የብዙሃን ማህበራትና የኢህአዴግ ተቃርኖ፤የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረትን እንደማሳያ

Gizachew Animawግዛቸው እንማው

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጉዳዮች ዙርያ ተጽፎ በ1994 ዓ.ም  ለንባብ የበቃውና አቶ መለስ ዜናዊ ከሞቱ በኃላ በእርሳቸው አንደተዘጋጀ የተነገረን የፖሊሲ ትንታኔ ሠነድ ከገጽ 127 ጀምሮ የብዙሃን ማህበራት በተመለከተ በርካታ ገንቢ ነጥቦችን እንደሚከተለው ያስነብበናል ፡፡

‹‹የብዙሃን ማህበራት በየትኛውም የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት እጅግ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱና የአንድ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከሚመዘንባቸው መስፈርቶች አንዱ በስርዓቱ ውስጥ ያሉ የብዙሃን ማህበራት መጠንና ጥንካሬ ነው፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ  የብዙሃን ማህበራት ሚና ከዚህም የላቀ መሆን አለበት››

ገፅ 128 ላይ ደግሞ ‹‹የብዙሃን ማህበራቱ ግልፅና ለአዳዲስ አባላት ክፍት ከመሆን ባሻገር መሪዎቻቸውን በነጻና ዴሞክራሳዊ አኳኋን የሚመርጡና የሚሽሩ መሆን አለባቸው፡፡ ውስጣዊ አሰራራቸው ፀረ-ዴሞክራሲያዊ የሆኑ ማህበራት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው በጎ አስተዋፅኦ ሊያደርጉ አይችሉም፡፡››

የብዙሃን ማህበራቱ ዜጎችን በእኩልነት ማስተናገድና ግልጽ መስፈርት አስቀምጠው መስፈርቱን ላሟላ ዜጋ ሁሉ በራቸውን ክፍት ማድረግ  እንዳለባቸው ፤በራቸውን ቀርቅረው የጥቂቶች የሚሆኑበት አሠራር ኢ-ዴሞክራሲያዊ እንደሆነ በጥብቅ ያወግዛሉ፡፡ ጉዳዩ ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ቢሆንም፡፡

ሌላው ‹‹የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ትግልና አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› በሚል ርዕስ በመጋቢት 1999 ታትሞ የወጣው የኢህአዴግ የፖሊሲ ትንታኔ ሠነድ የብዙሃን ማህበራትን በተመለከተ ከላይ ካየነው ባልተናነሰ መልኩ ሰፊ ሽፋን ይሰጣል፡፡ ሠነዱ በገፅ 66 ላይ ታሪክን በማጣቀስ የብዙሃን ማህበራቱ በምዕራቡ ዓለም የዲሞክራሲ ሥርዓት እንዲፈጠርና እንዲጠናከር በማድረግ ረገድ ወሳኝ ሚና አንደተጫወቱ ይገልፅና የብዙሃን ማህበራቱ የዜጎች ማሰባሰቢያ መድረኮች ብቻ  ሣይሆኑ የዴሞክራሲ ማስተማሪያ ተቋማትም እንደነበሩ ያስገነዝባል ፡፡

ማንኛውም ጤነኛ አመለካከት ያለው ዜጋ ከላይ በተጠቀሱት ሁለት መጽሐፎች የተካተቱትን የፖሊሲ አቅጣጫዎች አንብቦ ስለጠቀሜታቸው ይጠራጠራል ብዬ አላስብም፡፡ ሊነሳ የሚችለው  ቁልፍ ጥያቄ ኢህአዴግ ምን ያህሉን ፖሊሲዎች ተግባራዊ  እያደረጋቸው ነው የሚል ይመስለኛል ፡፡

በዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ እምነት መሠረት ኢህአዴግ እንደ መንግስት ቢያንስ  ከላይ በዝርዝር ከቀረቡት የፖሊሲ አቅጣጫዎች ጥቂቶቹን እንኳን ተግባራዊ አድርጎ ቢሆን ፤በኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ ሊኖሩ የሚችሉ የብዙሃን ማህበራት በቁጥርም በይዘትም አሁን ካለንበት ተጨባጭ ሁኔታ የተለየ በሆነ ነበር፡፡

ማንም ሰው እንደሚረዳው ብዙሃን ማህበራት የህብረተሰቡን የተለያዩ ጥቅሞችና ፍላጎቶች በመወከል የሚጫወቱት ሚና ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ይህንን ሚናቸውን በተግባር አንዳይወጡና ራሳቸውንም በሚገባ እንዳያጠናክሩ በማድረግ ረገድ የመንግስት ጣልቃ ገብነት በዋና ምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡

ይህ አላስፈላጊ የሆነና ስግብግብነት የወለደው የመንግስት ጣልቃ ገብነት “በአንድ ራስ ሁለት ምላስ” እንዲሉ ኢህአዴግ ራሱ የፃፈውን ፖሊሲ አንዲሽርና በእያንዳንዱ እርምጃው ከራሱ አስተሳሰብ ጋራ አንዲቃረን ያደርገዋል ፡፡

ከላይ በተገለፁ ሠነዶች የተፃፉትን ተግባራዊ በማድረግ ማህበራቱ በገለልተኝነትና በነፃነት የሚሰሩበትን ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ይልቅ ኢህአዴግ የራሱ መሳሪያና መጠቀሚያ እንዲሆኑ በማድረግ  ከሀገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ተቃራኒ ሲቆም በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ( አቶ ልደቱ አያሌዉ “መድሎት” በተባለው መጽሐፋቸው ከገፅ 162 ጀምሮ በግልፅ እንዳስቀመጡት ባለፉት አመታት በገሃድ እንደታየው ኢህአዴግ  ከራሱ ፍላጎት ጋር አብረው የሚቆሙትን ማህበራት በተለያዩ መንገዶች የሚደግፈውን ያህል ከሱ ፍላጎት ጋር የማይቆሙትን ደግሞ በዚያው መጠን በተለያዩ ተፅዕኖዎች ለማዳከም ጥረት እንደሚያደርግና ራሱን ከሌሎች ጥቃት ለመከላከልና ሌሎችንም ለማጥቃት እንደ ጦርና ጋሻ እንደሚጠቀምባቸው ሊካድና ሊስተባበል በማይችል መጠን  በተደጋጋሚ መታየቱ ሌላው ኢህአዴግ ራሱ ከፃፈው ፖሊሲ ጋር የሚፈጥረው በደንብ ታቅዶበት፣ በእውቀት፣ስልጣንን ከበርካታ አቅጣጫዎች ከሚመጣ ማእበል ለመከላከል የሚደረግ ተቃርኖ ነው፡፡

መንግስት ማህበራትን የራሱ የፖለቲካ ጥቅም ማስከበሪያ መሳሪያ ከማድረግ ይልቅ ከተመሠረቱበት ዓላማ አንጻር በነፃነትና በገለልተኝነት እየሠሩ ለሀገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ በመፍጠርና ተገቢ የቁጥጥር ሥርዓት በመዘርጋት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ አቶ ልደቱ ከላይ በተጠቀሰው መጽሀፋቸው ያስገነዝባሉ፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ህብረት ድሮና ዘንድሮ

በአፍሪካ ደረጃ ሁሌም ቢሆን በመንግስታትና በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል ያለው ግንኙነት ገንቢ ሆኖ አያውቅም፡፡  ለዚህ ደግሞ እንደየ ሀገሮቹ ተጨባጭ ሁኔታ የሚለያዩ ቢሆንም ዋናው ምክንያት ተቋማዊ ነፃነት እንዲኖር፣የመማር ማስተማሩ ከመንግስት ተፅዕኖ ነፃ እንዲሆን (academic freedom)፣ እና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እንዲረጋገጥ በተማሪዎች የሚደረገው ንቅናቄ በመንግስት በኩል የሚበረታታ ሆኖ ስለማያውቅ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ህብረት በአፍሪካ ደረጃ እንጋፋ የተማሪዎች ማህበር ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካውያን ተማሪዎች ገና በቅኝ ግዛት ሥር ሆነው በገዢዎቻቸው ላይ ጥያቄ ማንሳት ሳይጀምሩ የተቋቋመና በኢትዮጵያ ታሪክም በገበሬውና ከብሔርተኛው ይበልጥ ተማሪው ነበር፡፡ መጀመሪያ የምሁራንና የምርምር መድረክነት ባህርይ የነበረው ሁኔታ በ1950ዎቹ መጨረሻና በ1960ዎቹ መጀመሪያ አቢዮታዊ እንቅስቃሴን እየያዘ መጣ፡፡ ለዚህ አጋዥ የሆኑ ነባራዊና ህሊናዊ ምክንያቶች ነበሩ ይላሉ ፕሮፌሠር ባህሩ ዘውዴ፡፡

ታሪክም አሁን ላለው ሁለንተናዊ ለውጥ የራሱን አሻራ ማሳረፍ የቻለ ተቋም ነው፡፡ እንደ ፕሮፌሠር ባህሩ ዘውዴ አተያይ ከሆነ ለሥርዓቱ ፀር በመሆን ከገበሬውና ከብሔርተኛው ይበልጥ ተማሪው ነበር፡፡

በመጀመሪያ የሀገሪቱ ሁኔታ በተለይም የገጠሩ አርሶ አደርና የከተማው ሠርቶ አደር የኑሮ ደረጃ እየከፋ መምጣቱ የዚህ የከፋ ተቃውሞ ነባራዊ መሠረት ነው፡፡ መንግስት ንቅናቄውን ለማፈን የሚወስዳቸውም እርምጃዎች ተማሪዎቹን ይበልጥ እልህ ውስጥ አስገባቸው፡፡ የተማሪዎች ተቃውሞና የመንግስት አፈና እርስ በእርስ እየተፋጩ በመጨረሻም የ1966ቱን አቡዮት ወለዱ፡፡ ተማሪዎቹ በንቅናቄያቸው የመጀመሪያ አመታት የታገሉት በነጻ ማህበር ለመደራጀትና ሀሳባቸውን በነፃ ለመግለፅ የሚችሉበት መፅሔት ለማቋቋም ነበር፡፡ የተማሪዎች ህብረት በተማሪዎች ዲን ቁጥጥር ስር ስለነበር ነፃ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡
ተቃውሞው እየተጠናከረ ሲሄድ መንግስት በተማሪዎች ላይ የፀረ-ተማሪ ፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ካካሄደ በኋላ በታህሳስ 19 የተማሪዎቹን መሪ ጥላሁን ግዛውን ገደለ፡፡ በማግስቱም መሪያችንን በክብር እንቀብራለን ብለው 6 ኪሎ ቅጥር ግቢ በተሰበሰቡት

ተማሪዎች ላይ የፀጥታ ሀይሎች ተኩስ ከፍተው የተወሰኑትን ህይወት ቀጠፉ አያሌ ተማሪዎችን አቆሰሉ፡፡ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ለለውጥ ባለው ፅናትና በመስዋትነት ስሜቱ ብዙም ወደር የሚገኝለት አይደለም፡፡
እንደዛሬው ሳይሆን በቀደመ ተክለ-ሰውነቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ህብረት በአፍሪካ ደረጃ እጅግ ጠንካራ የተማሪዎች ወንድማማችነት መፍጠር የቻለ ተቋም ነበር(Randi፣ the quest for expression)፡፡ እ.ኤ.አ ጥቅምት 1 1989 ዓ.ም ለህትመት የበቃው Ethiopian herald ጋዜጣ የኢትዮጵያ ተማሪዎች የሠሩትን አዲስ ታሪክና የተጫወቱትን ሚና በማጉላት የፊውዳሉን ሥርዓት በመቃወም ያደርጉት የነበረውን ተቃውሞ መቼም የማይረሳ የቅርብ ጊዜ ትውስታ (fresh memories) ነው፡፡ ተማሪዎች የከፈሏቸው  መስዋዕትነቶች የሀገራችን ብሔራዊ ቅርስ አካል ናቸው ሲል ጋዜጣው ይዘክራቸዋል፡፡
በዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ እምነት ትናንትም ዛሬም የኢትዮጵያ ተማሪዎች የህዝቡን አጀንዳ ተሸክመው የሚንቀሳቀሱ ዜጎች ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ትግሉን ከጫንካቸው ላይ አውርዶ እነሱ በትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ለማድረግ የሚያስችል ጠንካራ ተቃዋሚና የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ሀገሪቱ ውስጥ አለመፈጠራቸውና እንዲፈጠሩም  በመንግስት አለመፈለጋቸው ነው፡፡
ይህ እስኪሆን ድረስ ግን ተማሪዎች የህዝብን አጀንዳ ከመሸከም ባለፈ ዩኒቨርስቲዎችን እንደ አንድ ምቹ የህዝባዊ አጀንዳ መፍጠሪያ ቦታ አድርገው  መውሰዳቸው ዛሬም የማይቀር ይመስለኛል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ህብረት በዘመነ ኢህአዴግ

የዚህ  ፅሁፍ አዘጋጅ የተማሪዎች ህብረት አባል የነበርኩት ከፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል የሶሻል ሣይንስ ኮሌጅን በመወከል ነበር፡፡ በኮሌጁ ሥር ካሉ የትምህርት ክፍሎች የተመረጡ ተወካዮች የወቅቱ የኮሌጁ ዲን በነበሩት ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ ፊት እጅግ ትንቅንቅ የተሞላበትን የምረጡኝ ዘመቻ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ካደረግን በኋላ በምስጢር ድምፅ አሠጣጥ በከፍተኛ ድምፅ ለህብረቱ ኮሌጁን ወክዬ እንድሠራ መመረጤ ተገለፀልኝ፡፡

በዚህ ሁኔታ ወደ ህብረቱ ከሄድኩ በኋላ የህብረቱን የሥራ አስፈፃሚ አመራረጥ በተመለከተ የተለያዩ ወሬዎች መናፈስ ጀመሩ፡፡ የወሬዎችን ተጨባጭነት ለማጣራት የቀረብኩት አንድ የኦህዴድና የህብረቱ አባል በጣም ተናዶ ሣግ ሣግ እያለው በኢህአዴግ የተሰራውን ህገ-ወጥና መርህ አልባ ተግባር ከሀ እስከ ፐ ተረከልኝ፡፡ የህብረቱ ሥራ አስፈጻሚ ከመመረጡ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ኢህአዴግ ወደ ህብረቱ የመጡትን የተለያዩ ኮሌጅ ተወካዮች 4 ኪሎ ኢህአዴግ ፅ/ቤት በመሰብሰብ የመጀመሪያ ሦስት ተቀዳሚ አመራሮችን እንዳስመረጠ፤ በዚህም መሠረት ፕሬዚዳንቱ ከብአዴን ም/ፕሬዚዳንቱና ዋና ፀሐፊው ከኦህዴድ ሥም በመጥቀስ መመረጣቸውንና በነዚህ ተሿሚዎች ላይ ሌሎችን አባላት የማሳመንና ዩኒቨርስቲው አስተዳድር ለህብረቱ ስራ አስፈጻሚ ምርጫ ሲጠራ የማፅደቅ ሥራ ብቻ እንዲሠራ ኢህአዴግ የቤት ሥራ መስጠቱን አረጋገጠልኝ፡፡ እንደሚታወቀው ዛሬም ድረስ አመነበትም አላመነበትም ብዙኃኑ የዩኒቨርስቲ ተማሪ የሥራ ዋስትና     ከምረቃ በኋላ ለማግኘት የአባልነት ፎርም ይሞላል፡፡ ያኔም ከ90% በላይ የህብረቱ አባል የኢህአዴግ አባል እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡

የህብረቱ   የሥራ አስፈፃሚ ምርጫም የተባለውና የተጠበቀው ሆነ፡፡ ፕሬዚዳንቱ ከብአዴን፣ ም/ፕቄዚዳንቱና ዋና ፀሐፊው ከኦህዴድ፡፡የመጀመሪያውን መረጃ የነገረኝ የህብረቱ አባል ለሥራ አስፈጻሚው ለመወዳደር ራሱን አዘጋጅቶ  በግምገማ እንደወደቀ የግምገማውን መስፈርት በትንሽ ብጣሽ ወረቀት እያስነበበ አስረዳኝ፡፡
በተማሪዎች ህብረት በነበረኝ የ2001/2002 ሥራ ዘመን የታዘብሁትና የተረዳሁት  ነገር ቢኖር ኢህአዴግ ጥቅሙን ለማስከበር ምንያህል መርህ  አልባ ሥራ ሲሠራ እንደነበርና ወደፊትም ሊሠራ እንደሚችል ነው፡፡ ‹‹የተመረጡ›› የህብረቱ አመራሮች ለኢህአዴግ ጥቅምና ፍላጎት ዘብ መቆማቸውን ለማረጋገጥ ወጭ ደብዳቤዎችን ለኢህአዴግ ጽ/ቤት በግልባጭ ያሳውቁ ነበር፡፡

እዚህ ላይ ኢህአዴግ ከላይ በመግቢያዬ አካባቢ ከተጠቀሱ የራሱ ፖሊሲዎች ጋር ያለውን ተቃርኖ ማየቱ የኢህአዴግን መርህ አልባነት በሚገባ ያሳያል ብዬ አምናለሁ፡፡ ፖሊሲው የብዙሃን ማህበራት ለአዳዲስ አባላት ክፍት መሆን አለባቸው ይላል፤ አዳዲስ አባላት ግን ተቀባይነት ሊያገኙ የሚችሉት የኢህአዴግ አባላትና በኢህአዴግ ላይ ምንም አይነት ጥያቄ ላለማንሳት ለራሳቸው ቃል ከገቡ ብቻ ነው፡፡ፖሊሲው የብዙሃን ማህበራት ሁሉንም ዜጎች ማስተናገድ አለባቸው ይላል፤ በተግባር ግን እጅግ አግላይና አድሎ በተሞላበት ሁኔታ የፖለቲካ አመለካከትን ብቸኛ መመዘኛ በማድረግ እየተሠራበት ነው፡፡

ለምን የሚል ጥያቄ ሲነሳ ‹‹እያንዳንዱ አደረጃጀት በአብዮታዊ ዴሞክራቶች የማይመራ ከሆነ ለሥርዓቱ አደጋ ነው››የሚል መልስ ይሰጣል፡፡ ፖሊሲው ማህበራቱ ግልጽ መስፈርት እንዲኖራቸውና መስፈርቱን ላሟላ ዜጋ ሁሉ  እኩል እድል እንዲሰጡ ያስገድዳል፤ በተግባር ግን ኢህአዴግነት በስውር መስፈርትነት እየቀረበ ብዙዎችን ሲያደናቅፍ እያየን ነው፡፡ ፖሊሲው የብዙሃን ማህበራት የዴሞክራሲ ማስተማሪያ መድረክ መሆን አለባቸው ይላል፡፡ በተግባር ግን የብዙሃን ማህበራት/ተቋማት የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ስብከት ማዕከላት ናቸው፡፡

ማጠቃለያ

የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ሀገራዊ አጀንዳን ያነገበ/ያቀፈ ውይይት በማድረግ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱ ልዩ ጥበቃና ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡

በሀገራችን ከአፄ ሀ/ስላሴ አገዛዝ ጀምሮ የነበሩት እና ያሉት ገዢዎቻችን ዩንቨርሲቲዎች የሀገሪቱ ቁልፍ ተቋማት መሆናቸውን ስለተረዱ እና ስለሚያቁ ያለ የሌለ የፈሪ ጡንቻቸውን ሲያሣርፉባቸው አይተናል፤  እያየንም ነው፡፡ ይህ ከባድ ጡጫ በተማሪዎች ላይ የሚበረታው ሥልጣንን ከማጣት ከሚመጣ ሥጋት ነው፡፡ ዘላቂው መፍትሄ እና ያለው አማራጭ ሁለት  ነው፤እሱም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በተሟላ መልኩ መመለስና ተማሪዎቹ በትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግ አሊያም በጡንቻ የተማሪዎቹን የተለያዩ ጥያቄዎች መድፈቅና ለጊዜውም ቢሆን ፋታ ማግኘት፡፡
ምርጫው ለሀገር ጥቅም ዘብ በመቆምና ለተወሰነ ቡድን ጥቅም በመታገል መካከል ያለ ነው፡፡ ለሀገር ጥቅም ዘብ በመቆም ግን አብሮ መጠቀም ይቻላል !!!

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter