ከተፈናቀሉ ዜጎች ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከኢዴፓ የተሰጠ መግለጫ

ከተፈናቀሉ ዜጎች ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የተሰጠ መግለጫ

በፖለቲካም ሆነ በልማት ስም ያለበቂ ዝግጅትና ቅድመ ሁኔታ የተፈናቀሉ ዜጎች ጉዳይ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ኢዴፓ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

ባለፉት ዓመታት የአማራው ብሔረሰብ ተወላጆችና ሌሎችም ብሔር-ብሔረሰቦች በብሔረተኝነትና በፖለቲካ ምክንያት ሕይወታቸውን ከመሰረቱበት ቀየ ሲፈናቀሉና ሲሰደዱ መስማት የተለመደ ጉዳይ ነበር፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የመፈናቀሉ ጉዳይ ጋብ ያለ ቢመስልም የዛሬ ዓመት ገደማ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ከጉራፈርዳ ወረዳ በርካታ የአማራ ተወላጆችን መፈናቀልን ተከትሎ በቅርቡ ከሶማሌ ክልላዊ መንግስት ከጅጅጋ ከተማ በርካታ ቁጥር ያላቸው የአማራ ተወላጆች መፈናቀላቸው ተዘግቧል፡፡ አሁን በቅርቡ ደግሞ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት በሺህ የሚቆጠሩ አማራዎች የመፈናቀላቸው ጉዳይ ሰፊ የዜና ሽፋን አግኝቶል ከርሟል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከልማትና ከኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ ምክንያትም የኦሮሞው፣ የጋምቤላው፣ የአፋርና የሌሎች ብሔር- ብሔረሰቦች ከመኖርያ ሰፈራቸውና ከትውልድ ቀያቸው ያለበቂ ዝግጅትና ቅድመ ሁኔታ፤ የተገባላቸው ቃል ሳይከበርና ሕይወታቸውን ለማሳካት የሚያግዛቸው መሰረታዊ ነገር ሳይሟላ ተፈናቅለውና ተበትነው የመቅረታቸው ጉዳይ አሁንም የዓለም አቀፍና የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘገባ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡

ዜጎች የሚፈናቀሉበት ምክንያት ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ አሊያም ብሔረተኝነት፤  የትውልድ ቦታቸውና መሰረታቸው ከየትኛውም ብሔር ይነሳ የሚፈናቀሉትበት መንገድ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀበለቻቸውና ስምምነት የተደረሰባቸው የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን ያከበረ መሆን አለበት፡፡ በተለይ ደግሞ በሕገ-መንግስታችን ውስጥ በክፍል አንድ ሰብዓዊ መብቶች  አስመልክቶ በአንቀጽ 14 ላይ የሕይወት፣ የአካል ደህንነትና የነጻነት መብትን አስመልክቶ በተደነገገው መሰረት “ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነትና የነጻነት መብት አለው፡፡” የሚለውንና እንዲሁም በአንቀጽ 25 የእኩልነት መብት አስመልክቶ “ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው፤ በመካከላቸውም ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በሕግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ በዘር፣በብሔር ፣ በቀለም፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ አመጣጥ፣ በሀብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት አላቸው፡፡” የሚሉትና ሌሎችም መሰረታዊ የመብትና የሕልውና ጥያቄዎችን የማይጻረር መሆን ይገባዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ከላይ የተጠቀሱት መፈናቀሎች በስምምነትም ይፈጸሙ በአስገዳጅ ሁኔታ ዜጎቻችን የተፈናቀሉት በአንድ ሕገ-መንግስትና ሉአላዊ ሃገር ማዕቀፍ ውስጥ እንደመሆኑ መጠን መፈናቀላቸውንና ስደቱን ተከትሎ የተከስተው ማዋከብና ድብደባ አሳሳቢና አነጋጋሪ ጉዳይ  ከመሆኑም በላይ በማንኛውም ሞራላዊ መስፈርት ተቀባይነት የሌለው ድርጊት ነው፡፡

ዜጎች  ሕይወታቸውን ለማስቀጠል የሚያችሉበት የተሻለ መሰረት እስካልተፈጠረላቸው ድረስ የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ሕልውና ለማቆየት በሚችሉበት በማንኝውም ቦታ ላይ ሕጋዊ መንገድን ተከትለው የመስፈርና ሕይወታቸውን የማቆየት ጥያቄ  ከብሔረተኝነትም  ሆነ ከልማት ወይም ከየትኛውም የፖለቲካ ፍልስፍና በላይ የሆነ የሰብአዊ መብት አጀንዳ ነው፡፡ ማንኛውም መንግስት ዜጎች በሰላም ሰርቶ  የመኖር ሕይወታቸውን የማቆየት መብታቸው እንዳይጣስ ልዩ ጥበቃ የማድረግ ሕጋዊም ሆነ ሞራላዊ ግዴታ አለበት፡፡ ማንም ሊገነዘብው በሚችል ደረጃ ሁሉም የሰው ፍጡር በሰላም ሰርቶ ከመኖርና ሕይወቱን ከማቆየት በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው አጀንዳ የለውም፡፡ ከላይ ለማንሳት እንደተሞከረው እነዚህ በዜጎች ላይ የተፈጸሙ መፈናቀሎች መንስኤቸው ልማታዊም ይሁን ፖለቲካዊ ወይም የብሄረተኛነት ጥያቄ፤ ሃያ አንድ ዓመት ያስቆጠረው ብሔርን ያማከለው የኢህአዴግ የፖለቲካ ፍልስፍናና መሬትን በመንግስት መዳፍ ስር ጥገኛ ያደረገው የኢኮኖሚ ፖሊሲው ሊፈታውም ሆነ ሊገታው የማይችለው መሰረታዊ ችግሮች እንዳሉና በቀጣይም እንደሚኖሩ ፍንትው አደርገው የሚያሳዩ ሕያው መገለጫዎች ናቸው፡፡

የዜጎች የመፈናቀል ችግር ከሃያ አንድ ዓመት የብሔረተኛነት ፖለቲካና የገዢ መደብ መዳከም በኃላ ስደቱና መፈናቀሉ በተለያየ መልክ እንደገና ማገርሸቱ ኢህአዴግ እንደሚለው በብሔሮች ማንነት ላይ የተመስረተው የፖለቲካ ፍልስፍናውና መሬትን የመንግስት ንብረት ያደረገው የኢኮኖሚ አስተሳሰቡ በዜጎች ላይ የእኩልነት መንፈስ መፍጠርም ሆነ በመሬት ላይ የነበራቸውን ባለቤትነት ማረጋገጥ ያልቻለ ነው፡፡  ከዚህ በላይ በፊውዳሉም ሆነ በገዢ መደብ ስርዓት ውስጥ ዜጎች ያለበቂ ዝግጅትና ቅድመ ሁኔታ ከመሬታቸው፣ ከይዞታቸውና ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ያስቀራል የተባለለት የኢህአዴግ የብሔረተኝነት የፖለቲካ ፍልስፍና ዛሬም በርካታ ያልተፈቱ እቆቅልሾችን ያዘለ  መሆኑ ግልጽ ሆኗል፡፡ ከዚህ አኳያ ኢዴፓ ዜጎች በብሔር ማንነታቸው ኮርተው በመኖራቸው ሕጉ የሚያጎናጽፍላቸው መብትና ጥቅም የመኖሩን ያህል ኢትዮጵያዊ ነን ሲሉም ከጋራ የስም መጠርያነትና ስሙ ከሚጥለው ግዴታ የማይነጠል ሁሉንም በጋራና በእኩሌታ የሚያጎናጽፋቸው መብትና ጥቅም ሊኖረው ይገባል የሚል ጽኑ እምነት አለው፡፡

በኢንቨስትመንት ስምም ሆነ በብሔሮች መካከል በሚከሰቱ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ግጭቶች በሚቀሰቅሱት መፈናቀል ምክንያት የሚፈጠሩትን የዜጎች ዋይታና ለቅሶ መስማት ለማንም ዜጋ የሚያስደስት ዜማ እንዳልሆነ የኢህአዴግ የፖለቲካ ፍልስፍና በተግባር ማረጋገጥ እንዳለበት ኢዴፓ አበክሮ ያሳስባል፡፡ በዚህ ምክንያትም ዜጎች በሃገራቸው ላይ እምነት ሲያጡ የማናይበትና የማናዳምጥበት ቀን በኢትዮጵያ ምድር እንዲፈጥር እንፈልጋለን፡፡ በየክልሎቹ የሚከናወኑ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችም አንዱን ብሄር ከሌላው እየለዩ የማያፈናቅሉና ሁሉንም ዜጎች ሰው ሆኖ በመፈጠር የሚቀዳጃቸውን መብቶች የማይሸረሽሩ መሆናቸው መረጋገጥ አለበት፡፡

ዜጎች በታሪክ አጋጣሚ በተገኙበትና ለዓመታት በኖሩበት አንዲሁም ጥሪት ባፈሩበት ቦታ ላይ ሁሉ ያለስጋትና ያለጥርጣሬ መኖር መቻላቸውና ለዚህም ጥበቃ እንደሚደረግላቸው ስርዓቱ መተማመኛ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ አስገዳጅ ሁኔታዎች ዜጎችን ለመፈናቀል የሚዳርጋቸው ቢሆን እንኳን መፈናቀሉ በበቂ ቅድመ ዝግጅት ላይ ተመስርቶና ለሕልውናቸው መሰንበት የሚያስፈልጋቸው  መሰረታዊ  አቅርቦት መሟላቱን ማረጋገጥ ከሕገ-መንግስታዊም ሆነ ከሞራል አኳያ በመንግስት ላይ የወደቀ ግዴታ መሆኑ ለአንድ አፍታም ቢሆን መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ መሆኑን ኢዴፓ በጽኑ ያምናል፡፡

ከዚህ በመነሳት በዚህ ዓመት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በጉራፈርዳ ወረዳ፣ በሱማሌ ሕዝቦች ክልል በጅጅጋ ከተማ አንዲሆም በቤንሻንጉልና ጉሙዝ  ክልል ያሶ ወረዳ የተፈናቀሉ አማራዎች ጉዳይ አንዲሁም በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በሶማሌና በሌሎቹም ክልሎች  የተፈናቀሉ ዜጎች ጉዳይ ያስከተለው የሰብአዊ መብት ጥሰትና ማህበራዊ ቀውስ፤ በየክልሉ በሚኖሩ ቀሪዎቹ ዜጎች በሰላም ሰርቶ የመኖር ፍላጎትና ሃበት ባፈሩበት ቀየ የመሰንበት ጥያቄ ላይ ስጋት እያጫረ እንደሆነ ኢዴፓ ተገንዝቧል፡፡

ይህ የስነልቦና ቀውስ በተፈናቃዮችም ሆነ ከክልላቸው ውጭ በሚኖሩ ዜጎች ላይ ያስከተለው ስጋትና ጥርጣሬ እንደ ሕዝብ ጥያቄ ተገቢውን መልስ ማግኝት እንዳለበት ኢዴፓ ያምናል፡፡ ከዚህ በመነሳትም  መንግስት ለጉዳዩ ነጻና ገለልተኛ አካል በማቋቋም በጉዳዩ ላይ ተገቢውን ሕጋዊ ማጣራት በማድረግ  ሕጋዊ መፍትሔ እንዲያበጅለት ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ መፍትሔው ዘለቄታ ባለው መልክ ከዚህ በኃላ ያለበቂ ዝግጅት ከመሬቶቻቸውና ከቅያቸው የመነቀልና የመሰደድ ምዕራፍን ደምደሞ የተፈናቀሉም ሆነ በስጋት ላይ የሚገኙ ዜጎች ሕይወታቸውን በተረጋጋ መንገድ እንዲቀጥሉ መፍትሄ ሰጭና አቅጣጫ ጠቋሚ አንዲሆኑ ኢዴፓ ጥሪውን  በድጋሚ ያቀርባል፡፡

 

ሰላምና ህብረ ብሔራዊነት ዓላማችን ነው!
የኢዴፓ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ሚያዚያ 1/2005

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter