ወ/ት ሣባ ተሾመ ደምሴ አጭር የሕይወት ታሪክ

Saba Teshomeየሐዘን መግለጫ

ወ/ት ሣባ ተሾመ ከአባቷ ከኮረኔል ተሾመ ደስታ እና ከእናቷ ከወ/ሮ አልማዝ ግርማፂዎን በአዲስ አበባ ከተማ ሚክሲኮ አደባባይ መብራት ሃይል ጀርባ አሁን በላይ ገራዥ ያለበት አካባቢ ተወለደች፡፡ እድሚዋ ለትምህርት ሲደርስ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ተከታትላለች፤ በመቀጠልም የከፍተኛ ትምህርቷን በገጠማት የአይን ህመም ምክንያት ብታቋርጥም በግል ኮሌጅ ውስጥ በትራንስፖርት ማኔጅመንት ለመመረቅ ችላለች፡፡ ትምህርቷን ከዚህ በላይም የመቀጠል ፍላጎት ቢኖራትም በደረሰባት የአይን ህመም ምክንያት ከዚህ በላይ ለመቀጠል አልቻለችም፡:

በሥራው አለምም በመስማራት በርታ ኮንስትራክሽንን ጨምሮ በተለያዩ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ውስጥ በመቀጠርም ሆነ በግሏ ስራዎችን በመውሰድ እራሷንም ሆነ አገሯን ለመጥቀም እውቀቷን ጉልበቷን ሳትሰስት ሰጥታለች፡፡

ወ/ት ሣባ ተሾመ የአንድ ሴት ልጅ እናት ስትሆን ልጇንም እንደአባትም እንደእናትም ሆና በማሳደግ ለልጇ ብቻ የኖረች እናት ነበረች፡፡ ልጇንም በከፍተኛ ጥንካሬና ትጋት እንደጓደኛዋ ጭምር ሆና በማሳደግና በማስተማር ለዩንቨርስቲ ደረጃ አድራሳ የልፋቷን ፍሬ ልታይና ልጇም ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ አርክቴክት ድፓርትመንት /ደብብ ካምፓስ/ ልትመረቅ ሁለት አመት ብቻ ሲቀራት ነበር ከዚህ አለም በሞት የተለየችው፡፡

ወ/ት ሣባ ተሾመ በፖለቲካው መስክ የተቻላትን አስተዋፅኦ ለማድረግ በማሰብ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ኢዴፓ) አባል በመሆን ከተራ አባልነት እስከ ከፍተኛ አመራርነት እንዲሁም በተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች ውስጥ ተሳትፎ በማድረግ እስከ እለተ ሞቷ ድረስ የተቻላትን ተሳትፎ አድርጋለች፡፡ እንዲሁም በ2002 አገር አቀፍ ምርጫ ኢዴፓን በመወከል በአዲስ አበባ ከተማ ወረዳ 21 ውስጥ ለፓርላማ አባልነት በእጩነት ቀርባ በተወዳዳረችበት ወረዳ የፓርቲዋን ስም ከፍ አድርጎ ለማስጠራትና ለማሸነፍ ጊዜዋን ጉልበቷን ብሎም ገንዘቧን ጭምር በመስጠት የፓርቲዋንና የፓርቲያችንን አስተሳሰብ በመራጩ ህብረተሰብ ውስጥ ለማስረፅ ቀንም ሆነ ምሽት ሳይገድባት ቤት ለቤት ጭምር በመዘዋወር እልህ አስጨራሽ ትግል አድርጋለች፡፡ በዚህም የተነሳ በምርጫ ክልሏ ላይ ከኢህአዴግ ቀጥሎ አብረዋት የተወዳደሩትን ከፍተኛ የተቃዋሚ አመራሮች ጭምር በመብለጥ በሁለተኝነት አጠንቃለች፡፡ ወ/ት ሣባ ኢዴፓ ለሚያራምደው አስተሳሰብ ከነበራት ጥልቅ ፍቅር የተነሳ በአገኘችው አጋጣሚ ሁሉ የፓርቲዋን አስተሳሰብና አቋሞች ለህብረተሰቡ ለማድረስ በድፍረት የምታደርገው ተጋድሎ ለብዙዎቻችን አርያ የሚሆን ነበር፡፡

በማህበራዊ ህይወቷም ቅን ከሰው ጋር ተግባቢ ያላትን ተካፍሉ ለመብላት የምትጓጓ ስትሆን በመንፈሳዊ ህይወቷም ለምታምነው እምነት ጥልቅ መረዳት ያላትና በህሊና ዳኝነት የምታምን ፍሪሀ እግዚአብሔር የተላበሰች ነበረች ፡፡

ወ/ት ሣባ የካቲት 01 ቀን 2006 ዓ.ም ቅዳሜ ከምሽቱ 1 ሰዓት አካባቢ ወደ አዳማ /ናዝሪት/ ዘመዶቿን ለመጠየቅ እየሄደች ባለችበት ሰዓት የተሳፈረችበት መኪና ሞጆ አካባቢ ሲደርስ በደረሰበት ድንገተኛ አደጋ ነበር እሷን ጨምሮ የ9 ሰዎች ህይወት ለህልፈት የተዳረገው፡፡ በዚህ ሁኔታ ነበር የዚች ደግ ሩህርህና አዛኝ የትግል አጋራችን ህይወት የተቀጠፈው፡፡ ይህን ቅስም ሰባሪ መርዶ የኢዴፓ አባላት ሰኞ የካቲት 03 ቀን 2006 ዓ.ም ጠዋት በተሰበረ ልብ ሆነን ነበር ያደመጥነው በዛው ቀን በለቡ ገብርኤል ቤ/ክርስትያን ይችን የምንወዳትንና የምትወደንን የትግል አጋራችንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሸኘናት፡፡

ለቤተሰቦቿ ለወዳጅ ዘመዶቿና ለትግል አጋሮቿ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢ.ዴ.ፓ) መጽናናትን ይመኛል፡፡

የሣባን ጠንካራ እምነቶችና የኢዴፓን አስተሳሰቦች በማስቀጠል የእህታችንን ህያውነት እናረጋግጣለን

ከኢዴፓ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

ሣቢ ሁሌም በልባችን ትኖሪያለሽ! 

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter