በሐረር ከተማ የተፈጠረው ችግር አስቸኳይ መፍትሄ ያሻዋል!

ቀን 02/07/2006 ዓ.ም
ቁጥር ኢ.ዴ.ፓ.023/06

የካቲት 30 ቀን 2006 ዓ.ም ምሽት ሁለት ሰዓት አካባቢ በሐረር ከተማ ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ ተከስቷል፡፡ ከዚህ በፊትም በዚሁ አካባቢ ተደጋጋሚ የእሳት ቃጠሎዎች መከሰታቸው ይታወሳል፡፡ ችግሩ እንደተከሰተ መንግሥት ድርጊቱን የፈፀመውን አካል ለማወቅ የማጣራትና ህብረተሰቡን የማረጋጋት ሥራ መሥራት ሲገባው በተመሳሳይ ቀን በተቻኮለ ሁኔታ ግሬደር አቅርቦ አካባቢውን ማፅዳት በመጀመሩ ህብረተሰቡ በመንግሥት ላይ የተለያዩ ጥርጣሬዎች እንዲያድሩበት ምክንያት ሆኗል፡፡

በዚህም ምክንያት አላስፈላጊ ግጭት ተፈጥሮ ንብረት ወድሟል፣ የንግድ እንቅስቃሴ ተቋርጧል፣ በሰዎችና በሰላማዊ ህይዎታቸው ላይ መጠኑ ያልተረጋገጠ ጉዳት ደርሷል፡፡ ስለሆነም መንግሥት እንደነዚህ እና መሰል ችግሮች ሲከሰቱ በሰከነ መንገድና ግልፅነት ባለው አሰራር ከህብረተሰቡ ጋር እየተመካከረ መፍታት ይገባዋል ብሎ ኢዴፓ በፅኑ ያምናል፡፡ ህብረተሰቡም ግጭቱ አቅጣጫውን ስቶ ተጨማሪ አላስፈላጊ ጉዳት እንዳይደርስ የበኩሉን አስተዋፅዖ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት የተፈጠረውን ግጭት መንግሥት ቆም ብሎ ችግሩ የተፈጠረበት ምክንያት ምን እንደሆነና ማን እንደፈጠረው በአስቸኳይ አጣርቶ እርምጃ እንዲወስድና በቃጠሎው ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ተገቢውን መፍትሄ በአስቸኳይ እንዲሠጥ ኢዴፓ በጥብቅ ያሳስባል፡፡

የኢዴፓ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

ሰላምና ህብረ-ብሔራዊነት አላማችን ነው!

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter