ኢህአዴግ ከዜሮ ድምር ፖለቲካ መውጣት አለበት!

Adane Tadesseከአዳነ ታደሰ
የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ

ፓርቲዎች ተቋቁመው ወደ ትግል ሲገቡ አላማቸውንና ፕሮግራማቸውን ለማስተዋወቅ ከሚጠቀሙበት ስልት አንደኛው አዳራሽ ውስጥ በሚያዘጋጁት ህዝባዊ ስብሰባ ደጋፊያቸውን በማግኘት ነው፡፡ ይህን የአዳራሽ ህዝባዊ ስብሰባ ለማዘጋጀት ደግሞ ገንዘብ፣የሰው ሃይል፣ግዜ ወሳኝ ድርሻ አላቸው፡፡ በተለይ ተቃዋሚዎች ሁል ግዜ ከፍተኛ ችግር ከሚሆንባቸው ነገሮች የፋይናንስ ጉዳይ አንደኛው ነው፡፡ ይሄንን ችግር እንደምንም ተወጥተው ቢገኙ አንኳ ሌላ ፈተና ላይ መጣዳቸው አይቀርም ይሄም የስብሰባ አውቅና ፈቃድ ማውጣት ነው፡፡ የሚገርመው የስብሰባ እውቅና ፈቃድ ይሄን ያህል ውስብስብ ቢሮክራሲ ኖሮት አይደለም፡፡ነገር ግን በሃላፊነት የተቀመጠው ግለሰብ አቶ ማርቆስ ሆነ ብሎ ለፍቃድ የሚመጡትን የፓርቲ ተወካዮች በማጉላላት የታወቀ ነው፡፡ በጣም ፈጠነ ከተባለ ከሳምንት በፊት ከሱ ቢሮ መላቀቅ አይቻልም፡፡ የበለጠ የሚያሳዝነው ደግሞ ሰውየው ጋር ሳምንት አይደለም ለአንድ ደቂቃ ቢሮው ውስጥ መቀመጥ መክበዱ ነው፡፡ አቀባበሉ ጥሩ ያልሆነ፣ንግግሩ የማይጥምና ትእቢቱ የቢሮ ሃላፊ ሳይሆን ውጥረት ውስጥ ያለ የፌደራል ፖሊስ ነው የሚመስለው፡፡

በዚህ 14 አመት ውስጥ በሄድኩ ቁጥር የማየው የሰውየው ባህሪ ይሄው በመሆኑ ሰው እንዴት ትንሽ ለውጥ አያሳይም እያልኩ እገረማለሁ፡፡ ይሄ ቢሮ ከገዥው ፓርቲ ጋር ተቃዋሚዎች የሚገናኙበት የመጀመርያው መስመር እንደሆነ ኢህአዴግ እያወቀ ምን የፖለቲካ ትርፍ አገኝበታለው ብሎ ሰውየውን አዛ ቦታ ለረዥም ግዜ እንዳስቀመጠው ባስብ ባስብ ሊመጣልኝ አልቻለም፡፡ ግን ይሄው እኛም እንደቆሰልን እሱም እንዳቆሰለን አለ፡፡ የበለጠ ጉዳዩን ከባድ የሚያደርገው ደግሞ ይህንን የእውቅና ፈቃድ ወረቀት አንድ ፓርቲ ሳይዝ አዳራሽ መከራየት አይችል፣በሬድዮና በቴሌቪዥን ማስታወቅያ ማስነገር አይችል፣በጋዜጣ ጥሪ ማስተላለፍ አይችል፣በራሪ ወረቀት መበተን አይችል፣በመኪና ተዘዋውሮ በድምጽ ማጉያ መቀስቀስ አይችልም በአጠቃላይ ምንም ማድረግ አይችልም እንደማለት ነው፡፡ የመጀመርያው ወሳኝ ሰው ይሄ ነው ማለት ነው ለፈረደብን ተቃዋሚዎች፡፡  ስለዚህ ከህዝብ ጋር ለመገናኘት ፈተናው የሚጀምረው ከዚህ ሰውዬ ነው፡፡ ኢህአዴግም ከህዝብ ጋር መገናኘትና መወያየት የዋዛ እንዳልሆነ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚጠቁመን ይሄን ሃላፊነት የማይሰማውን ግለሰብ የመጀመርያ መሰናክል በማድረግ ነው፡፡ ልብ ይስጣቸው ለአቶ ማርቆስ፡፡

ሌላው መሰናክል ደግሞ ይህንን የእውቅና ፈቃድ ይዘን አዳራሽ ለመከራየት የምናየው ፈተና ነው፡፡ አዳራሽ ለመከራየት የምናደርገው አሩጫ እጅግ ከፈጠነ ሳምንት ይፈጃል፡፡ አዳራሽ መረጣ አካሂደን ለመከራየት ደግሞ ያለው ችግር ለተቃዋሚዎች  ከባድ ነው፡፡ አዳራሽ ለመምረጥ ከመስፈርቱ ጀምሮ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ካልቻልን በስብሰባው ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ ቀላል እንዳልሆነ ስለምናውቅ ስንመርጥ በጥንቃቄ ነው፡፡ ስንመርጥም ሰፊ፣ ለትራንስፖርት አመቺ፣ አማካኝ ቦታ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ከዚህ ውስጥም ለተቃዋሚ ምርጫ ውስጥ የሚገባው የአዳራሽ ቁጥር ከሁለት አይበልጥም፡፡ እነዚህ የምንመርጣቸውን አዳራሾች አንዲያከራዩን ስንጠይቅም የተለያየ ምክንያት በማቅረብ ሲያጉላሉን ለታዘበ አዳራሹን የምንከራየው ሳይሆን የምንገዛው ነው የሚመስለው፡፡ በገንዘብ የምንከራየው ሁሉ አያስመስሉትም፡፡ በሃላፊነት አዳራሹን ለማከራየት የተቀመጡትም ሰዎች የሚታይባቸው ፍርሃት፣በራስ ያለመተማመን ስሜት እጅግ በጣም ያሳዝናል፡፡ አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ እነዚህን ሁኔታዎች በትእግስት መቋቋም ይጠበቅበታል፡፡ ምን አማራጭ አለው ትግልስ የተባለው ለዚሁ አይደል፡፡ እዚህ ላይ በጣም የሚቆጨኝ ያኔ 97 ምርጫ ላይ አዲስ አበባን ተረክበን ቢሆን ይሄ አሁን የምናየው ስብሰባ ለመጥራትና ለማድረግ እንቅፋት እና ከፍተኛ ችግር የሆነብን ነገር ምን ያህል ቀሎን በነበረ እላለሁ፡፡ እንደውም በፋንታው ኢህአዴግ አዳራሽ እኛን ለማስፈቀድ ይመጣ እንደነበር ሳስብ ቅንጅት ምን ያህል የማይረባ የፖለቲካ አመራር እንደሰጠ የሚያሳይ ስለሆነ በታሪኬ የማልረሳው ቀሽም የፖለቲካ ስህተት ነው እላለሁ፡፡

ይሄ ከላይ የጠቃቀስኳቸው ተቃዋሚዎች ስብሰባ ለመጥራት የሚያልፉባቸውን ሁለት ከባድ መሰናክሎችን ለግንዛቤ እንዲረዳችሁ በማሰብ ያስቀመጥኩት እውነት ነው እንጂ የዚህ ጽሁፍ አላማ ይሄ ሆኖ አይደለም፡፡  ጹሁፌ የሚያጠነጥነው ከሰሞኑ በኢዴፓ ላይ በደረሰው የስብሰባ መደናቀፍ ጉዳይ ላይ ብቻ ይሆናል፡፡

ኢዴፓ ከሰሞኑ የህዝባዊ ስብሰባዎችን በአምስት ከተሞች ማለትም በአዲስ አበባ፣በመቀሌ፣በባህር ዳር፣በደሴ እና በሃዋሳ ለማካሄድ አቅዶ በመንቀሳቀስ ላይ ነበር፡፡ ከነዚህ ህዝባዊ ስብሰባዎች መካከልም  የዋና ከተማዋ የአዲስ አበባ ህዝባዊ ስብሰባ አንዱ ነው፡፡ ለዚህ ህዝባዊ ስብሰባ መሳካትም ከሁለት ወር በፊት ጀምሮ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ላይ አመራሩ ደፋ ቀና ሲል ሰንብቷል፡፡ ለዚህም ይረዳው ዘንድ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከመግባቱ በፊት የመጀመሪያ ያደረገው ነገር የእውቅና ፈቃድ ደብዳቤ በእጁ መያዝ ነበር፡፡ ይህንንም ከአንድ ወር በፊት ጉዳዩ ከሚመለከተው የአዲስ አበባ ህዝባዊ ስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ፍቃድ ክፍል ለአምስት ቀናት ተመላልሶ በእጁ አስገባ፡፡ ከዛ በኋላ ለስብሰባው በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ ሲንቀሳቀስና ዝግጅቱን ሲያካሂድ ቆይቶ ለስብሰባው ሦስት ቀን ሲቀረው የህዝባዊ ስብሰባ ወሳኝና የመጨረሻ ምእራፍ ወደ ሆነው የቅስቀሳ ስራ ለመግባት ዝግጅቱን አጠናቀቀ፡፡ አስፈላጊውን ለቅስቀሳ የሚሆኑትን ነገሮች ሁሉ በእጁ አስገብቶ እሮብ በ9/11/2006 ዓ.ም በቅስቀሳው  ላይ የተመደቡ አባላቶች የሐምሌ ብርድና ዝናብ ሳይበግራቸው ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጊዮን የሚገኘው ቢሮ ተገናኘን፡፡ የቅስቀሳ መኪናችንን በባነር አስጊጠን፣ ሞንታርቦና ጄኔሬተራችንን በአግባቡ ጭነን፣ በራሪ ወረቀቶቻችንን ይዘን ለወሳኙ ጉዞ እራሳችንን አዘጋጀን፡፡ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓትም ወደ አዲስ አበባ አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን ጋር በቅስቀሳ እና በበራሪ ወረቀት ግንኙነት አድርጎ ወደ ስብሰባ የመጋበዝ ስራ ተሰማራን፡፡ የዛን ቀን ሽሮ ሜዳ አካባቢ ህዝብ የተሰበሰበበት ቦታ አትቀስቅሱ ውጡ ከማለት ውጪ የገጠመን ችግር የለም፡፡ ከቀኑ 11 ሰዓት ቅስቀሳችንን ስንጨርስ ከህዝቡ በርቱ፣ ከጎናችሁ ነን፣ የያዛችሁት መንገድ ለትውልድ የሚበጅና የሚመጥን ስለሆነ ወደ ኋላ እንዳታፈገፍጉ ከሚል የማበረታቻ ቃል ጋር ስለሆነ በውሎአችን ተደስተን ነበር የገባነው፡፡

በነጋታው ሀሙስ እንደተለመደው ከትናንት ውሎአችን ያገኘነውን ልምድ ተጠቅመን የዛሬን ምን ማድረግ እንዳለብን ከተነጋገርን በኋላ አቅጣጫ ቀይሰን ለሚኒባስ ሹፌራችንም የምንጓዝበትን መንገድ ነግረነው ሜክሲኮ ዙሪያ ቅስቀሳ ለማድረግ ተንቀሳቀስን፡፡ ከጊዮን ተነስተን በአራተኛ ክፍለ ጦር አድርገን ወደ ጨርቆስ ገብተን በገነት ሆቴል ጋር ወጥተን ቀስተ ዳመና ስፖንጅ ፋብሪካ ጋር ስንደርስ የመጀመሪያው ችግር ተፈጠረ፡፡ አስፋልቱ ላይ ቆመን ሌላም ጊዜ ቅስቀሳ ላይ እንደምናደርገው በራሪ ወረቀት በመበተን ላይ እንዳለን አንድ ፖሊስ ወደ መኪናው ተጠግቶ ፈቃድ ጠየቀን ፈቃዳችንን አሳየነው፡፡ ፖሊሱ በያዘው የእጅ ስልክ ወደ ሆነ ቦታ ደውሎ አናገረና “የያዛችሁት የስብሰባ ፍቃድ እንጂ የቅስቀሳ ስላልሆነ ወደ ቄራ ፖሊስ ጣቢያ ተጠርታችኋል እኔም ይዘህ ና ተብያለሁ” አለ፡፡ እኔም ያሉትን አባላቶች አረጋግቼ ወረቀት ለመበተን የወጡትንም ጠብቄ ገባንና ወደ ቄራ ፖሊስ ጣቢያ ጉዞ ጀመርን፡፡ ሁላችንም የመሰለን ጉዳዩ ስላልገባቸው እንጂ ምን የተለየ ፍቃድ አለ ከዚህ በፊት  ስንቀሰቅስ የነበርነው አሁን በያዝነው ፈቃድ ነው እያልን ጉዳዩ ቀላል እንደሚሆን ገምተን ቄራ ፖሊስ ጣቢያ ደረስን፡፡ የያዘንም ፖሊስ ሳጅን አንተነህ ይባላል ለኢንስፔክተር አየለ አበበ አስረክቦን ወዲያው ከአካባቢው ተሰወረ፡፡ ኢንስፔክተር አየለም ሳጅን አንተነህ ያለውን በመድገም “ህገ-ወጥ ተግባር ፈጽማችኃል ” አለን እኛም የነበረንን የረዥም ግዜ ህዝባዊ ስብሰባ የማድረግ ልምድና ይሄ አሁን የሚሉን ነገር አዲስ መሆኑን ለማስረዳት ሞከርን ምንም ልንግባባ አልቻልንም፡፡ በኋላ ላይ ሳስበው እሳቸው የታዘዙትን እንጂ የያዝነው ወረቀት ተገቢ መሆኑን አጥተውት እንዳይደለ ነው የተረዳሁት፡፡ በመጨረሻ ቃል ስጡ ተብለን እነሱ ህገ-ወጥ ነው ያሉትን ነገር እኛ ህጋዊ እንደሆነ አስረግጠን እኔን ጨምሮ 7 የአዲስ አበባ ኮሚቴ አባሎች ቃላችንን ሰጠን፡፡ ቃላችንን ሰጥተን ከጨረስን በኋላ የክፍለ ከተማው ፖሊስ አዛዥ ከሌሎች የፖሊስ አባሎች ጋር ሆኖ 9 ሰዓት አካባቢ ወደ ጣቢያው በፒካፕ የፖሊስ መኪና ገቡ፡፡ ትንሽ ቆይታ ካደረጉ በኃላ ግቡ ተብለን ገባንና በፊት ያናገሩን ሁለት ፖሊሶች ያሉትን ነገር እሳቸው መልሰው ነገሩን የሳቸው ለየት የሚለው በከፍተኛ ቁጣና ማንአለብኝነት መሆኑ ነው፡፡ እኛም ተገቢ ያልነውን ነገር ነገርናቸው በመጨረሻም ‹‹ከዚህ በኋላ ቅስቀሳ ማድረግ እንደማንችልና ዋስ እያስጠራ እንዲለቀን ለኢንስፔክተሩ ትዕዛዝ አስተላልፈው እኛን ጥለው ወጡ፡፡ እደጅ ሲወጡ ሚኒባሱን ፊት ለፊት ሲያዩ የትራፊት ፖሊስ ጥሩ ብለው አዘዙ የትራፊክ ፖሊስ በሚያስገርም ፍጥነት ከተፍ ብሎ ለሀላፊው ሰላምታ ሰጥቶ ምን ልታዘዝ አላቸው፡፡ ሀላፊውም “ይሄን ሚኒባስ ያለ ስራህ ስትሰራ ተገኝተሀል ብለህ ታርጋውን ፍታና ቅጣው” የሚል ቀጭን ትእዛዝ አስተላልፈው በመኪናቸው እብስ አሉ፡፡ ያዛዡን ትእዛዝ በጆሮአችን ሰምተን እንደጨረስን የገረመኝ ትራፊኩ ለሹፌሩ የነገረው የቅጣት ምክንያት ነው፡፡ “ቅድምም ፊሽካ እየነፋሁ ጥለኸኝ መጥተሀል ስለዚህ ታርጋህ ይፈታና ትራፊክ ጽ/ቤት ሄደህ ቅጣቱን ትከፍላለህ” ብሎት ታርጋውን ይዞት ወጣ፡፡ በጊዜው የነበርነው አባላቶች ከኛ መታሰር በላይ የልጁ (የሹፌሩ) በዚህ አይነት ህገ-ወጥ ምክንያት ታርጋው መፈታቱ በጣም ስላበሳጨን ሁላችንም በአንድ ድምጽ ታርጋው ካልተመለሰለት እንደማንወጣ ተስማማን፡፡ ፖሊሶቹም ከየት የመጣ ትእዛዝ እንደሆነ ባይታወቅም ዋሱ ቀርቶ ሁላችንም ወደ ቤታችን እንድንሄድ በኤንስፔክተሩ ተነገረን፡፡ የሹፌሩ ጉዳይ እልባት ካላገኘ አንሄድም ከተከሰስንም እኛ ነን እንጂ እሱ መሆን የለበትም ብለን ብዙ ተጨቃጨቅን፡፡ በኃላ ላይ አንድ ፖሊስ ተሰጥቶን ጉዳያችንን ትራፊክ ጽ/ቤት እንድናስረዳ ተባለና ወጣን በኋላ ላይ ከፖሊስ ጣቢያው እንድንወጣ ብቻ ስለፈለጉ የተሰራ ሴራ እንጂ የሹፌሩ ችግር እንዲፈታ አለመሆኑን ትራፊክ ጽ/ቤት በደረስን ጊዜ ተረዳሁ፡፡ ትራፊኮቹም ህግ ተላልፏል የተባለን ሰው በህግ መሰረት መቅጣት እንጂ ስለ ሌላው ነገር እንደማያውቁ ነግረውን የሀሙስ የቅስቀሰ ስራ በህገ-ወጥ መንገድ ተደናቅፎ ውሎአችን በአሳዛኝ ሁኔታ ተደመደመ፡፡ እዚህ ላይ ሹፌር መለስ ያየሁበት ጥንካሬና በራስ መተማመን ሳላደንቅለት አላልፍም፡፡ አባል ላልሆነበት ፓርቲ እንደዚያ በቁርጠኝነት ምንም ሳይደናገጥ ያሳየን ትብብር ከልብ እንድኮራበት አድርጎኛል፡፡ “በእኛ ጉዳይ ተጉላላህ” ስለው “የኔም እኮ ጉዳይ ነው ዛሬ በእናንተ ላይ የደረሰው ችግርና የሚወራባችሁ አሉባልታ ያለውን ልዩነት ተረድቻለው” ነበር ያለኝ፡፡ በኃላ ላይ ስደውልለት 500.00(አምስት መቶ ብር)እንደተቀጣ ነግሮኛል፡፡ ወደ 11 ሰአት ቢሮ ገባንና የቀን ውሎአችንን ተነጋግረን የተሰራብን ህገ-ወጥ ተግባር መሆኑን መግባባት ላይ ደርሰን ከሚመለከተው አካል ጋር መነጋገር እና ችግሩን መፍታት ተገቢ መሆኑን ተግባብተን በበነጋታው ከእኔ ሌላ ስራ አስፈጻሚዎች ተጨምረን ቅስቀሳው እንዲቀጥል  ውሳኔ ላይ ደርሰን ወደየቤታችን ተለያየን፡፡     በበነጋታው እንደተባባልነው በጠዋት ተገናኝተን አስፈላጊውን ነገር አሟልተን ለቅስቀሳ ወጣን፡፡ ጉዟአችንም እስከ 5 ሰዓት መልካም ስለነበር የትናንትናውን ቅስቀሳ ማደናቀፍ ትክክል አለመሆኑ ገብቷቸዋል ብዬ እንዳስብ አስችሎኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ልክ አምስት ሰዓት ላይ በአማኑኤል አድርገን በገዳመ እየሱስ ቤተክርስቲያን በኩል ወደ 18 ማዞሪያ ቀለበት መንገድ ጉዞ እንደጀመርን መኪናውን የትራፊክ ፖሊስ አስቆመው፡፡ የትራፊክ ፖሊሱም ፈቃድ ጠይቆ ፈቃድ ሲሰጠው “ይሄ የሚለው ስብሰባ አድርጉ እንጂ ቀስቅሱ የሚል አይደለም  የፈቃድ ወረቀቱ ላይ ደግሞ የዚህ ሚኒባስ ታርጋ መጻፍ ሲገባው ስላልተጻፈ ህገ-ወጥ ናችሁ መኪናው ይቀጣል” እያለ የተቀናጀ በሚያስመስል ሁኔታ መገናኛ የያዙ ፖሊሶች ከተፍ አሉ፡፡ በዚህ ግዜ በቃ የቲያትሩ መጋረጃ መከፈቱ ገባኝ፡፡ ወዲያው መኪናው መቀጣት አለበት የሚለው ትራፊክ ከፖሊሶቹ ጋር አያይዞን ካጠገባችን ዘወር አለ፡፡ የያዙን ፖሊሶችም ወደ ጣቢያ መሄድ እንዳለብን ነግረውን ጦር ሃይሎች አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱን፡፡ ጣቢያው እንደደረስን ያው እንደተለመደው የተከሰስንበት ጉዳይ ተገለጸልን፡፡ የዛሬውን ክስ ለየት የሚያደርገው መስኪድ አካባቢ ቀስቅሳችኋል የሚል መሆኑ ነው፡፡ ምን ያህል የህግ አስፈጻሚው የፈለገውን ህገ-ወጥ ድርጊት በግለሰብ ላይ እየለጠፈ እንደሚያስር የሚያሳይ ክስ ነበር የተመሰረተብን እኔ አንድ የህጋዊ ፓርቲ አመራር አባል ሆኜ እንደዚህ በፈጠራ ክስ የምታሰር ከሆነ አንድ ተራ ኢትዮጵያዊ ወገኔ በነዚህ ህግ አስፈጻሚዎች መዳፍ ከወደቀ ምን ሊሆን እንደሚችል ሳስበው ያስጨንቀኛል፡፡ የሆነው ሆኖ የቲያትሩ አንዱ አካል እንደሆነ ስላወቅን የሚሰሩትም ተግባር ዋና አላማው ስብሰባውን የማደናቀፍ እንደሆነ ስለተረዳን ተገቢ ያልነውን ቃል ሰጥተን እደጅ በረንዳው ላይ ቁጭ አልን፡፡ ስራ አስፈጻሚዎቹ እደጅ ቁጭ ብለን  ቀኑ እየገፋ ሰአቱም እያለቀ ሲሄድ ቢሮ ካሉት ስራ አስፈጻሚዎች ጋር በመነጋገረ ስብሰባው መሰረዝ እንዳለበት ከቀኑ 9 ሰዓት አካባቢ ተስማማን፡፡ ምክንያቱም ቅስቀሳ ሳናደርግ ቅዳሜ አዳራሽ ብንሄድ ሰው የማግኘት እድላችን ጠባብ እንደሚሆንና የስብሰባው አዳራሽ በሰው አለመሞላት ደሞ የገዢው ፓርቲ ሚዲያ ለምን አላማ ሊያውለው እንደሚችል በመግባባት ነው፡፡ በመጨረሻ ከቀኑ 10፡30 ላይ ወደ ክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ ኑ ተብላችኋል ተብለን ወደዚያው አመራን፡፡ በአብነት እድርገን ጉዞ ስንጀምር ግን በመንገድ የምናየው ነገር በአካባቢው ከፍተኛ ችግር እንደነበር የሚያሳይ ነው፡፡ ሱቆች ተዘግተዋል፣ መኪኖች ተሰባብረዋል መንገዱ በትልልቅ ድንጋዮች ተሞልቷል አልፎ አልፎም ፖሊሶች የተወሰኑ ሰዎችን በግሩፕ በግሩፕ አድርገው በየመንገዱ ይዘው አየን፡፡ ወደ ፖሊስ ጣቢያውም ስንደርስ የገጠመን ላየነው ነገር ማረጋገጫ የሚሆን ጉዳይ ነው፡፡ ፌደራል ፖሊሶች የድንጋይ መከላከያና የአስለቃሽ ጋዝ መተኮሻ መሳሪያ ይዘው መምሪያውን ሞልተውት አገኘን፡፡ ወደ ውስጥ ገብተን ለመምሪያው እረዳት ሃላፊ ምክትል ኮማንደር ሲሳይ ተርፋሳ የወሰደን ፖሊስ ሲያስረክበን በከፍተኛ ቁጣ “አትላካቸው አላልኩትም ነበር” አለና ሞባይላችንን አጥፍተን ቢሮ እንድንገባ አዘዘን፡፡ ቢሮ አስገብቶ ስማችንን፣ አድራሻችንን ከተቀበለ በኋላ የታሰሩትን የሙስሊም ተከታዮች ሲጭኗቸው እንዳናይ ይመስለኛል ከነሱ ነጥሎ ጓሮ ውሀ ልክ ላይ አስቀመጠን፡፡ ትንሽ ከቆየን በኋላ በድጋሚ ጠርቶን ስለተፈጠረው ነገር በጥሩ ሁኔታና ለመግባባትና ለመደማመጥ በሚጋብዝ ሁኔታ ንግግር እያደረገ እያለ ኮማንደር ሀይለ ማርያም የጣቢያው አዛዥ መሆኑን ቆየት ብዬ ነው የገባኝ ግለሰብ ተንደርድሮ ገብቶ‹‹ እንዳትለቃቸው ሁሉንም ከዚህ የሁከት ተግባር ጋር ግንኙነት ሲያደርጉ አግኝቻቸዋለሁ ብለህ ቃላቸውን እየተቀበልክ እሰራቸው ይህች አገር ስትኖር ነው እናንተም የምትኖሩት ህገ-መንግስቱም የሚኖረው እናንተ ማናችሁ? ምን እንደምታመጡ አያችኋለው›› ብሎ በከፍተኛ ቁጣ ተናገረ፡፡ መልስ ለመስጠትና ለማስረዳት ብንሞክርም ፍቃደኛ አልሆነም፡፡ በመጨረሻ ወደ በረንዳ ውጡ ተብለን ትንሽ እንደቆየን ያ አራስ ነብር ሆኖ የነበረው ኮማንደር በምን ምክንያት እንደሆነ ባናውቅም ወዲያው ቀዝቅዞ ተመልሶ መጣና “መሄድ ትችላላችሁ ከፈለጋችሁም ቀስቅሱ” የሚል ነገር ተናገረ፡፡ ለብዙዎቻችን ግን ፌዝ ነው የመሰለን ከምሽቱ 11 ሰዓት ይህን አይነት መልስ ማግኘታችን አንድ የድራማው መጋረጃ መዘጋቱን ሁለት ትናንትም ዛሬም ሲሰጥ የነበረው የህግ ጥሳችኃል ውትወታ ያሳየን ነገር ስብሰባው እንዳይካሄድ በኢህአዴግ ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን ብቻ ነው፡፡
ከዛ ከወጣሁ በኃላ የማብሰለስለው ነገር እውነት ኢህአዴግ እንደሚለውና እነደሚያወራው ነው፡፡ህግን ተከትለው ከሚሰሩ ፓርቲዎች ጋር፣የመድብለ ፓርቲ ስርአት እንዲጠናከር ከሚሰሩ አካላት ጋር በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመምከር ዝግጁ ነኝ የሚለው ለፕሮፖጋንዳ ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ለመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርአት ተግቼ እሰራለሁ ማለት በሰላማዊ ትግል የምንቀሳቀስ ፓርቲዎችን ማሰር ነው ማረጋገጫው፣ከደጋፊያችን ጋር ባለማገናኘት ነው የሚገለጸው እራሱን ሊፈትሽ ይገባል፡፡ከሰሞኑ በኢህአዴግ ላይ የሚታየው የህግ ጥሰት ግን በጣም አሳሳቢ ነው፡፡በመጭው መርጫ ተሳትፎአችንም ላይ ከወዲሁ ቀዝቃዛ ውሃ የቸለሰ ተግባር ነው፡፡ኢህአዴግ እራሱን ቆም ብሎ እውነት በሰላማዊ ትግሉ ላይ ያለው ቁርጠኝነት ምን ያህል እነደሆነ ካልመረመረ፣ለመድብለ ፓርቲ ስርአት መጠናከር ወሳኙን ሚና መጫወት ካልቻለ፣ከአፍ ባለፈ ለዴሞክራስያዊ ስርአት መገንባት ያለውን ወሳኝነት በተግባር ማረጋገጥ ካልቻለ ጫካው ነው እንጂ አዲስ አበባ የገባው አሁንም ኢህአዴግ ከጫካ አልወጣም ሚለውን የፌዝ ንግግር የሚጠናክረው እንዳይሆን እላለሁ፡፡ኢህአዴግ 23 አመት ሙሉ የችግር መፍቻና የመብት ጥያቄ ማስተንፈሻ አድርጎ ከሚጠቀመው ሰዎቻን የማሰርና የማገት ተግባር ምንም ለውጥ እንደማይመጣ በመረዳት እሱንም ሀገሪቷንም ከማይጠቅም ከዜሮ ድምር ፖለቲካ መውጣት አለበት እላለሁ፡፡ቸር እንሰንብት፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter