ህገ-መንግሰቱ እና ኮማንደሩ

Ermias Balkewኤርሚያስ ባልከው
የኢዴፓ ድርጅት ጉዳይ ኃላፊ

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሐምሌ 12 ቀን 2006 ዓ.ም ሜክሲኮ አደባባይ በሚገኘው የመብራት ሃይል መሰብሰቢያ አዳራሽ ለጠራው ሕዝባዊ ስብሰባ ከአዲስ አበባ መስተዳድር የስብሰባ ፍቃድ ክፍል ሰኔ 09 ቀን 2006 ዓ.ም የስብሰባ ፈቃድ ወስደን እንቅስቃሴ ጀመርን፡፡  ህዝቡ ጋር ለመድረስ ካሰብናቸው መንገዶች አንዱና ዋናው ከሀምሌ 09 እስከ ሃምሌ 12 ቀን 2006 ዓ.ም ድረስ በከተማው ውስጥ በተሸከርካሪ እየተዘዋወሩ ቅስቀሳ ማድረግ ነበር፡፡ ቅስቀሳውን ለማድረግ በታቀደው መሰረት እሮብ ሐምሌ 09 ቀን 2006 ዓ.ም ቅስቀሳ ተጀመረ፡፡ በእለቱ ምንም ችግር ሳይገጥመን ቅስቀሳው ተጠናቋል፡፡ በማግስቱ ሐምሌ 10 ቀን 2006 ዓ.ም ከጠዋቱ 4 ሰዓት ቡልጋሪያ የሚገኘው የቀስተ ዳመና እስፖንጅ ፋብሪካ አካባቢ ሲቀሰቅሱ የነበሩ የኢዴፓ የአዲስ አበባ ኮሚቴ አባላትና የስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑትን አቶ አዳነ ታደሰን ጨምሮ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የቄራ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ በመውሰድ በቁጥጥር ስር አዋሏቸው፡፡ በመጨረሻም ቃላቸውን በመቀበል ቅስቀሳ ማድረግ እንደማይችሉና እራሱን የቻለ የቅስቀሳ ፈቃድ እንደሚያስፈልግ በመግለጽ የምንቀሰቅስበትን መኪና አግባብ ያልሆነ ስራ ስትሰራ ተገኝተሀል በሚል ታርጋው ከተፈታ በኋላ ሹፌሩ 1000 ብር (አንድ ሺ ብር) ተቀጥቶ አመሻሹ ላይ እስረኞቹ ተለቀዋል፡፡

ይሄን ተከትሎ ከሌሎች የኢዴፓ አመራሮች ጋር በተነጋገርነው መሰረት እኔ ወደ አዲስ አበባ መስተዳድር ሄጄ ሃላፊዎች ለማነጋገር በተስማማነው መሰረት ወደ አዲስ አበባ መስተዳድር ሄድኩ፡፡ የስብሰባ ፍቃድ ሰጪ ክፍል ሃላፊ የሆኑትን አቶ ማርቆስ ብዙነህ አገኘኋቸው፡፡ እሳቸውን ለማነጋገር እንደመጣሁ፣ የመጣሁበትን ፓርቲ፣ ሀላፊነቴንና የመጣሁበትን ምክንያትም ገለፅኩ፡፡ ማለትም ኢዴፓ ከእሳቸው ቢሮ ስብሰባ ፍቃድ መውሰዱን አስታውሼ ስብሰባውን ለመጥራት ቅስቀሳ ስናደርግ ፖሊሶች አባላቶቻችንን መያዛቸውን ገለጽኩላቸው፡፡ እሳቸውም በማናለብኝነት ቅስቀሳ ማድረግ እንደማይቻል ገለጹልኝ፡፡ እሺ ታዲያ የቅስቀሳ ፍቃድስ የትነው የሚወሰደው ስላቸው አዲስ አበባ መስተዳድር ውስጥም ሆነ ከዛ ውጪ ያለ አካል የቅስቀሳ ፍቃድ እንደማይሰጥ ገለፁልኝ፡፡ በሰጡኝ መልስ በመገረም ሌላ ጥያቄ ልቀጥል ስል ሌላ ጥያቄ የማስተናገድ ፍላጎት እንደሌላቸው በቁጣም በግልምጫም ጭምር ገለጹልኝ፡፡ አቶ ማርቆስ ለ 20 ዓመታት ያህል በዚያ የሃላፊነት ቦታ ላይ ለምን ተቀመጡ ብዬ እያሰብኩና የራሴን መላምቶች  እየሰጠሁ ወጥቼ ሄድኩ፡፡

የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ አባላት በዚያው እለት ምሽት ላይ ተገናኝተን ቅስቀሳው ፍፁም ህገወጥ በሆነ መንገድ እንዲቆም መደረጉ ተገቢ አለመሆኑን በማመን ቅስቀሳው በነጋታው ሐምሌ 11 ቀን 2006 ዓ.ም. መቀጠል እንዳለበት ወሰን፡፡ የስራ አስፈጻሚ አባላት የሆንን ሰዎችም በቅስቀሳው ላይ እንድንገኝ ተስማምተን ወጣን፡፡ በዚህ መሰረት በጠዋት ሚኒባስ ተከራይተን ለቅስቀሳ ተንቀሳቀስን:: እንደወጣን ቀኑ አርብ ስለነበር የሙስሊም ወገኖች የአርብ ጸሎት (ጁምአ) ሰአት ከመድረሱ በፊት መርካቶ አካባቢ ማድረግ የሚገባንን ቅስቀሳ ጨረስን፡፡ መርካቶ ጣና አካባቢ ፖሊሶች ያስቆሙን ቢሆንም ፍቃዳችንን አይተው ለቀውናል፡፡ ከዚያም በበርበሬ ተራና በአብነት በኩል አድርገን ከኮካ-ኮላ ወደ አማኑኤልና አስራ ስምንት ኮልፌ የሚያወጣው ቀለበት መንገድ ጋር ስንወጣ እንደገና ትራፊክ አስቆሞን ፍቃዳችንን እንድናሳየው ጠየቀን፡፡ ያስቆመን ትራፊክ ፖሊስ ፈቃዳችንን ካየ በኋላ የያዝነው ፍቃድ የስብሰባ እንጂ የቅስቀሳ አለመሆኑን ገልፆልን ቅስቀሳ እንድናቆም እየነገረን ሌሎች ፖሊሶች ደርሰው በህግ እየተፈለግን እንደሆነ ገለጹልን፡፡ከዚያም በቁጥጥራቸው ስር እንድንሆን አድርገው ወደ በልደታ ክ/ከተማ የጦር ሃይሎች ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱን፡፡ በወቅቱ ሰአቴን ሳይ ከጠዋቱ 5 ሰዓት ነበር፡፡ የያዙን ፖሊሶች ለአለቆቻቸው ካስረከቡንና ከበላይ ሀላፊዎች ጋር ከተነጋገሩ በኋላ በየተራ እያስገቡ  ቃል ሲቀበሉን ክሳችን በሁለት ምክንያት መሆኑን ነገሩን፡፡  አንደኛው የቅስቀሳ ፍቃድ ሳይኖር መቀስቀስ፤ ሁለተኛው መስጊድ ላይ ሲቀሰቅሱ በመገኘት የሚል ሆነ፡፡

እኔም ስለመጀመሪያው ክስ ህዝባዊ ስብሰባ የማካሄድ ፍቃድ እንዳለንና ቅስቀሳ ለማድረግ ግን ሌላ ፍቃድ ሰጪ አካል እንደሌለና ፈቃድ እንደማያስፈልግ ነገርኩዋቸው፡፡ ሁለተኛውን ክስ በተመለከተ ቁሙ ተብለን የቆምነው በትራፊክ ፖሊስ እንደሆነ፤ የቆምነውም ትራፊኩን ለማናገር  እንጂ ለመቀስቀስ አለመሆኑን በአካባቢውም ላይ መስጊድ ይኑር አይኑር የምናውቀው ነገር እንደሌለ፡፡ ቦታውም ቀለበት መንገድ ስለነበረና ብዙም ሰው ስላልነበረበት ተቁሞ የሚቀሰቅስበት ቦታ እንዳልሆነ በመግለፅ ክሱም ተገቢ እንዳልሆነ በመቃወም ቃሌን ሰጥቻለው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሳጅን አውራሪስ የሞያውን ስነምግባር የጠበቁ ሰው ሆነው ስላገኘኋቸው ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡ እስከ ቀኑ 10 ሰዓት ድረስ በምርመራው ቦታ ከቆየን በኋላ ጥቁር አንበሳ አካባቢ  ወደሚገኘው ልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ተወስደን፡፡

በመንገድ  ላይ ስንሔድ አካባቢው ብዙም ሰላም አይመስልም ነበር፡፡ በተለይ በርበሬ ተራ አካባቢ ብዙ ፖሊሶች እንዳሉና  ከሰአታት በፊትም ድንጋይ ውርወራ እንደነበር የሚያሳይ ሁኔታ እንደነበር ለማየት ችለናል፡፡ ፖሊስ መምሪያ ስንደርስ የድንጋይ መከላከያ ጭብል፣ ጉልበታቸው ድረስ የሚደርስ መጋጫና አስለቃሽ ጋዝ የመተኮሻ መሣሪያ የያዙ ፖሊሶች ግቢው ውስጥ በብዛት ነበሩ፡፡ ወደ ግቢው ልንገባ ስንል በር ላይ ያለው ጥበቃ ምንድን ናችሁ አለን ከጦር ሀይሎች  ይዞን የመጣው ፖሊስ ወረቀት ሲበትኑ ተይዘው ነው አለው፡፡ ወደ ግቢው ከገባን በኋላ ምክትል ኮማንደሩ ምንም ዓይነት የስልክ ንግግር ማድረግ እንደማንቻል በቁጣ ነገሩን፡፡ ከዚያ ወደቢሮዎቸው አስገብተው ስማችንንና ሃላፊነታችንን በየተራ ከጠየቁን በኋላ ከኃላፊዎች ጋር ተነጋግሬ እጠራችኋለሁ በማለት ከቢሮቸው እንደገና አስወጡን፡፡

ኮማንደሩ መልሶ እስኪጠራን ድረስ በረዳው ላይ ቆመን እያለን ከአንዋር መስጊድ አካባቢ በተነሳው ብጥብጥ የተያዙ በርካታ ሙስሊም ወንድሞችን አይተናል፡፡ወዲያውኑ ከበረንዳው አካባቢ ዞር እንድንልና በጣቢያው ጓሮ በኩል ተቀምጠን እንድንቆይ ተደረገ፡፡ ከጥቂት ስአት ቆይታ በኋላም እንደገና ወደ ምክትል ኮማንደሩ ቢሮ ተጠርተን ገባን፡፡ ኮማንደሩም ያለቅስቀሳ ፈቃድ መቀስቀስ እንደማይቻል፤ ሁላችንም መኖር የምንችለው ሰላም ሲኖር እንደሆነና ሌላም ጊዜ ቅስቀሳ ለማድረግ ከተፈለገ የግድ የቅስቀሳ ፍቃድ የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ነገረን፡፡ እኔም የቅስቀሳ ፈቃድ የሚሰጥ ምንም አይነት መንግስታዊ ተቋም እንደሌለና ይህንንም አዲስ አበባ መስተዳድር ድረስ ሄደን ጠይቀን በአቶ ማርቆስ በኩል እንደተነገረን በድጋሚ ገለፅኩላቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ ከምክትል ኮማንደሩ ጋር እየተነጋገርን በነበርንበት ወቅት የመምሪያው ዋና ኮማንደር የሆኑት ኮማንደር ኃይለማርያም ወደ አለንበት ቢሮ ገቡ፡፡ እንደገቡም ጠረጴዛውን በሃይል እየደበደቡ ማንም ሊያድናቹ አይችልም፣ እኔ የምጠብቀው ህገ-መንግስቱን ነው፣ ከህገ-መንግስቱ ሌላ ማንም ሊያዘኝ አይችልም – ማንም ሊያድናችሁ አይችልም በማለት በጩኸት ተናገሩ፡፡ እኔም የሚናገሩት ነገር ግራ ስላጋባኝ የተከሰተውን ነገር ለማስረዳት ፈልጌ – ገና “እኛም እኮ” ብዬ መናገር ስጀምር “ዝም በል!” በማለት ንግግሬን በቁጣ አቋረጡኝ፡፡ ከዚያም “እሰራቸውና ጉዳያቸው ይጣራ” የሚል ትእዛዝ ለምክትላቸው ሰጥተው ወጡ፡፡ እኛም የትኛውን የህገ-መንግስት ድንጋጌ እንደጣስን ሳይገባን፣ ይልቁንም የኛ ህገ-መንግስታዊ መብት በንግግርም ሆነ በድርጊት በየደቂቃው እየተጣሰ ማየታችን አስገርሞን ዝም ብለን የሚያደርጉትን ማየት ቀጠልን፡፡ እንደ ኮማንደር ሀይለማርያም ያሉት ሰዎች በዚህ ቦታ ላይ የተቀመጡት ለምን ዓላማና ለማን መብት መከበር እንደሆነ ማወቅ ተሳነኝ፡፡

በረንዳ ላይ ቆመን የት ወስደው እንደሚያሳድሩን በመጠባበቅ ላይ እያለን ዋናውና ምክትል ኮማንደሩ ረዘም ላለ ጊዜ ሲያወሩ አየን፡፡ ትንሽ ቆየት ብሎም ኮማንደር ሀይለማርያም ቀደም ብሎ ሲያሳዩት ከነበረው የቁጣ መንፈስ በተለየ በተረጋጋ ስሜት ወደኛ መጡ፡፡ ኮማንደሩ በእጃቸው የያዙትን የእኛን የስብሰባ ፈቃድ አስተውለው እያዩ – “እዬው-እዚህ የፍቃድ ወረቀታቹ ላይ የፖሊስ ጥበቃ እንደሚያስፈልጋቹ ጠይቃችኋል፣ እናንተ ግን ለእኛ ሳትነግሩን ብጥብጥ ያለበት አካባቢ ዘላችሁ ገባችሁ፡፡ አሁን በናንተ ላይ ጉዳት ቢደርስ ማን ተጠያቂ ሊሆን ነው? አንድ ችግር ቢደርስባቹ መንግስት እንደዚህ አደረገን ልትሉ ነው?” ካሉ በኋላ-አሁንም እንደገና “ለምን የቅስቀሳ ፈቃድ አልያዛችሁም? ፈቃድ የሚሰጠን አካል አለ እኮ!” አሉን፡፡እኔም በድጋሜ-የስብሰባ ፈቃድ እንጂ የቅስቀሳ ፈቀቃድ እንደማያስፈልግ፣ እንዲህ አይነት ፈቃድ የሚሰጥ አካልም አገሪቱ ውስጥ እንደሌለ፣ ባለፉት ዓመታት ስንሰራበት የኖርነው ልምድም ከዚህ የተለየ እንዳልሆነ፣ ማንም አካል ህዝባዊ ስብሰባ ከጠራ ቅስቀሳ የሚያካሂድ መሆኑን አስቀድሞ የሚታወቅ መሆኑን፣ ይህንንም በተደጋጋሚ አዲስ አበባ መስተዳድር ድረስ ሄደንና አቶ ማርቆስን ጠይቀን እንዳረጋገጥን ነገርኳቸው፡፡
ኮማንደሩም “አቶ ማርቆስ እንዲህ ሊል አይችልም – አሁን ደውዬ ልጠይቀው?” አሉን፡፡ “አዎ ደውለው ይጠይቁት” አልኳቸው፡፡ ስልካቸውን አውጥተው ለመደወል የሞከሩ ከመሰሉ በኋላ መደወሉን ተውት፡፡ ከትንሽ ቆይታ በኋላም ኮማንደሩ መልሰው ጣብያ ልታድሩ የምትችሉበት ምክንያት ስለሌለ፤ እንዲያውም ከፈለግን ቅስቀሳ ማድረግ እንደምንችል ነገሩን፡፡ ነገር ግን ቅስቀሳውን ልናደርግ የሚገባንን ጊዜ ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ በመታሰርና በመፈታት አልፎ ስለነበር ቅስቀሳውን መቀጠሉ ሳያስፈልገን ወደየቤታችን ተመለስን፡፡

በጣም ያስገረሙኝ ነገሮች
አንደኛ- ኮማንደር ሀይለ ማርያም በደቂቃ ውስጥ የአቋም ለውጥ አድረገው እዚህ የምታድሩበት ምክንያት የለም፣ ውጡ፣ መቀስቀስም ትችላላችሁ፣ ብለው መናገራቸው፡፡ ከመጀመሪያው ስሜታቸው አንጻር የሚያስገርም ነበር፡፡
ሁለተኛው- የስብሰባው ፈቃድ ደብዳቤአችንን ግልባጭ አዲስ አበባ መስተዳድር ለተለያዩ መስሪያ ቤቶች በትኖታል፡፡ ከነዚህ መስሪያ ቤቶች አንዱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ነው፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መቼም ስብሰባው በልደታ ክ/ከተማ እንደሚደረግ እያወቀ ኢንፎርሜሽኑን ለልደታ ፖሊስ መምሪያ መስጠቱ የማይቀር ነው፡፡ ይህ ባይሆን እንኳን ተጠያቂው የአዲስ አበባ መስተዳድር ወይም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንጂ ኢዴፓ ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ የሚያሳየው ከአንድም ሁለት ቀን እንድንያዝ የሆነው ሆን ተብሎ በመንግስት ሀላፊዎች ትእዛዝ እንደሆነ አመላካች ነው፡፡ ስብሰባውን ፈቅዶ ጥሪውን መከልከል ስብሰባው እንዳይካሄድ ከመፈለግና ይህንኑ በተግባር ከማድረግ የተለየ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም፡፡ ይህ ደግሞ ህገ-ወጥ ተግባር ብቻም ሳይሆን መሰረታዊ የህገ-መንግስት ጥሰት ነው፡፡
ሦስተኛው- ኮማንደሩ የቅስቀሳ ፈቃድ ያስፈልጋል፣ ያለ ቅስቀሳ ፈቃድ መቀስቀስ አይቻልም ሲሉ እንዳልነበር ቀኑ ከመሸ በኃላ ቅስቀሳ ማድረግ እንደምንችልና ከጠዋት ጀምረን መታሰራችንን እርሳቸው አለማወቃቸውን ሲነግሩን ይህ ለእኛ ቀልድ ነው፡፡ በመጀመሪያ የያዙን ፖሊሶች ከመምሪያው ሐላፊዎች ጋር በመነጋገር ነው ቃላችንን እንድንሰጥ ያደረጉን፡፡ ስለዚህ የኮማንደሩ ቃል በጣም ተአማኒነት የጎደለው ነው፡፡
በአጠቃላይ- እንደኔ እምነት በእነዚህ ሁለት ቀናት በኢዴፓ አመራር እና አባላት ላይ የተሰራው ሁሉ ህገ- መንግስቱን የጣሰ ተግባር ነው፡፡ ይህ ድርጊት ስብሰባው እንዳይሳካ ሆን ተብሎ የተደረገ ድርጊት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገራችን የኢኮኖሚ ሙስና የሰሩ አንዳንድ ሰዎች በህግ ሲጠየቁ እያየን ነው፡፡ ነገር ግን እንደዚህ አይነት ህገ-መንግስቱን የሚፃረር የፖለቲካ ሙስና (political Corruption) የሰሩ አካላት መችና እንዴት ነው በህግ ሲጠየቁ ልናይ የምንችለው?

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter