እስር የመፍትሄ እርምጃ መሆኑ እስከመቼ ይቀጥል ይሆን?

Adane Tadesse, executive committee member of Ethiopian Democratic Partyከአዳነ ታደሰ
የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ አባል
ለሰንደቅ ጋዜጣ ነሃሴ 21 2006

ለዛሬ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ ጉዳይ በባለፈው ወርም ሀነ ከሰሞኑ በገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ እየተወሰደ ያለው የማሰርና የመክሰስ እርምጃ ነው፡፡ይሄ እርምጃው የስርአቱ መገለጫ ከሆነ ሰንበት ቢልም በዚህ ወቅት መሆኑ ስላሳሰበኝ የበኩሌን ለማለት ተነሳሳሁ፡፡ በዚህ የሰሞኑ የኢህአዴግ ባህሪ መጭው ምርጫ ከወዲሁ ውጥረት ውስጥ መግባቱ አልተመቸኝም፡፡ ለዚህም የፖለቲካውን አየር በየዕለቱ የሚምገው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ስጋቴን እነደሚጋራኝ እምነቴ ነው፡፡ይሄስ የኢህአዴግ የማሰር ተግባር መቼ ነው በውይይትና በጠረጴዛ ዙርያ ሰጥቶ በመቀበል መርህ በሚደረግ ድርድር የመፍታት ባህል የሚቀየረው ብዬ ሳስብ የበለጠ ስጋቴ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ የስጋቴ መጨመርም ያለምክንያት አይደለም፤ ይሄው መንግስት 23 አመት አለፈው ሲያስር፣ሲያስር፣ሲያስር እንጂ ኢትዮጵያ ያሉባት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሲፈቱ ግን አይተን አናውቅም፡፡

ይሄ መንግስት ምን ያህል ስር የሰደደ ችግሮችን በዴሞክራስያዊና በመቻቻል የመፍታት ባህሪው ደካማ መሆኑን ለማሳየት አበይት የሆኑትን የችግር መፍቻ ተደጋጋሚ ስልቱን  ለማስቃኘትና ለማስታወስ ይረዳ ዘንድ ወደ ኋላ ልመልሳችሁ፡፡

ገዥው ፓርቲ ገና አዲስ አበባን እንደተቆጣጠረና የመንግስትነት ስልጣኑን እንደተረከበ የመጀመርያ አበይት የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም የነበረው ትኩረት ሳቢ ነበር፡፡በዚህ በገዥው ፓርቲ ፊትአውራሪነት የተዘጋጀው ታላቅ እንድምታ ያለው ጉባኤም በጊዜው ወሳኝ እርምጃ ነበር፡፡  ብዙም ሳይቆይ በተቃዋሚዎች  የተዘጋጀው ታላቅ ጉባኤም በግዜው መነጋገርያ ነበር፡፡ ገዥው ፓርቲ የእስር መፍትሄውን ገና በትረ ስልጣኑን በያዘ ማግስት አንድ ብሎ የጀመረው ለጉባኤው የመጣውን የኢህአፓ አባል በማሰር ነው፡፡

አስቀድሞ በሽግግር መንግስቱ ምስረታ ጉባኤ ላይ በኤርትራ መገንጠል ዙርያ የሰላ ሂስ የሰነዘሩት አንጋፋ ምሁርና የቀዶ ጥገና ስፔሻሊስቱ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ሌላው ሰለባ የሆኑ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ እኝህ አንጋፋ ምሁር ያንን የሰላ ሂስ ከሰነዘሩ በኋላ መአህድ የሚባል ድርጅት መስርተው መንቀሳቀስ እንደጀመሩ በኢህአዴግና በሻቢያ የሚወደድ ትግባር ባለመሆኑ ከጅምሩ ነበር ጥርስ ውስጥ የገቡት፡፡ ፓርቲውን በመሰረቱ በሁለት አመት ውስጥ በ1986 ዓ.ም ደብረ ብርሃን ከተማ ላይ ፓርቲው በጠራው ስብሰባ ለአመጽ የሚቀሰቅስ ንግግር አድርገዋል በሚል ወደ ዘብጥያ ተወረወሩ፡፡

በ1987 መስከረም ወር የሳቸውን ዘብጥያ መውረድ በመቃወም ከፍተኛ ፍርድ ቤት ችሎት ጉዳያቸው እየታየ በነበረበት ወቅት “አስራት ይፈቱ” የሚሉ ደጋፊዎቻቸውን ወጣት፣ሽማግሌ፣አሮጊቶችን ሳይለይ ሰብስቦ ሰንዳፋና ኮልፌ ማሰልጠኛ ወስዶ አጉሯቸዋል፡፡ በኃላም ከአንድ ወር እስከ ሶስት ወር የሚደርስ የእስር ግዜ አሳልፈው እንደተመለሱ ጸሃፊው በግዜው የመአህድ አባል ስለነበረ የሚያስታውሰው ተግባር ነው፡፡ ፕሮፌሰሩም በዚሁ የእስር ጦስ እስር ቤት ውስጥ እያሉ ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል፡፡
ይሄን የማሰር ድርጊት አጠናክሮ የቀጠለው ኢህአዴግ ብዙም ሳይቆይ የመምህራን ማህበሩን ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታዬ ወልደ ሰማያትን በማሰር እና የሰራተኛ ማህበሩን አቶ ዳዊ ኢብራሂምን ለማሰር በማስፈራራት ከሀገር እንዲሰደዱ አድርጓል፡፡ ግን ይሄው  በመምህራን ማህበርና በሰራተኛ ማህበሮች የሚነሱ የመብት ጥያቄዎች ዛሬም እንደቀጠሉ ነው፡፡
በ1994 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ያነሱትን የመብት ጥያቄ ተከትሎ በተከሰተው ችግር ጉዳዩን አባብሳችኃል፣ አነሳስታችኃል በሚል ሰበብ የኢዴፓን ወጣት አመራሮች አቶ ልደቱ አያሌውን፣ አቶ ሙሼ ሰሙን ፣አቶ ተክሌ የሻውን እና ሌሎችንም በሸዋ ሮቢትና በዝዋይ እስር ቤቶች ወስዶ አስሯቸዋል፡፡ በኃላም ፓርቲው በፍርድ ቤት በከፈተው አካልን ነጻ የማውጣት (አቭየርኮርፐስ) ክስ በአመራሮቹ ላይ ከፍተኛ አካላዊ ጉስቁልና ቢደርስባቸውም  ሊያስለቅቃቸው ችሏል፡፡ ግን ይሄው በዩንቨርስቲዎች የሚነሱ የመብት ጥያቄዎችና ግጭቶችም እንደቀጠሉ ዛሬም አሉ፡፡

ከዛም በመቀጠል በ1997 ምርጫን ተከትሎ በተነሳው ሁከት  እጃቸው አለበት የተባሉትን የቅንጅት አመራሮችን ወደ ቃሊቲ በመክተት በመጨረሻ አመራሮች ባቀረቡት የይቅርታ ደብዳቤ መለቀቃቸው ይታወሳል፡፡ የይቅርታ ደብዳቤ አስገብተው ከተለቀቁት አመራሮች መካከልም በድጋሚ አልፈፅምም ብለሽ ቃል  የገባሽውን ጥፋት ፈፅመሻል ተብላ ወ/ት ቡርቱካን ሚደቅሳ በድጋሚ መታሠሯ ሣይዘነጋ ማለትነው፡፡ ይሄንን ምርጫ ተከትሎም ከፖለቲከኞቹ በተጨማሪ ጋዜጠኞችም ወደ ቃሊቲ ተወርውረዋል፡፡ ግን አሁንም ምርጫ በመጣ ቁጥር እስርና እገታው እንደቀጠለ ነው ህዝቡም በፍራቻ “ደሞ ይሄ ግንቦት መጣ” እያለ ነው፡፡

ከላይ የኢህአዴግ የእስር እርምጃዎች የጠቃቀስኩት ታሣሪዎቹ ህግ ጥሰው ነው? ሣይጥሱ? ጥፋተኛ   ናቸው? ጥፋተኛ አይደሉም? በሚል ለመከራከር አይደለም፡፡ ገዢው ፓርቲ ምን ያህል በስልጣን ዘመኑ እስርን የመፍትሄ አካል አድርጎና የስርአቱም መገለጫ ሆኖ እንደቀጠለ ለማሣየት ነው፡፡ ከላይ በማስታውሳቸው የእስር እርምጃዎች ውስጥ ከመጀመሪያው የእስር ታሪክ በስተቀር በሌሎቹ ውስጥ ለጉዳዩ ቅርብና የታሪኩም አካል ስለነበርኩ መፍተሄው ትክክል ነው ብዬ አላምንም፡፡ ኢህአዴግ ከእስር በተሻለ በውይይትና በድርድር ቢፈታው ይችል ነበር እላለሁ፡፡ ያንን አድርጎ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላይ የሀገራችን የፖለቲካ ባህል ከዚህ በተሻለ ደረጃ ላይ በተገኘ ነበር፡፡

በዚህ በባለፈው የሐምሌ ወር ይኸው የኢህአዴግ የማሠር አባዜ ደግሞ ማገርሸቱ ከመጪው ምርጫ አንፃር ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ ከሠሞኑ በፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ላይ የጸረ  ሽብሩን ህግ ተንተርሶ የተወሰደው እርምጃ ማንኛውንም ፖለቲከኛ እንደሚያስጨንቀው እኔንም አስጨንቆኛል፡፡ የሰላማዊ ትግሉንም አጣብቂኝ ውስጥ እንዳይከተውና በአንጻሩ ጽንፈኛ የሆኑትንም ወገኖች እንዳያጠናክር ስጋት አለኝ፡፡ መንግስት ዋነኛ ተግባሩ ሀገርንና ህዝቡን ከማንኛውም ጥፋት መከላከልና ደህንነቱን የማስጠበቅ ሃላፊነት እንዳለበት እምነቴ ጽኑ ነው፡፡ በጸረ-ሽብር ህጉ ላይ ያለው አተረጓጎም ግልጽ ያለመሆን በዚህም ምክንያት ያኔ ህጉ ሲወጣ የገለጽነው ስጋት አሁን በግልጽ እየታየ ችግሩም ጎልቶ እየወጣ ነው፡፡ አሁንም ግዜው አልረፈደምና የሽብርተኛ ህጉ በድጋሚ ቢታይና አተረጓጎም ላይ ያለው ክፍተት ቢደፈን ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ ምክንያቱም በቅርቡ የተወሰደው እርምጃ የፖለቲካ አመለካከትን ታይቶ ላለመወሰዱ እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል ነው፡፡  አለበለዚያ ግን ግልጽነት በሚጎለው ህግ በሚወሰድ እርምጃ የተነሳ የሰላማዊ ትግሉ እንቅስቃሴ ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ ነው የሚገባው፡፡ ባንጻሩ ሰላማዊ ትግሉ አያዋጣም ለሚሉት ወገኖችም ምክንያታዊነታቸውን እንዳያጠናክርና ሰላማዊ ትግሉን እንዳያዳክም መንግስት መጠንቀቅ አለበት እላለሁ፡፡ በዚህ ሀገር የሚመጣ መፍትሄ በሰላማዊ ትግል ብቻ መሆኑን ለማሳየት መንግስት የሰላማዊ ትግሉን ሜዳ ደልዳላ የማድረግ ሃላፊነቱን በቁርጠኝነት ሊወጣ ይገባል፡፡ ለሚነሱ ማንኛውም ጥያቄዎች ፖለቲካዊ እርምጃ ለመውሰድ መንግስት ከመጣደፍ ይልቅ ብስለት በተሞላበትና በሃላፊነት ስሜት ጥያቄውን ለመመለስ ጥረት ማድረግ አለበት፡፡

ሌላው ለሁለት አመት የዘለቀውን በሙስሊም እምነት ተከታዮች ዘንድ ለሚነሳው ጥያቄ  በውይይት ጉዳዩን ከመፍታት ይልቅ የሚወሰደው እርምጃ ላይ ስጋቶች አሉኝ፡፡ መንግስት ጥያቄያቸውን ከሽብርተኝነትና ከአክራሪነት ጋር በማገናኘት  አርብ በመጣ ቁጥር የሙስሊሙን ማህበረሰብ በማሰር መፍትሄ ለማምጣት መዳከሩ ውጤት የሚያስገኝ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም መንግስት የሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄ ሃይማኖታዊ አይደለም፣ጥቂት አክራሪዎች ናቸው፣ብዙሃኑ ሙስሊም ሰላማዊ ነው ካለ ሰላማዊ ናቸው ከሚላቸው ጋር በሰላማዊ ውይይት ችግሩን ለመፍታት ለምን አቃተው? እንደሚመስለኝ ይሄንንም  እንደተለመደው በማሰር አስተነፍሰዋለው ከሚል የተለመደ የግብተኝነት ባህሪው የሚመነጭ ካልሆነ በስተቀር ውሃ የሚቋጥር ምክንያት ማግኘት አይቻልም፡፡ ከዚህ ይልቅ ጥያቄያቸው ከጀርባው ሌላ ነገር ያዘለና ያላዘለ መሆኑንም ለማወቅ የሚያስችለው ሰላማዊ ጥረቱን አሟጦ ሲጠቀም ስለሆነ ችግሩ ሳይባባስ ሰላማዊ መድረክ አመቻችቶ ጥያቄያቸውን ሌላ ፖለቲካዊ ምክንያት ሳይሰጥ በሰለጠነ መንገድ ሊፈታው ይገባል፡፡
ተቃዋሚውም በሃይማኖት ጉዳይ ውስጥ በመግባት ጉዳዩን ከማባባስና የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት  ከሚደረግ ተገቢ ያልሆነ እንቅስቃሴ ራሱን ማራቅ አለበት፡፡ አንዳንድ ፖለቲከኞች የሙስሊሙን ጥያቄ ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ በማራገብና በማስጮህ መንግስት ከጀርባቸው የሚገፋቸው ሃይል አለ ብሎ ለሚያሰማው ክስና ሙስሊሙ ላይ ለሚያደርሰው ተጽእኖ ዱላ በማቀበል መተባበር የለባቸውም እላለሁ፡፡

የሙስሊሙም ማህበረሰብ የማንኛውም የፖለቲካ ሃይል መጠቀሚያ ከመሆን በመቆጠብ ከብጥብጥና ከሁከት በራቀ መልኩ፣የሌላውን ሙስሊም ወገኖቹን መብት ባልጣሰ ሁኔታ ጉዳዩን ለመፍታት ጥረት ማድረግ አለበት፡፡ በጥፋት ማንም ተጠቃሚ አይሆንምና፡፡ ችግሮቹን በትልልቅ ሃይማኖታዊ አባቶቹ በኩል መፍትሄ እንዲያገኝና ሃይማኖታዊ ስርአቱን በጠበቀ ሁኔታ እንዲቋጭ መንገዱን ማመቻቸትና ከመንግስታዊ አካላት ጋር በመነጋገር መጨረስ አለበት፡፡

ሌላው እና የመጨረሻው የሰሞኑ የስጋቴ ምንጭ በአንዳንድ የግሉ ፕሬስ አባላት ላይ ሊወሰድ የታሰበው እርምጃ ነው፡፡ በተወሰኑ የግል ፕሬሶች ላይ ሰሞኑን መንግስት ክስ መመስረቱን ስሰማ “ምን ነካው” ይሄ መንግስት ነው ያልኩት፡፡ በግሉ ፕሬስ ላይ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መኖራቸው ባይካድም ያለው ችግር ግን በዚህ መንገድ ይፈታል ብዬ አላስብም፡፡ ፕሬሱ እንደሌሎቹ ተቋሞቻችን የአቅም ውስኑነት፣ለሙያው ያለ ታማኝነት፣ከግራ ፖለቲካው የወረስነው የጥላቻ ፖለቲካ ሰለባ የመሆን ችግር የሚታይበት ዘርፍ ነው፡፡ ይሄ በአንዳንድ ውስን ጋዜጦች ላይ የሚታይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መንግስት የተወሰነ ድጋፍ ቢያደርግላቸው በአጭር ግዜ ይፈታል እላለሁ፡፡ መንግስት መረጃ የማግኘት ክፍተታቸውን የሚሞላ ከሆነ፣አቅማቸው የሚጠናከርበትን መንገድ የሚፈጥር ከሆነ፣በችግሮቻቸው ዙርያ ለመወያየት ፈቃደኛ ከሆነ የሀገራችን የፕሬስ ችግር በተወሰነ መልኩ ይቃለላል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ስለዚህ ከማሰርና ከማዋከብ በመለስ ጉዳዩን በሰለጠነ መንገድ በመፍታት ፕሬሱን ወደ ተሻለ ደረጃ የማሳደግ ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡

ይሄን ይሄን የሰሞኑን ሁኔታ ለሚታዘብ ማንኛውም ወገን መጭው ምርጫ ከመሆኑ አንጻር ጉዳዩ ቢያሳስበው በቂ ምክንያት ነው እላለሁ፡፡  መጪው 2007 ምርጫ በሰላማዊ መንገድ ተጀምሮ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ የሁሉም ወገን ሃላፊነት ይመስለኛል፡፡ በተለይ መንግስት ከሰሞኑ የሚወስዳቸው እርምጃዎች የ2007 ምርጫ ከወዲሁ በህዝቡ ዘንድ በስጋትና በፍራቻ እንዲጠበቅ እያደረገው ነው፡፡ መንግስት ስጋት ውስጥ ገብቶ ህዝቡንም ስጋት ውስጥ መክተት የለበትም፡፡ መንግስት የሚገጥሙትን ጉዳዮችና ችግሮች በሀይል ለመፍታት ከመጣደፍ ሰከን ሊል ይገባል፡፡ በሰላማዊ ትግል ውስጥ ያለን ፓርቲዎችም በሀላፊነት ስሜት በመንቀሳቀስ የዚችን አገር መፃኢ እድል በምርጫ ካርድ ላይ ብቻ በሚገኝ ለውጥ ላይ እንዲመሰረት መጣር አለብን፡፡ የምንወስዳቸው እርምጃዎችና የምንቀሰቅስባቸው መንገዶች ሁሉ ሀገራችንን ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረሳቸውንም እርግጠኛ መሆን አለብን፡፡ የፖለቲካ ትርፍን ታሳቢ ካደረጉ ያልተገቡ አካሄዶች መጠንቀቅ አለብን፡፡ የምንሄድበት መንገድ የምንሰራው ፖለቲካ ሀገር ማፍረስ ከሆነ ውጤቱ የታሪክ ተጠያቂ ከመሆን አንድንም፡፡ በፓርቲዎች ዘንድ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የሚለው የተለመደው የፖለቲካ አካሄድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በዚህ ትውልድ ማብቃት አለበት፡፡ ህዝቡም ለእንደዚህ አይነት ፖለቲካዊ አካሄዶች በጭፍን ድጋፍ ማድረግ አይኖርበትም፡፡ ለሚደግፋቸውም ሆነ ለሚቃወማቸው ፓርቲዎች ሚዛኑ መሆን ያለበት የሀገር መጠቀምና አለመጠቀም መሆኑን እርግጠኛ መሆን አለበት፡፡ ቸር እንሰንብት፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter