ አቶ ግርማ አይነት የወረደ ግን አይደለም፡፡ ስለቅንጅት አልያም በ97 ስለነበረው የፖላቱካ እንቅስቃሴ ማንም ሰው መፀሃፍ ሊፅፍ ይችላል ግዴታ ለምን መሪ አልነበርኩም ሊባል አይችልም አቶ ግርማም ስለቅንጅትም ሆነ ስለ97 ምርቻ ለመፃፍ የቅንጅት ከፍተኛ አመራር መሆን አይጠበቅባቸውም ነገር ግን በተቻላቸው መጠን ዋና ተሳታፊ ከነበሩ ሰዎች የተፃፈ መፀሃፍ በደንብ ማንበብ የነበሩ ሰዎችንም መጠየቅ ለፃፉት መፀሃፍ የተሞላ እንዲሆን ይጠቅማቸው ነበር፡፡አቶ ግርማ በሆነ መጥፎ የታሪክ አጋጣሚ አልያም በሌላ ከፓርላማ የፊት ወንበር የመቀመጥ እድል አግኝተዋል በዚህ ብዙ የሚዲያ እድል አላቸው፡፡ (ከሌሎች አንፃር ሲታይ ማለት ነው) ይሄ ለእሳቸው እውቅና የፈጠረ በጎ አጋጣሚ ነበር፡፡ በዚህ እድል የበለጠ ከመጠቀም ምልቅ ከኔበላይ አዋቂ የለም በሚል ተኮፍሰዋል፡፡ የፓርቲያቸውም ሌሎች አመራሮች ፓርላማ የመግባት እድል አጊኝተው ቢሆን ኖሮ የእሳቸው ትክክለኛ ቦታ ከኋላ ይሆን ነበር፡፡ የአቶ ግርማ ማንነት በሚሰጣቸው ኢንተርቪውም በጉልህ ይታያል፡፡ ለምሳሌ በሐምሌ 3 ቀን 2005 ዓ.ም እትም ላይ በቁጣ የሚሰጡት መልስ ለሳቸው ምንነት  መገለጫ ነው፡፡ ለነገሩ አቶ ግርማም ቢሆኑ አልሰበቁንም በመፅሀፋቸው መደምደሚያ አካባቢ ባህሪዬ “ለወታደርነት ይቀርባል” ብለዋል አሁን ባላቸው ባህሪ ፓለቲካ መሪ ከመሆን ይልቅ እሳቸው ባህሪያቸውን እንደገለፁት ወታደር ቢሆኑ ባልልም በሙያቸው ቢያገለግሉየበለጠ ሀገራቸውን እንደሚጠቅሙ ይሰማኛል፡፡ በፖለቲካ መሪነታቸው ለመቀጠል ግን ለመማር በጣም ዝግጁ መሆን አለባቸው በዚህ ከቀጠሉ አቶ ግርማን የፓርላማ ቆይታቸው ሲጠናቀቅ በፖለቲካው መድረክ ላይ ማየት ዘበት ነው ጠሚሆነው፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ካገኘሁት በሌሎች የመፅሀፍ ክፍሎች አስተያዬቴን  አካፍላለሁ፡፡ ለዛሬው የብቸኛው የተቃዋሚ የፓርላማ ተወካይና መፀሀፋቸው እይታዬን በዚህ አበቃው፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter