ጠመንጃን በጠመንጃ የሚል የትግል ስልት ዘመኑን አይመጥንም
ኢህአዴግ በትረ-ስልጣኑን ከያዘ እንሆ 23ኛ ዓመቱን ሊድፍን በጣት የሚቆጠሩ ቀናቶች ቀርተውታል፡፡በዚህ የስልጣን ዘመኑ እሱን ለመታገል የተደራጀን የፖለቲካ ኃይሎች በነዚህ ሁሉ ዓመታት በትግል ስልት ዙሪያ ሦሰት ዓይነት አቋም እያራመድን እንገኛለን፡፡
ኢህአዴግን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አልገነባም፤ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችን አላከበረም፤ሕገ-መንግስቱ ውስጥ ለህዝብ የማይጠቅሙ አንቀጾችን በምርጫ አሸንፈን ለሕዝብ እንዲጠቅሙ ለምናደርገው ትግል እንቅፋት ፈጣሪ ነው፤በሚል ወደ ሰላማዊ የትግል ጎራ በመቀላቀል ሃሳብን በነፃነት የመግለፅና የመሰብሰብ መብት በመጠቀም ከምርጫ ቦርድ ህጋዊ ሰርተፍኬት ወስደናል፡፡አሁን የምርጫ ቦርድ ባወጣው መረጃ ከ70 በላይ ፓርቲዎች በሰላማዊ ትግሉ ጎራ ተሳታፊ ሆነናል፡፡