እውነቱን ተናግሮ ከመሸበት ማደር

Adane Tadesseከአዳነ ታደሰ
የፓርቲው የፋይናንስ ሃላፊ

በሀገራችን የፖለቲካ ትግል ታሪክ ውስጥ በተለይም ከኢህአዴግ ስልጣን መያዝ ማግስት ጀምሮ የተቋቋሙ የተቀዋሚ ፓርቲዎች እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ ጥቂቶቹ ፓርቲዎች ፕሮግራም ደንብ እና አማራጭ ፖሊሲ ቀርጸው ወደ ትግሉ ሜዳ ገብተው ለመታገል ሲያስቡ ደጋፊ ህዝብ አገኛለሁ ብለውና ታሳቢም አድርገው እንደሆነም እሙን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ አብዛኞቹ የተቃዋሚ ፓርቲዎች  የራሳቸው አፈጣጠርና ያሉበት ነባራዊ ሁኔታ የራሱ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ያሉበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁንም ድረስ ከፍተኛ ተግዳሮት ሆኖባቸው ያለው ህዝቡ ተገቢውን ድጋፍ ማበርከት አለመቻሉ ነው፡፡ ድጋፍም ይሰጣል እንኳን ቢባል ድጋፉን የሚገልጽብት መንገድ ለመድብለ ፓርቲ ስርአት ግንባታ፤ለመቻቻልና ለመደማመጥ ፖለቲካ ማበብ የሚያስችል አይደለም፡፡ ይሄንን ለታዘበ ታድያ በዚህ ሀገር በአጭር ግዜ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ተገንብቶ የማየት ህልሙ ቅዥት መሆኑን ለመረዳት ሰከንድ አይፈጅበትም፡፡ ምክንያቱም ይሄ በህዝቡ ውስጥ የሚታየው አስተሳሰብ ለመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርአት ማበብ የሚበጅ ባለመሆኑ ነው፡፡ ፓርቲዎች ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ያላቸው አባላትንና ምክንያታዊ በሆነ መስፍርት የሚቃወምና የሚደግፍ ህዝብ ባለመፍጠራቸው እና ከጎናቸው ባለማሰለፋቸው ትግላቸውን አስቸጋሪ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ተቃዋሚውም በ23 አመት ውስጥ ወደ ለውጥ ከመቅረብ ይልቅ በየግዜው ትግሉ ከዜሮ የሚጀመርና  ሰላማዊ ትግሉም በፍጥነት ለውጥ የማይታይበት ሆኗል፡፡

በሀገራችን ብዙ ለዴሞክራስያዊ ስርአት መጎለበት የሚያግዙ፤ለመግባባትና ለመቻቻል አርሾ የሚሆኑ፤ለፍትህ ስርአት መጠናከር መነሻነት የሚረዱ ብዙ አሴቶች እንዳሉን የሚካድ አይደለም፡፡ ለምሳሌ እድር፤እቁብ፤ማህበር፤እና የገዳ ስርአታችን ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ህዝቡም አነዚህን ማህበራዊ ተቋማት ገንቢ ሚናቸውን በአግባቡ ማጎልበትና ማሳደግ ከቻለና ፖለቲካው ውስጥም እዛ ላይ የሚያሳየውን ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት መድገም የሚችል ከሆነ የተወሰነውን የቤት ስራችንን እንደሰራን ጸሀፊው ይረዳል፡፡ ግን እንዳለመታደል ሆኖ ይሄንን ገንቢ ማህበራዊ መሰረት በአግባቡ መጠቀም አልቻልንም፡፡ እንደውም በተቃራኒው አየሄድን ነው፡፡ ይሄ የሆነው ከምንም ተነስቶ ሳይሆን ስር ሰድዶ የነበረው የግራ ፖለቲካ አስተሳሰብ አሁንም ስጋና ደም ለብሶ በአብዛኛው ህዝብ ውስጥ መታየቱና የዚህ ጽንፈኛ ፖለቲካ አራማጅ የነበሩ ግለሰቦች በገዥውም ሆነ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ አሁንም በአስተሳሰባቸው ላይ ለውጥ ሳያሳዩ ፖለቲካውን እየመሩ በመሆኑ ነው፡፡ ለዚህም ነው ለዴሞክራስያዊ ባህል ግንባታ የሚጠቅሙ የመቻቻል፣ የመከባበር፣የመደማመጥ፣እውቅና የመሰጣጣት፣ያለመፈራረጅ፣የሌላውን ሃሳብ የማክበር፣የመሳሰሉት ዴሞክራስያዊ አስተሳሰቦች ቦታ እንዲያጡ ሆነው ያሉት፡፡በዚህ የተነሳ አብዛኛው ህዝብ የ60ዎቹ ፖለቲከኞች አስተሳሰብ ሰለባ ሆኗል ለማለት ያስደፍራል፡፡   ሌላው ነገር ደግሞ የበቀልንበት ማህበራዊ መሰረታችን ላለብን መሰረታዊ ችግር የራሱን አስተዋጽዎ አድርጓል፡፡ እስከአሁን በኢትዮጵያ ያለው ማህበራዊ ትስስራችን በአብዛኛው በአባትና በእናት፣በአባትና በልጅ፣በታላቅና በታናሽ ወዘተ…..ስንተገብረው የኖርነው ግንኙነት አምባገነንን እንጂ ዴሞክራትን የሚፈጥር ላለመሆኑ ሁላችንም የራሳችንን እድገትና የመጣንበትን ማህበራዊ መሰረት መፈተሸ በቂ ነው እላለሁ፡፡ ዛሬ ላይ ትግሉን እየመራን ያለን የፖለቲካ ሃይሎችም በግልጽና በድፍረት ሕዝቡ ጋር ያለውን ችግር ገምግመን የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥ አለብን፡፡ በግልጽ በችግሮቹ ዙሪያ መወያየት ካልቻልን ግን ትግላችን የሚሆነው ውሃ ቢወቅጡት እንቦጭ አይነት ነው፡፡ ይሄንን ስር የሰደደ የህዝብ ችግር ሸሽተንም ደግሞ የትም አንደርስም፡፡ ህዝቡ የለውጥ ሃይል እንዲሆንና ትግሉን በአግባቡ እንዲደግፍ ዛሬ በድፍረት መነጋገር ካልቻልን ከዚህ በዃላ ሌላ 23 አመትም ቢመጣ ለውጥ ይመጣል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ በሆነ አጋጣሚ ለውጥ ቢመጣ እንኳ ለውጡ የስርአት ሳይሆን የመንግስት ነው የሚሆነው፡፡ ይሄ ደግሞ ለውጥ ሳይሆን አንዱን አምባገነን አንስቶ ሌላ የመተካት ፋይዳ ብቻ ነው የሚኖረው፡፡ ስለዚህ የህዝቡ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ምን መሆን አለበት በሚለው ላይ ፓርቲዎች መሰረተ ሰፊ ስራ መስራት እንዳለባቸው ይሰማኛል፡፡ ዞሮ ዞሮ የዛሬው ጹሁፌ ዋነኛ አላማም ያለፈውን የህዝቡን የትግል ተሳትፎ ገምግሞ ለወደፊቱ ትግላችን የህዝቡ ሚና ምን መሆን ይገባዋል በሚለው ላይ ያተኩራል፡፡ በነገራችን ላይ ህዝብ እያልኩ የገለጽኩትና ወደፊትም የምገልጸው በፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ የሚያደርገውን የህብረተሰብ ክፍል  መሆኑ ይታወቅልኝ፡፡ ለመሆኑ ለዚህ ለፖለቲካው ቅርብ የሆነው ህዝብ ዋነኛ ችግሮችና ድክመቶች ምንድን ናቸው?

አንደኛው የህዝቡ ችግር ይሄ ፓርቲ ወይም ያኛው በእከሌ የሚመራው ፓርቲ ጥሩ  ነው ብሎ ከአፍ ባለፈ በተግባር ድጋፍ ያለማድረግ፤ተደራጅቶም ያለመታገል ነው፡፡ ነገሩን ገራሚ የሚደርገው እነዚህ ወገኖች ተገቢውን ድጋፍ ብቻ አለማድረጋቸው አይደለም ችግሩ ተደራጅቶ የሚታገለውንም አካል ተገቢ ያልሆኑ ትችቶችን በመሰንዘር በመንቀፍ እና የማይገባን ስም በመስጠት ስም በማጥፋት ጊዜያቸውን ሲያጠፋ መስተዋላቸው ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ለትግሉ መዳከም የፓርቲ አመራሮችንና አባላቱን ብቸኛ ተጠያቂ በማድረግ ከደሙ ነጹህ ነን ለማለት ሲሞክሩ ይታያል፡፡ የሚገርመው ነገር ከኛ የሚጠበቀውን ማበርከት ሳንችልና ተሳትፎ ማድረግን እየሸሸን በአንጻሩ ደግሞ የሚታገሉትን ለመተቸትና ለመውቀስ መሞከራችን ነው፡፡ ይሄ የህብረተሰብ ክፍል የማንችስተርን እና የአርሴናልን ኳስ ለማየት የሚሰጠውን ግዜ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ሰጥቶ በሀገሩ ጉዳይ ላይ ቢመክር ኖሮ አሁን ያለው የሀገራችን ፖለቲካ ከዚህ በተሻለ ነበር፡፡ በ97 አ.ም በተደረገው ምርጫ ለሊት ወጥተው ተሰልፈው በመምረጣቸውና ሚያዝያ 30 መስቀል አደባባይ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ በመገኘታቸው ብቻ ከፍተኛ መስዋእትነት እንደከፈሉ ቆጥረው ሰላማዊ ትግሉ ከዚህ በኃላ አበቃለት፤የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከእንግዲህ አይረቡም ብሎ ድምዳሜ ላይ መድረስና ፓርቲዎችና ሰላማዊ ትግሉ  ላይ አጓጉል ነቀፋና ትችት ማቅረባቸውን ለሚያስተውል አብዛኛው ህዝብ ለከፍተኛ መስዋእትነት ዝግጁ አለመሆኑን ይመለከታል፡፡ ግን የየትኛውም በዴሞክራሲ ትልቅ ደረጃ የደረሱትን ሀገሮች ታሪክ ብናይ ለውጥ ማምጣት የቻሉት ተደራጅተውና ዋጋ ከፍለው እንደሆነ እንረዳለን፡፡ እጃቸውን አጣጥፈው ተቀምጠው እንዳልሆነም እናውቃለን፡፡ ለሀገራችን ፖለቲካ መቀዛቀዝና መዳከም ወደድንም ጠላንም ከፓርቲዎቹ ባልተናነሰ የዚህ ህዝብ ሚና ቀላል እንዳልነበር እንረዳለን፡፡ የቅርብ ግዜ ትዝታችንም የሚረሳ አይደለም፡፡ በ1997 አ.ም በስንት ትግል የተገኘን የህዝብ ድምጽ ቅንጅት አክብሮ ወደ ፓርላማ እንዳይገባ ተገቢ ያልሆነ ተጽእኖ በማሳደር፤በእወደድ ባይነት ፖለቲካ የተለከፉትን መሪዎች አቅጣጫ ያሳተው ይሄው ህዝብ ነበር፡፡  በዚህም የተነሳ ትግሉ 15 እና 20 አመት ወደ ኃላ ተመልሷል፡፡ ስለዚህ ይሄ ህዝብ ከስሜታዊነት ተላቆ በሃላፊነት ስሜት ተደራጅቶ ትግሉን ማገዝ ካልቻለ ዴሞክራሲያዊ ስርአትን በአጭር ግዜ ለመትከል እንደማንችል መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ሁለተኛው የዚህ ህዝብ ችግር የፖለቲካ አመለካከትንና ብስለትን ከሰዎች የትምህርት ደረጃና ካላቸው ሀብት ጋር አያይዞ የማየት ነው፡፡

ሁለተኛው የዚህ ህዝብ ችግር የፖለቲካ አመለካከትንና ብስለትን ከሰዎች የትምህርት ደረጃና ካላቸው ሀብት ጋር አያይዞ የማየት ነው፡፡
በነዚህ ወገኖቼ አስተያየት ዶ/ር እና ፕሮፌሰር ያልሆነ ሰው ፖለቲካውን በአግባቡ አይመራውም ብለው የማሰብ አባዜ ይታያል፡፡ ግን ይሄ አስተሳሰብ ከመነሻው ስህተት እንደሆነ ለማሳየት ሩቅ መሄድ አያስፈልግም፡፡ አብዛኛውን ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የሚመሩት ሁለት ድግሪ እና ከዛ በላይ ያላቸው ምሁራን ናቸው፡፡ አንዳንዶቹም ዴሞክራሲያዊ ባህል በዳበረባቸው ሀገሮች ተምረው የመጡ ናቸው፡፡ ቢሆንም ግን ውስጣዊ ዴሞክራሲያዊ ባህል የዳበረበት ጠንካራ ፓርቲ ፈጥረው ለማየት አልቻልንም፡፡ እንደውም አብዛኞቹ በተቃዋሚ ውስጥ ሆነው እንኳ ከስልጣን መውረድና መውጣትን ማረጋገጥ አቅቶአቸው ሰልጣንን ርስት አድርገው መያዛቸውን ለሚያይ መማር ብቻውን ዋጋ እንደሌለው ይረዳል፡፡ በመሆኑም ወደፊትም የዳበረ የፖለቲካ ባህል በሀገራችን ሊፈጠር የሚችለው የተማሩ ሃብታም ግለሰቦች የመሪነቱን ሚና ስለተጫወቱ ሳይሆን ምን ያህል ለዴሞክራስያዊ አስተሳሰቦች ተገዥ ናቸው በሚለው ነው መለካት ያለባቸው፡፡

እዚህ ላይ የተማሩ ግለሰቦች ፓርቲዎችን አይምሩ እያልኩ ሳይሆን ለሰለጠነና ዘመኑን ለሚመጥን ፖለቲካ የሚሆኑ መሆን አለባቸው ማለቴ እንደሆነ ይሰመርበት፡፡ ስለዚህ ህዝቡ ድጋፉንና ትብብሩን ማሳየት ያለበት ፓርቲው የያዘው አላማና ፕሮግራም ምንድን ነው፤ውስጣዊ ዴሞክራስያዊ ባህሉ ምን ይመስላል፤አላማውን ለማሳካት በሚከተለው የትግል ስልት ላይ ምን ያህል የማያወላውል አቋም አለው፤ከሚል መሆን አለበት፡፡ ሶስተኛው የኛ ህዝብ ችግር ሆኖ የሚታየው አብዛኛው የፓርቲ አባል የሚሆነው ከግል ጥቅሙ ጋር ጉዳዮችን አገናኝቶ መሆኑ ነው፡፡ ከሀገር ተሰዶ ጥገኝነት ለማግኘት በማሰብ ወደ ውጭ ለመሄድ ሲፈልግ ነው ወደ ፓርቲዎች ቢሮ ጎራ ሲል የሚታየው፡፡ ሌላው ደግሞ ፖለቲካው ሞቅ ሞቅ ሲል በስሜታዊነት ይመጣና የሚፈልገው ሆያ ሆዬ ሲያልቅ በዛው ይጠፋል፡፡ ስለዚህ ትግሉን ከግል ጥቅምና ከግዜያዊ ስሜት በራቀ መልኩ መደገፍ በሀገራችን ገና ብዙ የሚቀረው ነው፡፡ ከዚህ አይነት ስሜትና አስተሳሰብ ወጥተን ለነገ፤ለከነገወድያ እና ለትውልድ የሚተርፍ የበቃ ፓርቲ መፍጠር የምንችለው  ነገን የሚያይ ለሀገሩ ተቆርቋሪ አዲሲቷን ኢትዮጵያን ለማየት ናፋቂ ትግሉን በቆራጥነትና በታማኝነት የሚደግፍ ህዝብ ሲኖር ነው ሰላማዊ ትግሉ ሳይኮላሽ ዳር የሚደርሰው፡፡ አራተኛው ድክመታችን ስለ ለውጥ ያለን አስተሳሰብ ነው፡፡ በዚህ ፖለቲካ ውስጥ ተሳታፊ የሆነው አብዛኛው ህዝብ የፈለገው ብቻ ይምጣ ግን ኢህአዴግ ስልጣን ይልቀቅ የሚል ነው፡፡ በማንኛውም መንገድ ይሁን ለውጥ እንዲመጣ  ይፈልጋል፡፡ ግን ይሄ ትልቅና መሰረታዊም ስህተት ነው፡፡ ምንም ይምጣ ብሎ ለለውጥ መነሳት ራሱ ችግር አለው፡፡ ምክንያቱም ዋጋ ከፍሎ አምባገነንን በአምባገነን መተካት ነው ውጤቱ ሊሆን የሚችለው፡፡ ይሄን ስል ከምንም ተነስቼ አይደለም የሀገራችንን የመንግስታት ታሪክ ብናይ የሚያመለክተን አሁን እንደሚባለው የፈለገው ይምጣ በሚል ስሌት የተካሄዱ ለውጦች በመሆናቸው ነው፡፡ እስከአሁንም በሀገራችን የተከሰቱ የለውጥ አጋጣሚዎችን በአግባቡ መጠቀም ሳንችልም የቀረነው በዚሁ ስለ ለውጥ ባለን አረዳድ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይልቅስ በሰላማዊ ትግል ያሉብንን የተሳትፎ ድክመቶች እንደ ህዝብ በማረምና በማስተካከል ለውጡን የመንግስት ሳይሆን የስርአት ለውጥ እንዲሆን መታገል አለብን፡፡ ይሄንንም በማድረግ የምንፈልገውንና በህዝብ ድምጽ አሸናፊ የሚሆን ፓርቲ በመምረጥ ውጤቱ ወደ ኃላ የማይቀለበስ እና ያለፉት ትውልዶች ያልሰሩትን ታሪካዊ ድል ማስመዝገብ ይቻላል፡፡ ለዚህ ታሪካዊ ድልም  ከወዲሁ ወገብን ጠበቅ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

አምስተኛው እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አይነት አስተሳሰብ የብዙዎቻችን ድክመት መገለጫ ነው፡፡ የሰላማዊ ትግል በባህሪው ረዥም ግዜ ሊፈጅ የሚችል ነው፡፡ ምክንያቱም የዲሞክራሲ ሂደቱን በማጎልበትና በሂደቱ የሚገኙ ውጤቶችን እያሳደጉና እያጎለበቱ በመሄድ የሚገኝ ውጤት ስለሆነ ነው፡፡ እኔ ከሞትኩ……የሚለውን አስተሳሰብ የሚያራምዱ ሰዎች በለውጡ ራሳቸውንና ራሳቸውን ብቻ ለመጥቀም ነው ፍላጎታቸው የሚሆነው፡፡ በዚህም የተነሳ እነዚህ ግለሰቦች ብዙውን ግዜ ግብታዊ ለውጥንና አጋጣሚዎችን እንድንጠብቅና ምክንያታዊ አስተሳሰብም እንዳይኖረን ሲያደርጉ ይታያል፡፡ በተለይም ፖለቲካውን የሚመሩት ግለሰቦች በዚህ አይነት አስተሳሰብ የተጠለፉ ስለሆነና ለስልጣን ካላቸው ጥም የተነሳ ነው በማንኛውም መልኩ የተገኘ ለውጥ ናፋቂ ሲሆኑ የሚስተዋለው፡፡ አሁንም ምስክር የሚሆነው ያው ምርጫ 97 ነው በእንደኛ አይነቷ ገና ብዙ በሚቀራት ሀገራችን ለውጥ የመንግስት ይሁን ብሎ መንቀሳቀስ ያለንን በጎ ነገር የሚያሳጣና ሀገራችንንም ወደ አደጋ ሊከት እንደሚችል ማሰብ ጠቃሚ ነው፡፡ ነገሩን የበለጠ ከባድ የሚያደርገው በአሁኑ ሰአት ኢህአዴግ የሀገሪቱን ህልውና ከራሱ ህልውና ጋር አስተሳስሮ በማየት እኔ ከሌለሁ ሀገር ይፈርሳል በሚልበት ወቅት ብሄረሰባዊ፣ አካባቢያዊ ስሜትና ጠባብነት በጎለበተበት ወቅት የሚመጣ ግብታዊ ለውጥ አደጋው የከፋ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብዙ ሃብትና ንብረትም ያወድማል፡፡

ስለዚህ ስለ ለውጥ ስናስብ በመንግስት ለውጥና በስርአት ለውጥ መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት ከግምት አስገብተን ቢሆን ከዜሮ ድምር ፖለቲካ ተላቀቅን ማለት ነው፡፡ ስድስተኛው ልንፈትሸው የሚገባን ድክመታችን ሀገር ወዳድንና ጀግናን የምናይበት መነጽር ነው፡፡ በዚህ ላይ ህብረተሰቡ ስለ ሀገር ወዳድና ስለ ጀግና ሚሰጠው ትርጉም ያስገርመኛል፡፡
በዚህም በኩል የግራ ፖለቲካ አስተሳሰብ ምን ያህል ተጽእኖ እንዳለው የሚታይበት ነው፡፡ አሁን በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ያለን ቢሆንም በ60ዎቹ ግዜ እንደነበረው ነው ትርጓሜያችን፡፡ በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ የሀገር ወዳድነትና የጀግንነት መለኪያው ኢህአዴግን በጭፍን ጥላቻ በአደባባይ ማውገዝ፣የኢህአዴግን አባል መጠየፍ፣ህዝብንና ፓርቲን ለያይቶ የማይመለከት፣የኢትዮጵያ ሬድዮ አለማዳመጥ፣ኢቲቪን አለመመልከት፣ ስለ ብሔሮች መብት መስማት የማይፈልጉ፣ኢህአዴግን እንደ ወራሪ እንጂ እንደ መንግስት እውቅና የማይሰጡ ወዘተ……እንደ ሀገር ወዳድ ሲቆጠሩ ምንም አይነት አቋም ያራምድ በፖለቲካ ጉዳይ ከሀገር የተሰደደና፤ ምንም አይነት ፖለቲካዊ አቋም አራምዶ ቃሊቲ የገባ ግለሰብ የሀገሪቱ ማናዴላና ጀግና ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ሌሎቹን ደግሞ ስለ መቻቻል፣ስለ ምክንያታዊነት፣ስለ ሰላማዊ ትግሉ መጠናከር፣ስለ ምርጫ ተሳትፎ፣የአባይን ግድብ ጠቃሚነት መመስከር፣የከተማ ውስጥ ኮንስትራከሽን እድገቱን ማውራት እንደ ከሀዲ፣ ፈሪና፤ አድርባይ፣ የኢህአዴግ አጃቢና አሻንጉሊት ተደርጎ ያስቆጥራል፡፡ ስለዚህ በሀገራችን በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ እንደ ጀግና የሚቆጠሩት በኔ አመለካከት በተሳሳተ አቅጣጫ የሚሄዱትንና የእወደድ ባይነት ፖለቲካ አራማጅ ወገኖችን ነው፡፡ በመሆኑም የጀግንነትና የሀገር ወዳድነት ትርጉም ከዚህ የማይረባ አተረጓጎም ወጥቶ ሀገርንና ህዝብን ከሚጠቅም ተግባር ጋር ተያይዞ መራመድ ካልቻለ ሀገራችን እውነተኛ ጀግና ወደፊትም ይኖራታል ብዬ አላስብም፡፡

እዚህ ላይ በተለያየ ግዜ ሀገራቸውን ከወራሪ ሃይል የጠበቁትን ኢትዮጵያውያን ጀግኖች እንደማይመለከት ይሰመርልኝ እኔ እያነሳው ያለሁት ስለ ሞራላዊ ጀግንነት ነው፡፡
ህዝቡ ለመቻቻል ፖለቲካ፤ለመደማመጥ ባህል መጎልበት፤ለዴሞክራስያዊ ባህል እውን መሆን፤ለመድብለ ስርአት መጠናከር የሚታገሉትን ትቶ በትጥቅ ትግልና በአመጽ መንግስትን ከስልጣን እናስወግዳለን የሚሉ ግለሰቦችን እንደ ጀግና እየቆጠረ ድጋፍ የሚያደርግ ከሆነ ሀገሩ እንድትፈርስና ኢትዮጵያ እንድትጎዳ እየተባበረ በመሆኑ ለሰላማዊ ትግሉ የሚያደርገውን ድጋፍ ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል አለበት እላለው፡፡ በሰባተኛ ደረጃ የማነሳው በህዝቡ ውስጥ ስር ሰዶ የሚታየው ችግር የአሉባልታ ሰለባ መሆኑ ነው፡፡ አብዛኛው ህዝብ ጉዳዩን በጥልቀት መርምሮ እውነታውን ከማረጋገጥ ይልቅ ያነበበውንና የሰማውን አሉባልታ አምኖ ሲቀበል ይታያል፡፡ አንዳንድ ግለሰቦችና ጋዜጦች  አላማቸው እና አጀንዳቸው ስም ማጥፋት በመሆኑ ህዝቡም እነዚህ ሰዎች በጻፉትና በኢንተርኔት በለቀቁት ወሬና አሉባልታ  ሲታመስ መዋልና ማደሩ የተለመደ ሆኗል፡፡ የፈጠራ ወሬ ሁሉ እንደ ፖለቲካ ጉዳይ ተቆጥሮ እስከዛሬ ድረስ በ97 ዓ.ም ለተፈጠሩ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ግለሰቦች እንደ ማጣቀሻ የሚቆጥሩት በግዜው ኢትዮጵ፣አስኳልና ሳተናው ጋዜጣ ላይ የተጻፉትን ጽሁፎች መሆኑን ለሚያስተውል ምን ያህል አሉባልታ ስር የሰደደ ችግር እንደሆነ ይረዳል፡፡ በተለያየ ግዜ በአይናችን ከምናየው ይልቅ በጆሮአችን የሰማነውን አሉባልታ ለማመን ቅርብ ስንሆን ይታያል፡፡በነዚህ ግለሰቦች  በሚወጡ ጋዜጦች  በጀግንነቱ የተወደሰና  ከሱ በላይ ሀገር ወዳድ ላሳር ሲባል ህዝቡም አብሮ ሆ ይልና በዛው ሰሞን ይሄው ግለሰብ ከሃዲ ቅጥረኛና ባንዳ ሲባል ህዘቡም አብሮ ሲያወግዘው እናያለን፡፡ ይሄ የሚያሳየን ምን ያህል ምክንያታዊ እንዳልሆንና ጉዳዮችን ለመመርመር ትግስት እንደሌለንም ነው፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘምን እንዲህ አይነት ሁኔታ ውስጥ መገኘታችንም በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ የሀገራችን ፖለቲካ ከአሉባልታ ጸድቶ በአማራጭ አስተሳሰቦች፣በምክንያታዊነት ላይ ተመስርቶ በሚካሄድ ውይይትና የሃሳብ ልውውጥ መተካት መቻል አለበት፡፡ አለበለዚያ የምንፈልገውን በሌሎች ሀገሮች ላይ የምናየውንና የሚያስቀናንን ዴሞክራስያዊ ባህል መትከል አንችልም፡፡ ህዝቡንም እንደከዚህ ቀደሙ “ የነቃና የበቃ ህዝብ ”እያሉ ችግሮቹንና ድክመቶቹን እየሸፋፈኑ መጓዝ ዞሮ ዞሮ የሚጎዳው ሀገርንና ህዝቡንም እራሱ ነው፡፡ ይልቅ የህዝቡን ድክመቶችና ጉድለቶቹን በአግባቡ ገምግሞ የተነሳ የፖለቲካ ፓርቲ ወደ ኃላ የማይቀለበስ ለውጥ ማምጣት ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡ የሰለጠነና ዘመኑን የሚመጥን የለውጥ ሃይል የሚሆን ህዝብ ለመፍጠር ከዛሬ ጀምሮ መነሳት የሁሉም ፖለቲከኞች የቤት ስራ መሆን አለበት፡፡ እውነቱን ተናግሮ ከመሸበት ማደር ይሻላልና፡፡  በሚቀጥለው እትም ፓርቲዎችን በሚገመግመው ፁሁፌ እስክንገናኝ ቸር እንሰንብት፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter