የፖለቲካ ፍቃደኝነት ለላቀ የግብርና ምርታማነት

Abis Getachew Makuriaበአቢስ ጌታቸው

የግብርና ምርታማነትን እድገት ከሚወስኑት ግብዓቶች መካከል መሬት፤ ካፒታል፤ የሰው ሀይል፤ እውቀት እና ቴክኖሎጂ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከነዚህ መሰረታዊ የግብርና ምርትን ከሚወስኑት ነገሮች (determinants) መካከል ሀገራችን ኢትዮጵያ ያላት የካፒታል፤ የእውቀት እና የግብርና ቴክኖሎጂ እጅግ በጣም ኋላ ቀር ሊባል የሚችል ነው፡፡ እነዚህ የግብርና ምርታማነት የሚወስኑት ነገሮች (determinants) ኋላ ቀር መሆን ለግብርናው ዘርፍ ምርታማነት እና እድገት አሉታዊ ተጽእኖዎች ይኖሩታል፡፡ ከላይ ከተዘረዘሩት ወሳኝ ግብዓቶች መካከል የእርሻ መሬት የአገራችን የግብርና ዘርፍ ካለው ብቸኛ ሀብት ውስጥ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ ይህንን ብቸኛ ሀብት በትክክለኛው መንገድ መያዝ ለዘርፉ ያለው ብቸኛ ወቅታዊ አማራጭ ነው፡፡

በአገራችን ያለው የመሬት ፖሊሲ ከርዕዮተ አለማዊ አስተሳሰብ የመነጨ ሆኖ ሳለ አገራዊ መግባባት ሳይደረስበት ሕገ-መንግስታዊ ሆኗል፡፡ በእርግጥ አንድን አገራዊ ጉዳይ በተለይ እንደመሬት አይነትን ብቸኛው ሀብታችንን የተመለከተ አገራዊ ፖሊሲ ሕገ-መንግስታዊ ለማድረግ ብዙ ዉይይት እና ምክክር በተደጋጋሚ ማድረግን የሚጠይቅ ቢሆንም በአንድ ትውልድ ጊዜ ያውም ከእዝ ኢኮኖሚ ተላቆ ስለ ገበያ ኢኮኖሚ እና ስለ አለም ሁኔታ በውል ባልተረዳ ትውልድ በተደረገ “ውይይት” እና “መግባባት” በሚያሳዝን መልኩ መጪዎቹ ትውልዶች እንዲገዙበት ተገደዋል፡፡ በዚህ ጽሁፌ ላይ በአሁኑ ጊዜ ያለውን የመሬት ፖሊሲ በግብርናው ዘርፍ እድገት እና በአጠቃላይ የአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ላይ ያለውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመዘርዘር እሞክራለው፡፡

በአሁኑ የመሬት ፖሊሲ የከተማም የገጠርም መሬት ሙሉ በሙሉ የመንግስት በሆነበት ሁኔታ በአንደኛ ደረጃ የትኛውም አርሶአደር የመሬቱን ለምነት፤ ልስላሴ እና ምርታማነት ለመጠበቅ ገንዘቡን እና ጊዜውን ለማፍሰስ ፍላጎት አያድርበትም፡፡ በተግባር እንደታየውም ሚሊየነር አርሶአደር ተፈጥሯል በሚባልበት በአሁኑ ጊዜ እንኳን አርሶአደሩ ከመንግስት በብድር የሚሰጠውን ማዳበርያ ከመጠቀም ውጭ በራሱ ተነሳሺነት መሬቱን በአግባቡ ለመያዝ ያለው ቁርጠኝነት በእጅጉ ያነሰ ነው፡፡ ለምሳሌ በባህላዊ መንገድ የሚደረጉ የእርሻ መሬት አያያዝ እንደ ሰብልን እየቀያየሩ ማምረት (Shifting cultivation) እና ጦም ማሳደር (fallow) በአርሶአደሩ ዘንድ እንደ ቅንጦት የሚታዩ ሆነዋል፡፡ ለዚህም የመሬት የባለቤትነት ዋስትና ያለመኖር የመሬትን ለምነት እና ምርታማነት እንዳይጠበቅ ምክንያት ሆኗል፡፡ በተጨማሪም መንግስት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሰፋፊ የእርሻ መሬት ለባለሀብቶች ሲሰጥ ገበሬውን ከአካባቢው እያፈናቀለ ነው የሚለው ወሬ ገበሬው “ነግ በኔ ነው” በሚል የእርሻ መሬቱን ለምነትን መጠበቅ የሚለውን ሀሳብ እርግፍ አድርጎ ትቶት ይገኛል፡፡

ሁለተኛ አሁን ያለው የመሬት ፖሊሲ በገጠር የሚገኘውን ወጣት የህብረተሰብ ክፍል እጅግ እየጎዳው ይገኛል፡፡ በዚህ ጊዜ በገጠር የሚኖር ወጣት የህብረተሰብ ክፍል መሬትን ህጋዊ በሆነ ሁኔታ (በመግዛትም ሆነ ከመንግስት የማግኘት) እድሉ በጣም የጠበበ በመሆኑ ያለው አማራጭ ከቤተሰቡ የሚያገኘው ሽርፍራፊ መሬት ብቻ ይሆናል፡፡ይህ ደግሞ የእያንዳንዱ ቤተሰብ መሬት ይዞታ ከትውልድ ትውልድ እንዲቀንስ የሚያደርግ ሲሆን በመጨሻም ሁሉም ተያይዞ እንዲደኸይ የሚያደርግ መሆኑን ያሳያል፡፡ በወቅታዊው የናይትሮጂን ቴክኖሎጂ ምንም እንኳን በትንሽ መሬት ላይ ብዙ ምርት ማግኘት ቢቻልም አርሶአደሩ ባለው የካፒታል እና የቴክኖሎጂ እጥረት ይህንን ማድረግ ይከብደዋል፡፡ እነዚህ እጥረቶች ለመቅረፍ በመንግስት በኩል የተለያዩ ድጋፎች ለአርሶአደሩ ቢደረጉም እስካሁን የሚፈለገውን ያህል ለውጥ በተፈለገው ጊዜ ሊያስገኙ አልቻሉም፡፡

ሌላው የመሬት ሙሉ ባለቤትነት በመንግስት እጅ መሆኑ በሌላ አነጋገር አገሪቷ በዋናነት ያላት ሀብት በብቸኝነት በመንግስት እጅ ሆነ ማለት ነው፡፡ ይህ ሀብት አርሶአደሩ አንደፈለገው መሸጥ እና መለወጥ አለመቻሉ መንግስት በአሁኑ ጊዜ ሊተገብረው ለሚያስበው የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም ትልቅ እንቅፋት ሆኗል፡፡ አርሶአደሩ ለመሬቱ ተገቢውን የገበያ ክፍያ ሳያገኝ ወደሌላ ቦታ ለመሰባሰብ የሚኖረው ፈቃደኝነት እጅጉን ያነሰ ነው፡፡ ይህ ፈቃደኝነት ቢኖር እንኳን በመንደር በሚሰባሰብበት ቦታ ራሱን ለማደራጀት በቂ ገንዘብ ስለማይኖረው ወደባሰ ድህነት እንጂ መንደር በማሰባሰብ ፕሮግራሙ ራሱን ተጠቃሚ የሚያደርግበት የተመቻቸ መደላደል አይፈጠርለትም፡፡

መሬት ሙሉ በሙሉ በመንግስት እጅ መያዙ የሚያደርሰው አራተኛ ተጽእኖ የበቃ፤ በራሱ የሚተማመን እና በነፃነት ለራሱ የሚወስን ትውልድ ከመፍጠር አንፃር የሚፈጥረው ፈተና ነው፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው የሰው ሀይል አንዱ የግብርና እንዲሁም የአገር ኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ የሚያደርግ ግብዓት (determinant) ነው፡፡ የሰው ሀይል በአገር እድገት ላይ አስተዋጽኦ አንዲያደርግ እንዲሁም ምርታማ እንዲሆን በመጀመርያ በራሱ የሚተማመን እና ለራሱ የሚወስን ወጣት ሀይል መሆን ይጠበቅበታል፡፡ አገራችን በሰው ሀብት የታደለች አገር ብትሆንም በራሱ የሚተማመን እንዳይሆን ግን በእጁ የያዘው ሀብት ባለመኖሩ ከዛሬ ነገ የያዘውን መሬት እንዳይነጠቅ የሚፈራ እና የሚለማመጥ ዛሬ በገጠሩ ወጣት ዘንድ ማየት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ በገጠር አካባቢ የሚኖር ወጣት የማያምንበትን፤ የማይጠቅመውን እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ ለሚቃወመው ሀሳብ እንኳን ሳይወድ በግድ ሀብቱን እና ጥሪቱን እንዳይቀማ ሲል ሲደግፈው እና ሲመርጠው ይታያል፡፡ በርካታ የለውጥ አቅም ባለበት በገጠሪቷ ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት ትውልድ መፈጠሩ ጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ ቢያስገኝም ለዘላቂ አገር ግንባታው ሂደት ግን አሉታዊ አስተዋጽኦ እንጂ ምንም አይነት በጎ አስተዋጽኦ አይኖረውም፡፡

በሌላ በኩል መሬት በግል ባለቤትነት አለመያዙ መሬትን በአግባቡ በማይጠቀሙበት ሰዎች ስር እንዲሆን ሲያደርግ በተቃራኒው ደግሞ መሬትን በሚገባ ሊጠቀሙበት የሚችሉ ካፒታል፤ ቴክኖሎጂ እና እውቀት ያላቸው ሰዎች ተጨማሪ መሬት እንዳያገኙ እንቅፋት ይሆንባቸዋል፡፡ በእርግጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሬትን ከአርሶአደሩ በኪራይ አግኝተው ምርት ማምረት የጀመሩ ሰዎች ቢኖሩም እነዚህ ሰዎች የኪራይ መሬቱ ለምነት እና ደህንነት እንዲጠብቁ የሚገፋፋቸው አንዳችም ምክንያት የለም፡፡ ምክንያቱም የመሬትን ለምነት ለመጠበቅ ከፍተኛ ጊዜና ገንዘብ ለማውጣት ምንም ዋስትና የላቸውምና ነው፡፡ መሬቱን መግዛት የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሮ ቢሆን ኖሮ ለገዥውም ለሻጩም ታላቅ ጥቅምን ባስገኘ ነበር፡፡ ነገር ግን በመንግስት በኩል ገበሬው ጥቅሙን የማያውቅ እና ጥቅሙን አሳልፎ የሚሰጥ ነው ተብሎ ስለሚገመት አርሶአደሩ መሬቱን መሸጥ ሳይችል እንዲሁ እውቀቱና ቴክኖሎጂው ካለው ገበሬ ባነሰ ሁኔታ እያመረተ መቀጠሉ ለአገሪቱ የግብርና እድገት አንዱ ማነቆ ሆኖ ይቀጥላል፡፡

በአጠቃላይ የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ ለግብርናው ዘርፍ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ስለሆነ አሁን በስራ ላይ ያለው የመሬት ፖሊሲ በአስቸኳይ ሊከለስ ይገባዋል፡፡ ይህንን ለማድረግ የግብርና ዘርፉን ችግር እና በአገሪቱ ያለው የመሬት ፖሊሲው የኢኮኖሚ እድገት ላይ ያለውን ማነቆ መረዳት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ፈቃደኝነት እና ቁርጠኝነትንም (political will)  ይጠይቃል፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ የፖለቲካውን መዘውር ለመያዝ ቁልፍ የኢኮኖሚ ሀብትን መያዙ ለአገራችን ሁሉን አቀፍ እድገት የራሱን አሉታዊ ሚና ይጫወታል፡፡ በመሆኑም ከገዥው ፓርቲ የፖለቲካ ፍቃደኝነትን በመሬት ጉዳይ ላይ ይጠይቃል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ እኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለአገር አንድነት እና ብሔራዊ ጥቅም እንደምንሰራ እርስ በእርሳችን እና ከገዥው ፓርቲ ጋር መተማመን ይኖርብናል፡፡ ገዥውን ፓርቲ ከጊዜያዊ ጥቅም ብሔራዊ ጥቅምን አስቀድም እያልን እኛው ራሳችን ባገኘነው ቀዳዳ የፓርቲያችንን እና የድርጅታችንን ጊዜያዊ ጥቅም የምናሳድድ ከሆነ ለጥያቄያችን ከገዥው ፓርቲ አወንታዊ ምላሽ መጠበቅ አይኖርብንም፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ቁርጠኝነቱን ከገዥው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ከሁላችንም በኩል መሆን ይጠበቅበታል፡፡

የመሬት ጉዳይ ሕገ-መንግስታዊ ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን የፖለቲካ ፍቃደኝነት ያስፈልጋል ሲባል ሕገ-መንግስቱን ራሱ
ሕገ””-መንግስቱ በሚፈቅደው መልኩ እንዲሻሻል የፖለቲካ ፍቃደኝነትም ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ከገዥው ፓርቲ በኩል ሕገ-መንግስቱን እንደማይነካ ቃል አድርጎ መቁጠር በተቃራኒው ደግሞ ሌሎች ተቃዋሚዎች እንደሚያራምዱት አይነት ሕገ-መንግስቱን የተጻፈበትን ቀለም ያህል ዋጋ እንደሌለው አድርጎ መቁጠር እና እውቅና አለመስጠት መጨረሻው አገርን ታላቅ ዋጋ የሚያስከፍል አካሄድ ነው፡፡ ፖለቲካ እንደ አገሩ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተጨባጭ ሁኔታ ተለዋዋጭ በመሆኑ በአንድ ትውልድ ጊዜ በተረቀቀ ሕገ-መንግስት መጪዎቹ ትውልዶች ይተዳደሩበት ማለት የማይሰራ አስተሳሰብ ነው፡፡ ስለሆነም በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ በነበረ ትውልድ የተቀረፀ ሕገ-መንግስት የ21ኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ ላይ ያለ ትውልድ ሊያሻሽለው ግድ ይሆናል፡፡ በዋናነት የመሬት ጉዳይ በአገራችን የኢኮኖሚ እድገት ጉዞ ላይ ባጠላው ጥላ ምክንያት ሕገ-መንግስቱን መከለስ ቢያስፈልግም እንደጊዜው ሁኔታ ሌሎችም አንቀጾችም የሚሻሻሉበት ሁኔታ በዘላቂነት ሊፈጠር ይገባል፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter